ከቀናት በፊት ቡድኑ ስሑል ሽረ መቐለ 70 እንደርታን በገጠመበት ጨዋታ በ68ኛው ደቂቃ ላይ ከስነ-ምግባር ውጭ የሆነ ተግባር የፈፀመው ይህ ዩጋንዳዊ አማካይ ባልተሰለፈበት የዛሬው ጨዋታ መጀመር አስቀድሞ ወደ ሜዳ በመውጣት በድርጊቱ ላዘኑት የእግር ኳስ ቤተሰቦች በይፋ ይቅርታ ጠይቋል።
ተጫዋቹ በዕለቱ ተቀይሮ ሲወጣ በተለምዶ የስቴድየሙ አጠራር በፀሀይ በኩል ከሚቀመጡት የመቐለ ደጋፊዎች ግጭት ውስጥ የገባው አማካዩ በሰዓቱ ደጋፊዎችን ለነውጥ በሚገፋፋ መልኩ ላሳየው ያልተገባ ባህርይ ነው ይቅርታ የጠየቀው።
ተጫዋቹ በሰዓቱ ባሳየው ተግባር ከደጋፊዎች ተቃውሞ የደረሰበት ሲሆን የተወሰኑ ደጋፊዎችም ከተጫዋቹ ጋር የከረረ ፀብ ውስጥ ከመግባታቸው በፊት በስሑል ሽረ ቴክኒካል ዳይሬክተር አቶ በረከት ገብረመድህን እና የአሰልጣኞች ቡድን አባላት አማካኝነት ወደ ቡድኑ መቀመጫ አምርቷል።
ከስሑል ሽረ ጋር ያለውን ውል ለማራዘም በሂደት ላይ ያለው ይህ አማካይ በዛሬው ጨዋታ ቡድኑን ያላገለገለ ሲሆን በቀጣይ ቀናት የውል የማራዘሙ ሂደት ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
© ሶከር ኢትዮጵያ