የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ስምንተኛ ሳምንት 16 ጨዋታዎች ቅዳሜ እና እሁድ ተካሂደዋል። ቀሪዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ ነገ እና ከነገ በስቲያ ይደረጋሉ። የሳምንቱን ውሎም እንዲህ ተመልክተነዋል።
ምድብ ሀ
(በአምሀ ተስፋዬ)
ቅዳሜ ዕለት ቢሾፍቱ ላይ በተደረገ ብቸኛ ጨዋታ ገላን ከተማን የገጠመው ወሎ ኮምቦልቻ 1-0 በማሸነፍ በጥሩ ግስጋሴው ቀጥሎበታል። በመጨረሻው ደቂቃ ሀብታሙ ደሙ ያስቆጠራት ጎል ኮምቦልቻ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው ለገጣፎ ለገዳዲን እግር በእግር እንዲከተል አስችሎታል።
ለገጣፎ ላይ የምድቡ መሪ ለገጣፎ ለገዳዲ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ያደረጉት ጨዋታ በባለሜዳው 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። በ59ኛው ደቂቃ ዳዊት ቀለመወርቅ ለገጣፎን ቀዳሚ ሲያደርግ ኤሌክትሪክ ከ76ኛው ደቂቃ የአቻነት ግብ አስቆጥረው የነበረ ቢሆንም የጨዋታው ፊሽካ በሚጠበቅበት ወቅት ዘካርያስ ከበደ ጣፎዎችን ጮቤ ያስረገጠች የማሸነፍያ ጎል አስቆጥሯል።
አክሱም ከተማ በሜዳው አቃቂ ቃሊቲን አስተናግዶ 2-0 አሸንፏል። ሠላማዊ ገብረሥላሴ በ13ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ግብ በመምራት ጨዋታውን ያጋመሱት አክሱሞች በ58ኛው ደቂቃ ዘካርያስ ፍቅሬ ተጨማሪ ግብ አሸንፈው ወጥቸዋል።
ደብረ ብርሃን ላይ ሰሜን ሸዋ ደብረ ብርሃን ከፌዴራል ፖሊስ ያደረጉት ጨዋታ በባለሜዳው 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ለደብረብርሃን ሙሉቀን ወንድሙ በ10ኛው ደቂቃ ነው ያስቆጠረው።
ወልዲያ ላይ ወልዲያ ከደደቢት በ1 አቻ ውጤት ተለያይተዋል። ደደቢቶች በ55ኛው ደቂቃ መድሃኔ ታደሰ ባስቆጠረው ጎል እንግዶቹ መሪ ቢሆኑም አንዱዓለም ንጉሴ 75ኛው ደቂቃ የአቻነቱን ግብ አስቆጥሯል።
ደሴ ከተማ ከ ሶሎዳ ዓድዋ ያደረጉት ጨዋታ ያለ ግብ ተጠናቋል።
ምድብ ለ
(በአምሀ ተስፋዬ)
ዱራሜ ላይ ሀምበሪቾ በሜዳው ጋሞ ጨንቻን አስተናግዶ 3-0 አሸንፏል። ሀምበሪቾዎች ቢንያም ጌታቸው በ38ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ጎል እየመሩ ወደ እረፍት ሲያመሩ ቢንያም ጌታቸው በ70ኛው ደቂቃ በድጋሚ እንዲሁም በ76ኛው ደቂቃ ቴዲ ታደሰ ግብ አክለውበት በሀምበሪቾ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ቦንጋ ላይ ካፋ ቡና ከ ጅማ አባ ቡና ያደረጉትን ጨዋታ ባለሜዳው 3-0 አሸንፏል። ከጨዋታው በፊት የቦንጋ ዩንቨርስቲ ለከፋ ቡና ስፖርት ቡድን ሙሉ የትጥቅ ድጋፍ ያደረገ ሲሆን የስፖርቱ ልማት ዋና ኃላፊ አቶ ሽፈራው ገብረፃዲቅ ምስጋናቸውን አስተላልፈውል። በ19ኛው ደቂቃ ታሪኩ ጎጀሌ ባስቆጠረው ግብ ወደ እረፍት ያመሩት ሁለቱ ቡድኖች ከእረፍት መልስ በመጀመሪው ደቂቃ ፍፁም ጥላሁን እንዲሁም በ59ኛው ደቂቃ አድናን ረሽድ ባስቆጠሯቸው ግቦች 3-0 ተጠናቋል።
ሻሸመኔ ከተማ በሜዳው ኢኮስኮን ገጥሞ 2-1 አሸንፏል። ከማል አቶም እና ሙሉቀን ተሾመ የሻሼን ጎሎች ሲያስቆጥሩ ለኢኮሥኮ ብቸኛውን ግብ አሚር ሙደሲር አስቆጥሯል።
ሶዶ ላይ ወላይታ ሶዶ ከ ሀላባ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ በወላይታ ሶዶ 1-0 በሆነ አሸናፊነት ተጠናቋል። የምድቡ ቀሪ ጨዋታዎች ነገ እነመ ከነገ በስቲያ ሲቀጥሉ ነገ አዲስ አበባ ከተማ ከ ነቀምቴ ከተማ፤ ረቡዕ ቤንች ማጂ ቡና ከ መከላከያ የሚጫወቱ ይሆናል።
ምድብ ሐ
(በፋሪስ ንጉሴ)
አርባምንጭ ከተማ በሜዳው ደቡብ ፖሊስን አስተናግዶ 3-0 አሸንፏል። ከወትሮው ቁጥሩ አነስተኛ ተመልካች የተገኘበት ጨዋታ ፈጣን እንቅስቃሴ እና ጥሩ የኳስ ቅብብል የታየበት ነበር። በተለይ እንግዳዎቹ ኳስ ተቆጣጥረው ለመጨዋት የሞከሩበት መንገድ መልካም የሚባል ነበር። በዚህ ጨዋታ ላይ ከእንቅስቃሴ ባሻገር የጎል ሙከራዎች ግን ብዙም አልታየባቸውም።
ገና ጨዋታው በጀመረ 2ኛ ደቂቃ ላይ የደቡብ ፖሊሱ ያሬድ መሀመድ ቅጣት ምት በአርባምንጩ ግብ ጠባቂ በይሳቅ ተገኝ የተመለሰበት የጨዋታው ፈጣን ሙከራ ነበረች። 27ኛ ደቂቃ ላይ ለባለሜዳዎቹ አርባምንጮች ምንተስኖት አበራ ከረጅም ርቀት መቶ ወደ ውጭ የወጣበት ሙከራ ደግሞ በባለሜዳዎቹ በኩል የሚጠቀስ ነበር። በጨዋታው ደቡብ ፖሊሶች በተጋጣሚያቸው ላይ የኳስ ቁጥጥር ለመውሰድ የሞከሩ ቢሆንም በቀላሉ ይባልሽባቸው ነበር።
ከአርባምንጭ ከተማዎች በቀላሉ ግብ ለማስቆጠር ሲቸገሩ ቆይተው 29ኛው ደቂቃ ላይ እሱባለው ፍቅሬ በረጅሙ ያሻማውን ኳስ ማርቲን ኡቼ ለኤደም በግንባሩ አመቻችቶለት ኤደም በጥሩ አጨራረስ ባለሜዳዎቹን መሪ አድርጓል። ከዚህ ግብ መቆጠር በኋላ እንግዳዎቹ ተጭነው ግብ ለማስቆጠር ሲሞክሩ በቀላሉ ሲከሽፍባቸው ነበር። ለእንግዳዎቹ ደቡብ ፖሊሶች ጌታሁን አየለና የኋላሸት ሰለሞን በተደጋጋሚ የባለሜዳዎቹን የግብ ክልል ሲፈትኑ ቢቆዩም ግብ ማስቆጠር ግን አልቻሉም። የመጀመርያው አጋማሽም በአርባምንጭ ከነማ 1ለ0 መሪነት ተጠናቋል።
ሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱንም ክለቦች ከፈጣን እንቅስቃሴ የገታና በረጅም ኳሶች ጨዋታውን አሰልቺ የነበረ ሲሆን አልፎ አልፎ በሁለቱም ክለብ አጥቂዎች ኢላማቸውን ያልጠበቁ ሙከራዎች ተደርገዋል። ባለሜዳዎቹ አንደ ሁልጊዜው ከተጠባባቂ ወንበር በሚነሱ ተጫዋቾች የጨዋታውን እንቅስቃሴ ቀይረውታል። በተለይ አቦነህ ገነቱና ፍቃዱ መኮንን ተቀይረው ወደሜዳ ከገቡ በኋላ የማጥቃት ሃይላቸውን ጨምረው በተጋጣሚያቸው ላይ ጫና መፍጠር ችለዋል። የጨዋታው የመጨረሻ 10 ደቂቃዎች ላይም የደቡብ ፖሊስ ተከላካዮችን በማዳከም ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር ችለዋል።
80ኛ ደቂቃ ላይ ከመሃል የተሻገረለትን ኳስ ፍቃዱ የግል ጥረቱ ተጠቅሞ ሁለተኛውን ጎል አስቆጥሯል። በድጋሚ የእንግዳውን ቡድን መቀዛዝ ተመልክተው ጫና በማድረጋቸው
85ኛ ደቂቃ ላይ አቦነህ በግሩም ሁኔታ በአንድ ሁለት ቅብብል ለእሱባለው ፍቅሬ አቀብሎ እሱባለው የጨዋታውን ማሳረጊያ ጎል አስቆጥሯል። በ87ኛ ደቂቃ ለይ ከመሀል የተሻገረውን አብነት ተሾመ የደቡብ ፖሊስ ተጫዋቾችን ቀድሞ አገባ ተብሎ ሲጠበቅ በግብ ጠባቂው የተመለሰበትም አስቆጪ ሙከራ ነበር። የስምንተኛ ሳምንት መርሃግብርም በዚህ መልኩ በአርባምንጭ ከተማ 3ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ቡታጅራ በሜዳው ነገሌ አርሲን 3-1 አሸንፎ በመሪነቱ ቀጥሏል። ተከታታይ አምስተኛ ድሉን ላስመዘገው የአሰልጣኝ አሥራት አባተ ቡድን ሦስቱም አጥቂዎች ግብ ያስቆጠሩ ሲሆን ድንቅነህ ከበደ፣ አብዱልከሪም ቃሲም እና በላይ ገዛኸኝ የግቦቹን ባለቤቶች ናቸው። አርሲዎች ከሽንፈት ያልዳኑበትን ግብ ደግሞ ፍቅሩ ጴጥሮስ አስቆጥሯል።
ኦሜድላ ሜዳ ላይ ወራቤን የገጠመው ኮልፌ ቀራኒዮ 3-0 አሸንፏል። ብሩክ ሙልጌታ፣ አዳነ አየለ እና አኖር ብላ ጎሎቹን ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው።
መድን ሜዳ ላይ ኢትዮጵያ መድን ከ ባቱ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል። ባቱ ከተማ በ68ኛው ደቂቃ ቡስሪ ማሐመድ አስቆጥሮ ረጅም ደቂቃ መምራት ቢችሉም የጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ መድኖች በ89ኛው ደቂቃ አህመድኑር ናስር ባስቆጠረው ጎል አቻ ወጥተዋል።
ኦሜድላ ሜዳ ላይ ቂርቆስን ከ ጌዲኦ ዲላ ያገናኘው ጨዋታ 1-1 ሲጠናቀቅ የካ ከ ሺንሺቾ ያለምንም ግብ ተጠናቋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ