በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አስራ ሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ መደረግ ሲጀምሩ ወላይታ ድቻ ወደ ድል የተመለሠበትን ውጤት ድሬዳዋን በመርታት አስመዝግቧል፡፡
ወላይታ ድቻዎች በአስራ አንደኛ ሳምንት በሀዋሳ ከተረታው አሰላለፍ ውስጥ በአንድ ተጫዋች ላይ ለውጥ ሲያደርጉ ያሬድ ዳዊትን ከጉዳት በተመለሰው ደጉ ደበበ ተክተው ወደ ሜዳ የገቡ ሲሆን በአንፃሩ ድሬዳዋ ከተማዎችም በተመሳሳይ ያሬድ ሀሰንን በአማኑኤል ተሾመ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡
የዕለቱ ዋና ዳኛ እያሱ ፈንቴ ገና የፊሽካቸው ድምፅ እንደተስተጋባ ቅፅበታዊ የሆነች ፈጣን ግብ ተስተናግዷል፡፡ 40 ሰከንድ ብቻ እንደተቆጠረ የድሬዳዋው ሪችሞንድ አዶንጎ ኳስን እንደጀመረ ከእግሩ ስር እድሪስ ሰዒድ በፍጥነት ነጥቆ ወደ ድሬዳዋ ግብ ክልል ተጠግቶ ያሻገረለትን ኳስ እዮብ ዓለማየሁ የግብ ጠባቂው ሳምሶን አሰፋን ጎል ለቆ መውጣት በመጠቀም የዓመቱ ፈጣኗን ግብ በማስቆጠር ወላይታ ድቻን መሪ አድርጓል፡፡
ግብ ካስቆጠሩ በኃላ በድሬዳዋ የግብ ክልል ሲያነፈንፉ የነበሩት ወላይታ ድቻዎች ከአማካዩ እድሪስ መነሾ የሆኑና ከመስመር ወደ ጎን አጥበው ለሚጫወቱት የመስመር ተጫዋቾቹ እዮብ አለማየሁ እና ቸርነት ጉግሳ ቶሎ ቶሎ በማድረስ ጫናዎችን በብርቱካናማዎቹ ላይ በተደጋጋሚ አሳድረዋል። በዚህም ሂደት 6ኛው ደቂቃ እዮብ አለማየሁ ከመስመር ያሻገራትን ኳስ በጎሉ አቅራቢያ የነበረው ባዬ ገዛኸኝ ወደ ጎል ሞክሯት የግቡን አግዳሚ ትማ ወደ ውጭ ወጥታበታለች፡፡
የአደራደር ስህተት በተደጋጋሚ በተከላካዮቹ ላይ ሲታይባቸው የነበሩት ድሬዳዋ ከተማዎች ለማጥቃት ከመሞከር ይልቅ ብልጫ የተወሰደባቸውን የወላይታ ድቻ ጥቃትን መሰንዘር ላይ ተጠምደው ውለዋል፡፡ 10ኛው ደቂቃ ላይ ቸርነት ጉግሳ ለባዬ ገዛኸኝ አቀብሎት ባዬ ገዛኸኝ ከርቀት የመታት ኳስ ለጥቂት በጎሉ አናት ወደ ውጪ ከወጣች ሁለት ደቂቃ በኃላ ሁለተኛ ግብ ባለሜዳዎች አስቆጥረዋል፡፡ 12ኛው ደቂቃ በጨዋታው ጥሩ ጥምረት ሲያሳዩ የነበሩት እድሪስ ሰይድ እና ቸርነት ጉግሳ ተቀባብለው ያመጡትን ኳስ ቸርነት ጉግሳ ለባዬ ገዛኸኝ በቀኝ በኩል ወደ ግብ የላከለትን ባዬ ገዛኸኝ በጥሩ አጨራረስ ወደ ግብነት ቀይሮት የጎል ልዩነቱን ከፍ አድርጎታል፡፡
ጨዋታው የከበዳቸው ድሬዳዋ ከተማዎች ምንም ዓይነት ሁነኛ ሙከራ ለማድረግ ቢቸገሩም በሪችሞንድ አዶንጎ ወደ ግብ ለመጠጋት በተወሰነ መልኩ ጥረት አድርገዋል። ሆኖም አጥቂው ወደ ግብ ለመድረስ በሚያደርገው ጥረት የወላይታን የተከላካይ ክፍል ሰብሮ ለመግባት በደንብ መቸገሩን ካደረጋቸው እንቅስቃሴዎች መረዳት ይቻላል፡፡ በጉልህ በመከላከሉ ደካማ የነበሩት ድሬዎች 18ኛው ደቂቃ ጉዳት ያስተናገደው ዘሪሁን አሼንቦን በማስወጣት በረከት ሳሙኤልን ተክተው አስገብተዋል፡፡ በረከት ወደ ሜዳ ሲገባም እንደ ዘሪሁን ሁሉ ጉዳቱን ይዞ የገባ ቢሆንም በሜዳ ላይ ያደረገው እንቅስቃሴ ለድሬዳዋ ከተማ የተከላካይ ክፍል መረጋጋት የሰጠ ሆኗል፡፡
ጥቃት ሲሰነዘርባቸው የነበሩት እንግዳዎቹ በ26ኛው ደቂቃ እድሪስ ሰይድ ያሻገረለትን ኳስ ቸርነት ጉግሳ በደረቱ ለይ በማሳረፍ ይዞት የገባውን ኳስ ወደ ጎል መቶት ለጥቂት ወደ ውጪ አሁንም ወጣ እንጂ የድቻን የግብ መጠን ባሰፋ ነበር፡፡ 40ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብን አክለዋል፡፡ ፀጋዬ አበራ ከራሳቸው ግብ ክልል ተነስቶ በቀኝ መስመር አመርቂ አቋሙን ለክለቡ እያሳየ ላለው ቸርነት ጉግሳ ሰጥቶት ወጣቱ ተጫዋችም ከመስመር ተነስቶ ኳስን ወደ ጎል ይዞ በመግባት ጣጣውን የጨረሰ ኳስ አሻግሮ እዮብ አለማየሁ በሚገባ ተጠቅሟት ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ደግሞ ሦስተኛዋን ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡
42ኛው ደቂቃ ቸርነት ጉግሳ ከቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ አጥቂው ባዬ ገዛኸኝ በግንባር ወደ ግብ ቢገጫትም ግብ ጠባቂው ሳምሶን አሰፋ በጥሩ ሁኔታ አድኖበታል፡፡ አጋማሹ ሊጠናቀቅ በጭማሪ ደቂቃ 45+1 ከቅጣት ምት ኤልያስ ማሞ ወደ ግብ መቶ ኳስ ለጥቂት በጎሉ አናት ላይ የወጣችሁ ምናልባትም ይህቺ ሙከራ ድሬዳዋ ከነማዎች የሞከሯት የመጀመሪያዋ የጠራች የአጋማሹ ሁነኛ ሙከራ ነች፡፡ በጭማሪ ደቂቃ ላይ ቸርነት ጉግሳ በክፍት አጋጣሚ ተጨማሪ ጎል የሚሆን የግብ ዕድልን አግኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡
ከእረፍት መልስ ድሬዎች ሁለት ተጫዋቾችን ቀይረው ካስገቡ በኃላ በመጀመሪያው አጋማሽ የነበረባቸውን ደካማ እንቅስቃሴ የካሰ የሜዳ ላይ አቋምን አሳይተዋል፡፡ ያሬድ ታደሰን በያሬድ ሀሰን አማኑኤል ተሾመን በፈርሀን ሰይድ ከለወጡ በኃላ መጠነኛ መሻሻሎችን ቢያሳዩም ግብ የማስቆጠር ግን አልቻሉም። ወላይታ ድቻ በአንፃሩ በመጀመሪያው አጋማሽ የነበረው አቀራረብ ለወጥ በማድረግ ውጤት የሚስጠበቅ የሚመስል የጨዋታ መንገድን ተከትለዋል፡፡
55ኛው ደቂቃ ቸርነት ጉግሳ እና ባዬ ገዛኸኝ አንድ ሁለት ተቀባብለው ቸርነት ጉግሳ ወደ ጎል የመታት ኳስ ወደ ውጭ ወጥታበታለች፡፡ በ60ኛው ደቂቃ ያሲን ጀማል ከቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ
ፍሬዘር ካሳ በግንባር ገጭቶት ግብ ጠባቂው መክብብ ደገፋ በቀላሉ ይዞበታል፡፡ 71ኛው ደቂቃ ደግሞ ተስፋዬ አለባቸው ከመሃል ሜዳ በጥሩ ሁኔታ ያሻገረለትን ኳስ በእዮብ አለማየሁ ተቀይሮ የገባው ፀጋዬ ብርሃኑ ኳሷን ተቆጣጥሮ ወደ ጎል ሲደርስ ተከላካዩ በረከት ሳሙኤል ታክል በመውረድ አስጥሎታል፡፡ 83ኛ ደቂቃ ያሲን ጀማል ያሻማውን ኳስ ፍርዓን ሰዒድ በግንባር ገጭቶ ግብ ጠባቂው መክብብ ደገፋ በቀላሉ አድኖበታል፡፡
ወላይታ ድቻዎች በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ተስፋዬ አለባቸው መሀል ለመሀል ሰቶት ቸርነት አግኝቷት ወደ ግብ እየነዳ ገብቶ በረከት ሳሙኤል ከጉዳቱ ጋር እየታገለ በግሩም መልኩ አስጥሎታል፡፡ ከመጀመሪያው አጋማሽ በረከት ሳሙኤልን ከለወጡ በኃላ ግባቸውን ያላስደፈሩት ድሬዎች በመጀመሪያ አጋማሽ በተቆጠረባቸው ሶስት ግብ ለመሸነፍ ተገደዋል፡፡ ይህም በሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ ወላይታ ድቻ ድሬዳዋ ከተማን የረታበት ሆኗል፡፡
✿ ጨዋታው እየተደረገ ባለበት ወቅት የወላይታ ድቻው ግብ ጠባቂ መክብብ ደገፉ ደጋፊዎቹ ድጋፋቸውን ሲያቆሙ እየዞረ እንዲነቃቁ የሚያደርግበት መንገድ ራሳቸው ደጋፊዎች በተደጋጋሚ ሙገሳ ሲቸረው ያየን ሲሆን ቡድኑ እየመራ ከመሆኑም አንፃር ሜዳ ላይ ኳስን ሲይዝ ድራማዊ በሆኑ አክርባቶች እየተጠቀመ ኳስን የሚይዝበት መንገድ በርካቶችን ፈገግ ያሰኙ ድርጊቶች ነበሩ፡፡
©ሶከር ኢትዮጵያ