በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 12ኛ ሳምንት ነገ ከሚደረጉት ሁለት ጨዋታዎች መካከል የሆነው የሰበታ ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕናን ጨዋታ እንዲህ ተመልክተነዋል።
ሰበታ ከተማ ከቀናት በፊት በድሬዳዋ ከደረሰበት ሽንፈት አገግሞ ደረጃውን ለማሻሻል በማለም የነገውን የአዲስ አበባ ስታዲየም መርሐ ግብር ይጠባበቃል።
የሰበታ ከተማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ) | ||||
ተሸነፈ | አሸነፈ | ተሸነፈ | አሸነፈ | ተሸነፈ |
የውበቱ አባተ ቡድን በሊጉ ከሰበሰባቸው ነጥቦች አመዛኙን ባሳካበት የአዲስ አበባ ስታዲየም በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ከዚህ ቀደም እንደሚያደርገው ሁሉ ጨዋታውን ተቆጣጥሮ ለመጫወት ጥረት እንደሚያደርግ ይጠበቃል። ተጋጣሚው ሆሳዕና በተከታታይ ሽንፈት ያስተናገደ እና በሊጉ ግርጌ ላየረ የሚገኝ ቡድን እንደመሆኑ ከነገው ጨዋታ ቢያንስ አንድ ነጥብ ማሳካትን ምርጫው አድርጎ ከገባ የኳስ ቁጥጥር ላይ ባመዘነው አጨዋወቱ የጎል እድል መፍጠር ሊቸገር የሚችልበት አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል።
ቡድኑ በአማራጭነት የሚጠቀምበት የተሻጋሪ እና ድንገተኛ የሆኑ ቀጥተኛ አጨዋወቶች ነገ ውጤት ሊያስገኙለት ይችላሉ። በተለይ ተጋጣሚው የ3 ተከላካዮችን ጥምረት ምርጫው ካደረገ ጥሩ ከኳስ ውጪ እንቅስቃሴ ያላቸው የሰበታ አጥቂዎች በተከላካዮቹ መሐል በመገኘት የሚኖረውን ክፍተት ተጠቅመው አደጋ እንደሚፈጥሩ ይጠበቃል።
በኤዲት የተካተተ፡ ሰበታ ከተማ ዳዊት እስጢፋኖስ፣ በኃይሉ አሰፋ እና ሳቪዮ ካቩጎ አሁንም ጉዳት ላይ ሲሆኑ አስቻለው ግርማ ከጉዳት ተመልሷል። አዲስ ተስፋዬ ደግሞ በአምስት ቢጫ ጨዋታው ያልፈዋል።
የሀዲያ ሆሳዕና ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ) | ||||
ተሸነፈ | ተሸነፈ | አቻ | አሸነፈ | አሸነፈ |
ከደካማ አጀማመሩ የነቃበትን ተከታታይ ድል ካስመዘገበ በኋላ ባለፉት ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ተሸንፎ በድጋሚ ግርጌው ላይ የተቀመጠው ሀዲያ ሆሳዕና ከወዲሁ ከበላዩ ካሉት ቡድኖች በነጥብ ላለመራቅ ማሸነፍን አልሞ ወደ ሜዳ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።
ከሜዳው ውጪ አንድ ጨዋታ ከማሸነፉ በቀር በሌሎቹ ሽንፈት ያስተናገደው ሆሳዕና በነገው ጨዋታ አፈግፍጎ ክፍተቶችን በመድፈን እና በአደጋ ክልል የመቀባበያ አማራጮችን በመዝጋት ላይ አተኩሮ እንደሚጫወት ሲጠበቅ በፈጣን መልሶ ማጥቃት አደጋ መፍጠርን ምርጫቸው ያደርጋሉ ተብሎም ይገመታል። እዩኤል ሳሙኤል እና ሁለቱ ቢስማርኮች ከሰበታ ተከላካይ ጀርባ የሚጣሉ ኳሶችን በመጠቀም ጎል ለማግኘት ጥረት እንደሚያደርጉም ይጠበቃል። ሆኖም በነገው ጨዋታ የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች ይሁን እንደሻው በቅጣት አለመኖር በኳስ ስርጭቱ እና ጥቃት በማስጀመሩ ረገድ አሉታዊ ተፅእኖ መፍጠሩ አይቀሬ ነው።
በነብሮቹ በኩል ይሁን እንደሻው በአምስት ቢጫ ቅጣት የማይሰለፍ ሲሆን በጉዳት አብዱልሰመድ ዓሊ ጨዋታው ያመልጣቸዋል።
እርስ በርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለመጀመርያ ጊዜ ይገናኛሉ።
ግምታዊ አሰላለፍ
ሰበታ ከተማ (4-3-3)
ዳንኤል አጃይ
ኢብራሂም ከድር – አንተነህ ተስፋዬ – ወ/ይፍራው ጌታሁን – ኃ/ሚካኤል አደፍርስ
እንዳለ ዘውገ – መስዑድ መሐመድ – ታደለ መንገሻ
ናትናኤል ጋንቹላ – ፍፁም ገ/ማርያም – ባኑ ዲያዋራ
ሀዲያ ሆሳዕና (3-5-2 / 3-4-3)
ታሪክ ጌትነት
አዩብ በቃታ – ደስታ ጊቻሞ – ፀጋሰው ዴልሞ
ኢዩኤል ሳሙኤል – አፈወርቅ ኃይሉ – ሱራፌል ጌቻቸው – በኃይሉ ተሻገር – ሄኖክ አርፊጮ
ቢስማርክ አፒያ – ቢስማርክ ኦፖንግ
©ሶከር ኢትዮጵያ