ቅድመ ዳሰሳ | ፋሲል ከነማ ከ ወልዋሎ

በሁለተኛ ቀን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መርሃ ግብር የሚደረገውን የፋሲል ከነማ እና የወልዋሎ ዓ/ዩ ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል። 

በሜዳቸው እጅ የማይሰጡት ፋሲል ከነማዎች ያላቸውን የሜዳቸው ላይ ጥንካሬ ለማስቀጠል እና በዋንጫ ፉክክሩ ለመዝለቅ ነገ ወደ ሜዳ ይገባሉ።

የፋሲል ከነማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አቻ አሸነፈ ተሸነፈ አሸነፈ አቻ

በአሰልጣኝ ሥዩም ከበደ የሚመራው ፋሲል በተመሳሳይ የጨዋታ አቀራረብ ጨዋታዎችን ማድረግ ቀጥሏል። በተለይ ቡድኑ ኳስን ከፍጥነት ጋር በአላማ በመቀባበል የተጋጣሚን የግብ ክልል ለመጎብኘት እና የግብ እድሎችን ለመፍጠር ይጥራል። በነገውም ጨዋታ ቡድኑ የሜዳ ላይ ጥቅሞቹን በማስከበር ኳስን በቁጥጥሩ ለማድረግ እንደሚሞክር ይገመታል። በተለይ በመሃል ሜዳ ላይ የሚሰለፉት ሲራፌል እና በዛብህ ኳሶችን በፍጥነት በማስጀመር የተጋባዦቹን ጊዜ ከባድ ሊያደርጉ ይችለሉ።

በሙጂብ (በይበልጥ)፣ ሽመክት እና ማውሊ ጎሎች ተንጠልጥሎ ጨዋታዎችን እያሸነፈ የሚገኘው ቡድኑ ያለው የቡድኑ የግብ ማስቆጠር ተሳትፎ እጅግ የወረደ ሆኗል። በተለይ ተጋጣሚ ቡድን እነዚህን ሶስት አደገኛ ተጨዋቾች በመያዝ ጨዋታውን ሲያከናውን ቡድኑ ሌሎች የማሸነፊያ መፍትሄዎች በሌሎች ተጨዋቾቹ ማምጣት ይሳነዋል። ይህንን ተከትሎ ነገ ወልዋሎዎች ከሌሎቹ የፋሲል ከነማ ተጨዋቾች በተለየ ለሶስቱ ተጨዋቾች ትኩረት በመስጠት ጨዋታቸውን እንደሚያከናውኑ ይገመታል።

ፋሲሎች አብዱረህማን ሙባረክ፣ ሃብታሙ ተከስተ እና ኦሲ ማውሊን በጉዳት ምክንያት በነገው ጨዋታ አያገኙም። ቡድኑ ከሶስቱ ተጨዋቾች በተጨማሪ በግል ጉዳይ አዲስ አበባ የሚገኘውን ጅብሪል አህመድ ከስብስባቸው ውጪ አድርገዋል።

የወልዋሎ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
ተሸነፈ አቻ ተሸነፈ ተሸነፈ አሸነፈ

በሊጉ በወጥነት ጥሩ ብቃት ማሳየት ተስኗቸው ተከታታይ ነጥቦች ጥለው ደረጃቸው ያሽቆለቆለው ወልዋሎዎች ከአስከፊው ግስጋሴ ለመውጣት ወደዚህ ጨዋታ ይቀርባሉ።
በርካታ ወሳኝ ተጫዋቾች ጨምሮ ዋና  አሰልጣኛቸውም በቅጣት ያጡት ቢጫ ለባሾቹ በነገው ጨዋታ ከወትሮው በተለየ ጠጣር አቀራረብ  ይዘው ይቀርባሉ ተብሎ ይገመታል።

ቡድኑ በሜዳው በርካታ ግቦችን አስቆጥሮ የሚያሸንፈው ፋሲልን እንደ መግጠሙ በመከላከል ላይ ትኩረት አድርጎ ይገባል ተብሎ ቢጠበቅም ውጤታማው የመልሶ ማጥቃት ጥምረቱ መልሶ የሚያገኝ ከሆነ ለተጋጣሚ ተከላካይ ክፍል ፈተና የሚሆንበት ዕድልም የሰፋ ነው።

በዚህም ቡድኑ በነገው ጨዋታ ጠጣር እና በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት የሚሞክር ቡድን ይዞ ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል። ዋና አሰልጣኛቸው በቅጣት ያጡት ወልዋሎዎች በነገው ጨዋታ በምክትሎቹ አብርሃ ተዓረ እና በኮማንደር ኪዳነ ሀፍቱ እየተመሩ ይገባሉ።

ወልዋሎዎች ዓብዱልዓዚዝ ኬታ ፣ አይናለም ሀይሌ ፣ ፍቃዱ ደነቀ እና ካርሎስ ዳምጠው በጉዳት አያሰልፉም።

እርስ በርስ ግንኙነት

በሊጉ እስካሁን አራት ጊዜ ተገናኝተው ፋሲል ከነማ ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ በሁለቱ አቻ ተለለያይተው ወልዋሎ ምንም አላሸነፈም።

ግምታዊ አሰላለፍ 

ፋሲል ከነማ (4-3-3)

ሚኬል ሳማኬ 

ሰይድ ሀሰን – ያሬድ ባዬ – ከድር ኩሊባሊ – አምሳሉ ጥላሁን

በዛብህ መለዮ – መጣባቸው ሙሉ – ሱራፌል ዳኛቸው

ኢዙ አዙካ – ሙጂብ ቃሲም – ሽመክት ጉግሳ

ወልዋሎ (4-2-3-1)

ጃፋር ደሊል

ምስጋናው ወልደዮሐንስ – አሞስ አቼምፖንግ – ዳዊት ወርቁ – ሄኖክ መርሹ

ሚካኤል ለማ – ሳሙኤል ዮሐንስ

ብሩክ ሰሙ – ራምኬል ሎክ – ኢታሙና ኬይሙኔ

ጁንያስ ናንጂቡ

©ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ