ሪፖርት | ፍፁም ገብረማርያም ለሰበታ ወሳኝ ሦስት ነጥብ አስገኝቷል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 12ኛ ሳምንት ሁለተኛ የጨዋታ ቀን አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኘው ሀዲያ ሆሳዕናን ያስተናገደው ሰበታ ከተማ ተቸግሮም ቢሆን ሙሉ ሦስት ነጥብ ማሳካት ችሏል።

ባለሜዳዎቹ ሰበታ ከተማ ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት በድሬዳዋ ከተረታው ስብስብ የሶስት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል። በዚህም መሠረት አንተነህ ተስፋዬ፣ ደሳለኝ ደባሽ እና ጌቱ ኃይለማርያም ወደ መጀመርያ አሰላለፍ መካተት ሲችሊ በአንፃሩ በሆሳናዎች በኩል በወልቂጤ በሜዳው ከተረታው ስብስብ ውስጥ ሁለት ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ሱራፌል ዳንኤልና ሱራፌል ጌታቸውን በመጠቀም ነበር የዛሬውን ጨዋታ ማድረግ የቻሉት።

 ከግቦች መቆጠር በዘለለ ይህ ነው የሚባል ሳቢ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን ባላስመለከትን የመጀመሪያ አጋማሽ ሰበታ ከተማዎች ኳስን ተቆጣጥረው ለማጥቃት የሚያደርጉት ጥረት እንዲሁም የሀዲያ ሆሳዕናዎች መልሶ ማጥቃት ብዙም ውጤታማ ያልነበረበት አጋማሽ ነበር።

በመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃ የተሻሉ የነበሩት ሰበታ ከተማዎች ገና በ4ኛው ደቂቃ ነበር ፍፁም ገ/ማርያም ከሳጥን ውጭ ባደረጋት ሙከራ ነበር ጫና መፍጠራቸውን የጀመሩት። ጫናቸውም ፍሬ አፍርቶ በ7ኛ ደቂቃ የሚገባቸውን ግብ አግኝተዋል። ታደለ መንገሻ ወደ ያሻማውን ኳስ የሆሳዕና ተከላካዮች ሸርፈው ለማውጣት ባደረጉት ጥረት በቅርብ ርቀት የነበረው ባኑ ዲያዋራ በግንባሩ በመግጨት ቡድኑን መሪ ያደረገች ግብ አስቆጥሯል።

በጨዋታው እንደ ወትሮው ሁሉ ምንም እንኳን በተለዋጭ ሜዳ ቢሆንም ባለሜዳዎቹ ሰበታ ከተማዎች በተጓዥ የሀዲያ ሆሳዕና ደጋፊዎች የደመቀ ድጋፍ ከሜዳቸው ውጭ የሚጫወቱ እንዲመስላቸው ተገደዋል።

በዛሬው ጨዋታ የመከላከል መስመራቸው ላይ በርካታ ለውጦችን ያደረጉት ሰበታዎች በመሀል ተከላካይ ስፍራ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ከረጅሞ ጊዜ ጉዳት የተመለሰውን አንተነህ ተስፋዬን ከደሳለኝ ደባሽ ጋር ሲያጣምሩ በተመሳሳይ የቀኝ መስመር ተከላካዮን ጌቱ ሀ/ማርያምን ከሳምንታት በኃላ በተከላካይ መስመራቸው ላይ መጠቀም ችለዋል።

በመልሶ ማጥቃት አቅዳቸው ይህ ነው የሚባል የጎል እድል መፍጠር ያልቻሉት ሆሳዕናዎች በ32ኛው ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት ጎል አግኝተዋል። ከቀኝ መስመር ፍጥነቱን ተጠቅሞ ተጫዋቾችን እየቀነሰ የገባው ቢስማርክ አፒያ በግሩም አጨራረስ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል።

በ41ኛው ደቂቃ ኢብራሂም ከድር ከናትናኤል ጋንቹላ የደረሰውን ኳስ ከተቆጣጠረ በኃላ ከረጅም ርቀት አክርሮ የመታው ኳስ የግቡን ቋሚ ለትማ ልትመለስ ትችላለች።

ከእረፍት መልስ ሀዲያ ሆሳዕናዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ በይበልጥ ጥንቃቄን ጨምረው በሁለት በቅርብ የሚጫወቱ የመከላከል መስመሮችን በመዘርጋት በመከላከል ላይ ትኩረት አድርገው ቢጫወቱም በባለሜዳዎቹ በኩል ይህን የሚመጥን በሜዳው ስፋት በመጠቀም የሚደረግ የማጥቃት እንቅስቃሴ እምብዛም አልተመለከትንም። ይልቁን በመከላሉ ላይ ያተኩሩ እንጂ በመልሶ ማጥቃት የተከፋፈተውን የሰበታ የተከላካይ ክፍል በመፈተሽ ረገድ ሆሳዕናዎች የተሻሉ ነበሩ።

በሆሳዕናዎች በኩል በ51ኛው ደቂቃ ቢስማርክ አፒያ ያሳለፈትን የመልሶ ማጥቃት የተገኘ ኳስ ቢስማርክ አፖንግ የሞከረውና ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣበት እንዲሁም በ68ኛው ደቂቃ አፈወርቅ ሀይሉ ከተከላካዮች ጀርባ ያሳለፈለትን ግሩም ኳስ ቢስማርክ አፒያ ሳይጠቀምበት የቀረው ተጠቃሽ የግብ አጋጣሚዎች ነበሩ። በተመሳሳይ አፈወርቅ በመልሶ ማጥቃት የተገኘችውን ግሩም አጋጣሚ ወደ ግብ ሞክሮ ዳንኤል አጄ የያዘበት ኳስ ሌላው በሆሳዕናዎች በኩል የባከነ አጋጣሚ ነበር።

ነገርግን ሳይጠበቅ በ81ኛው ደቂቃ ላይ ባኑ ዲያዋራ ከግራ መስመር አንድ ተጫዋች አልፎ ያሳለፈለትን ኳስ ተጠቅሞ ፍፁም ገ/ማርያም አስቆጥሮ ቡድኑን ዳግም መሪ ማድረግ ችሏል።

በቀሩት ደቂቃዎች ሆሳዕናዎች የአቻነት ግብ ለማግኘት ያደረጉት ጥረት ውጤታማ መሆን ሳይችል ጨዋታው በሰበታዎች የ2ለ1 አሸናፊነት ሊጠናቀቅ ችሏል።

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ