“አሁን ሁላችንም የምናልመው ቅዱስ ጊዮርጊስ የለመደውን ዋንጫ ወደ ቤቱ ማምጣት ነው”
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ታሪክ በርካታ ጎል ካስቆጠሩ ተጫዋቾች አንዱ የሆነው ጌታነህ ከበደ ለዓመታት ከነገሰበት ደደቢት ለቆ ፈረሰኞቹን ሲቀላቀል ብዙዎች ደጋፊዎች ተስፋ አድርገውበት ነበር። ሆኖም የታሰበውን ያህል አገልግሎት ባለመስጠቱ ብዙዎች ግራ ተጋብተው ቆይተዋል። በዘንድሮ የውድድር ዓመት በተለይ ከስድስተኛው ሳምንት በኋላ ባሉት ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን በማመቻቸት እና ጎል በማስቆጠር ቡድኑ ለሁለት ዓመታት ከራቀው ዋንጫ ጋር ለማስታረቅ በሚያደርገው ጥረት የአንበሳውን ድርሻ እየወሰደ ይገኛል። ትናንት በአዲስ አበባ ስታዲየም ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲዳማ ቡናን ላይ የዓመቱን ከፍተኛ የጎል መጠን አስቆጥሮ የሊጉ አናት ላይ ሲቀመጥ ሁለት ጎሎችን በማስቆጠር ወደ አስፈሪነቱ መመለሱን እየጠቆመ ይገኛል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላም በወቅታዊ አቋሙ ዙርያ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።
በጉዳት ምክንያት የታሰበውን ያህል አገልግሎት አለመስጠትህ ስለ ፈጠረብህ ነገር እንድትነግረኝ በማድረግ ጥያቄዬን ልጀምር?
በየትኛውም ጊዜ የጉዳቱ መጠን ከባድም ይሁን ቀላል ተጫዋች ጉዳት ሲያስተናግድ አስጨናቂ ጊዜ ነው የሚያሳለፍው። ምክንያቱም የአቋም መውረድ ይመጣል፣ የሰውነት ክብደት ሊጨምር ይችላል። ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ይከሰታሉ። የእኔ ደግሞ ትንሽ ከበድ ያለ ጉዳት ነበር ያስተናገድኩት። በዚህም ምክንያት ደጋፊው ከእኔ ይፈልግ የነበረውን ነገር ባለማድረጌ ምክንያት ለአንድ ዓመት አስቸጋሪ ጊዜ ነው ያሳለፍኩት። ከጉዳቴ አገግሜ ወደ ሜዳ ከተመለስኩ በኋላ በድጋሚ ጉዳት አጋጥሞኝ ነበር። ጉዳት ሲደጋገምህ ደግሞ በጣም ነው የምትረበሸው። ለማንኛውም በጣም አስቸጋሪ ጊዜ ነው ያሳለፍኩት።
አሁን ፈረሰኞቹ ከአንተ የሚጠብቁት ትክክለኛ መንገድ ላይ ትገኛለህ። ልምድህን ተጠቅመህ ቡድኑን በከፍተኛ ሁኔታ እያነሳሳህ ትመራለህ፣ ለጎል የሚሆኑ እድሎችን ከየትኛውም አቅጣጫ ትፈጥራለህ፣ አመቻችተህ ታቀብላለህ ጎልም እያስቆጠርክ ትገኛለህ። እስቲ አሁን ስላለው ወቅታዊ አቋምህ ንገረን ?
አሁን የእኔ ወቅታዊ አቋም ጥሩ መሆን ብቻ ሳይሆን እንደ ቡድን ተጫዋቾቹ በጠቅላላ ጥሩ አቋም ላይ ነው የሚገኙት። አስቀድመው ሜዳ ላይ የገቡትም ቢሆን ተቀይረው የሚገቡት ተጫዋቾች በቡድኑ ውስጥ ልዩነት መፍጠር የምንችልበት ጊዜ ላይ ይገኛሉ። አሁን ሁላችንም የምናልመው ቅዱስ ጊዮርጊስ የለመደውን ዋንጫ ወደ ቤቱ ማምጣት ነው። ለዚህም ጠንክረን እየሰራን ነው። በግሌም የጉዳት ነገር ከዚህ በኃላ የሚያሳስበኝ ባለመሆኑ በዚህ አቋሜ እቀጥላለው።
አሁን ቅዱስ ጊዮርጊስ የሊጉ አናት ላይ በመቀመጥ መሪ መሆን ጀምሯል። ከሁለት ዓመት ከራቀበት የሊጉ ዋንጫ ጋር ታስታርቁት ይሆን?
ቅዱስ ጊዮርጊስ በታሪኩ ሁለት ተከታታይ ዓመት ዋንጫ ሳያነሳ ያለፈበት ጊዜ አልነበረም። ይህን ሦስተኛ ዓመት ማለፍ እንደሌለበት የክለቡ የበላይ አመራሮች በጣም አስጠንቅቀውናል። ያለንን ነገር ለመስጠት አቅሙ እንዳለን ነግረውናል። ስብስባችንም ዋንጫ ለማንሳት በቂ ነው ማለት ይቻላል። መጀመርያ አካባቢ መጣል የሌለብንን ነጥቦች ጥለናል። ይህም ቡድናችን እስኪዋሀድ ድረስ የነበሩ ፈተናዎች ነበሩ። አሁን በጥሩ መነሳሳት፣ በጥሩ አቋም ላይ እንገኛለን።
ደደቢት ቤት የነበረው ጥምረት ፈረሰኞቹ ቤት ተደገመ ልበል?
(ፈገግ እያለ) አዎ! ከደደቢት እዚህ ቤት በዝተናል ማለት ይቻላል። ወደ አምስት ስድስት ደርሰናል። ደስታ ደሙ፣ ያብስራ ተስፋዬ፣ አቤል ያለው እና ትንሽ ጉዳት ቢኖርበትም ወደ ትክክለኛ አቋሙ ሲመጣ አቤል እንዳለ ጥንካሪያችንን የበለጠ ይጨምራል። አሁን ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት ያለው አየር ተመችቶናል። ገና ብዙ ነው የምናስበው።
በተለይ ከአቤል ያለው ጋር ያላቹ ጥምረት እንዴት ይገለፃል?
ከአቤል ጋር ደደቢት እያለንም እንዲሁ አሁን እንደምታዩት በተመሳሳይ ጥሩ ጥምረት ነበረን። ያው እኔ እና አቤል ሳንተያይ ነበር ኳስ የምንሰጣጣው። አሁንም ይሄንኑ ነው እየደገምን ያለነው።
© ሶከር ኢትዮጵያ