ሪፖርት | ጅማ አባ ጅፋር ከወራጅ ቀጠና የወጣበትን ድል መቐለ ላይ አሳክቷል

በዛሬው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውሎ ጅማ ላይ መቐለ  70 እንደርታን ያስተናገደው ጅማ አባ ጅፋር በቡዙዓየሁ እንዳሻው ብቸኛ ግብ 1-0 ማሸነፍ ችሏል።

በካቻምና እና ዐምና የሊጉ ቻምፒዮኖች መካከል የተደረገው ጨዋታ ካሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት አንፃር በሁለቱም በኩል በርካታ የተጨዋቾች ለውጥ የተደረገበት ነበር። በ11ኛው ሳምንት ፋሲል ከነማን አስተናግደው የነበሩት ጅማዎች ያለግብ ከተለያየው ቡድናቸው የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ከድር ኸይረዲን ፣ ኤልያስ አታሮ ፣ ሄኖክ ገምቴሳ ፣ ሀብታመ ንጉሴ እና አምረላ ደልታታ በዛሬው ጨዋታ በወንድምአገኝ ማርቆስ ፣ አሌክስ አሙዙ ፣ ሱራፌል ዐወል ፣ ብሩክ ገብረአብ እና ቡዙዓየሁ እንዳሻው ተተክተዋል። በተለይ በስራ ፈቃድ ጉዳይ እስካሁን ጨዋታ ሳያደርግ የቆየው አሌክስ አሙዙ ለመጀርያ ጊዜ ተሰልፎ መጫወት ችሏል። 

በተመሳሳይ የአምስት ተጫዋቾች ለውጥ ያደረጉት መቐለዎች ሽረን ባሸነፉበት ጨዋታ ከተጠቀሙት ስብስብ አኳያ አስናቀ ሞገስ ፣ ዮናስ ገረመው ፣ ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ ፣ ያሬድ ከበደ እና የቀይ ካርድ ተመልክቶ የነበረው ኦኪኪ አፎላቢን ቦታ በታፈሰ ሰረካ ፣ ሄኖክ ኢሳይያስ ፣ አሚኑ ነስሩ ፣ ሳሙኤል ሳሊሶ ፣ እና ክብሮም አብፅአ ሸፍናዋል።

የዕለቱ ጨዋታ የቀይ መስቀል የህክምና ቡድን አባላት በሰዓቱ ባለመገኘታቸው መጀመር ከነበረበት አስር ደቂቃዎችን ዘግይቶ የጀመረ ነበር። በመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች በነበረው እንቅስቃሴ ጅማ አባ ጅፋሮች የተሻሉ ሆነው ቢታዩም በሙከራ ረገድ መቐለዎች በወሳኙ አጥቂያቸው አማኑኤል ገብረሚካኤል የማጥቃት መስመር በኩል በሚላኩ ተሻጋሪ ኳሶች አማካይነት የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን የመፍጠር ሙከራዎች ሲያደርጉ ተስተውሏል። 

ያም ቢሆን ጅማ አባ ጅፋሮች ከጨዋታው ሦስት ነጥብ ይዘው እንዲወጡ ያስቻላቸውን ግብ ማስቆጠር የቻሉት በዚሁ አጋማሽ ነበር። በ30ኛው ደቂቃ ብሩክ ገብረዓብ ለብዙአየሁ እንዳሻው ካሻገረለት ኳስ መነሻነት አጥቂው የተከላካዮችን ስህተት በአግባቡ በመጠቀም ባለሜዳዎቹን ጅማዎች መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቡ በኃላ የጨዋታው ፍጥነት በሁለቱም በኩል የጨመረ ሲሆን ሁለቱም ቡድኖች በተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችለዋል። ነገር ግን ተጨማሪ ግብ ያልተስተናገደበት የመጀመሪያው አጋማሽ በጅማዎች 1-0 መሪነት ተጠናቋል።
ከዕረፍት መልስ መቐለዎች ታፈሰ ሰረካን በማስወጣት እና ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስን በማስገባት የጨዋታ አቀራረባቸውን በመቀየር ነበር ጨዋታውን የጀመሩት። በአንፃሩ ጅማዎች መሪነታቸውን አስጠብቀው ለመዝለቅ ጥረት ማድረግን ምርጫቸው አድርገው ታይተዋል።

እንግዳው ቡድን ጥቅጥቅ ብለው የሚከላከሉትን የጅማ ተከላካዮችን ለማለፍ በተለይም በመስመር በኩል በአማኑኤል ገብረሚካኤል እና ሙልጌታ ወልደጊዮርጊስ በኩል ተደጋጋሚ የግብ ዕድል ቢፈጥርም ሙከራዎቻቸው የጅማውን ግብ ጠባቂ ሰዒድ ሀብታሙን አለፈው ግብ ለመሆን ሳይችሉ ቀርተዋል። የመቐለን የመስመር ጥቃት መቋቋም የቻሉት ጅማዎች ሙሉ ለሙሉ አፈግፍገው በመከላከል በመጀመሪያው አጋማሽ የተገኘችውን የቡዙዓየሁ እንዳሻው ግብ አስጠብቀው መውጣት ችለዋል። 

ውጤቱን ተከትሎም ጅማ አባ ጅፋሮች ከወራጅ ቀጠና ወጥተው ወደ 12ኛ ደረጃ ከፍ ማለት ሲችሉ ሊጉን እየመሩ የነበሩት መቐለ 70 እንደርታዎች ቦታቸውን አዲስ አበባ ላይ ድል ለቀናው ቅዱስ ጊዮርጊስ ለማስረከብ ተገደዋል።
©ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ