የአሰልጣኞች አስተያየት | ቅዱስ ጊዮርጊስ 6-2 ሲዳማ ቡና

በ12ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በአዲስ አበባ ስታዲየም ሲዳማ ቡናን አስተናግዶ 6–2 በሆነ ውጤት ቅዱስ ጊዮርጊስ ካሸነፈ በኃላ የፈረሰኞቹ አሰልጣኝ ሀሳባቸውን ሲሰጡ የሲዳማ ቡና አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ በየት በኩል እንደሄዱ ሳይታዩ አስተያየት ሳይሰጡ ከስታዲየም ወጥተዋል። 


“ቅዱስ ጊዮርጊስ ምን ዓይነት እግር ኳስ መጫወት እንዳለበት ያሳየንበት ነበር” አሰልጣኝ ሰርዳን ዝቪጅኖቭ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)

ስለጨዋታው

እንደማስበው ዛሬ ጨዋታውን ለመታደም የመጣውን ተመልካቾች ተዝናንተዋል፤ ስድስት ጎሎችን በማስቆጠራችን። ስለፍፁም ቅጣት ምቱ እርግጠኛ ባልሆንም በሰራናቸው ስህተቶች ነው ሁለት ጎሎች የተቆጠሩብን። በአጠቃላይ ግን ቅዱስ ጊዮርጊስ ምን ዓይነት እግር ኳስ መጫወት እንዳለበት ያሳየንበት ጨዋታ ነበር። በማጥቃት ላይ የተመሰረተ እና በርካታ ግቦችን ለማስቆጠር ጥረት የታየበት ነበር። ጥሩ ተጫውተናል ደስም ብሎኛል። ተጫዋቾቼንም እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለው። በእርግጥ ቀላል አልነበረም፤ ምክንያቱም በተደራራቢ ጨዋታዎች ተጫዋቾች ተዳክመው ነበር። ቢሆንም ግን ጥሩ ጨዋታ አሳይተን በብዙ ጎሎች አስቆጥረን አሸንፈናል። አሁን ትኩረታችን በቀጣዮቹ የፋሲል እና የወልዋሎ ጨዋታ ላይ መሆን አለበት። ዛሬን በውጤቱ ተደስተን ሥራችንን እንቀጥላለን፤ ሊጉ ረጅም ጉዞ በመሆኑ።

ሊጉን መምራት ስለመጀመራቸው

አላወኩም፤ ሰንጠረዡን አልተመለከትኩም። ነገር ግን ሊጉ ረጅም እና መጨረሻውም ሩቅ ነው። በሰንጠረዡ አናት ላይ ብንሆንም ጥሩ ነው። ነገር ግን ቻምፒዮን ለመሆን ትኩረት አድርገን ሁሉንም ጨዋታ እንደዛሬው መጫወት ይኖርብናል።

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ