ሪፖርት | የሙጅብ ቃሲም ብቸኛ ግብ ፋሲልን ባለድል አድርጓል

በ12ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጎንደር ላይ ፋሲል ከነማ በሜዳው ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲን አስተናግዶ 1-0 በሆነ ጠባብ ውጤት አሸንፏል።

ፋሲል ከነማ ከጅማ አባ ጅፋር ጋር 0-0 የተለያየው ስብስብ ላይ ምንም ዓይነት ለውጥ ሳያደርግ ወደ ሜዳ የገባ ሲሆን ወልዋሎም በተመሳሳይ በሲዳማ ቡና የተሸነፈውን ስብስብ ይዞ ቀርቧል። በጨዋታው መጀመሪያ ላይ የፋሲል ከነማ የቀድሞ ተጫዋች ለሆነው ራምኬል ሎክ የራሱን ምስል የያዘ የፎቶ ፍሬም ስጦታ ተበርክቶለታል።

ተመጣጣኝ በነበረው በሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ ጨዋታ ፋሲል ከነማዎች የወልዋሎ ዓዲግራት ዮኒቨርስቲን የተከላካይ መስመር ሰብረው መግባት ሲከብዳቸው ተስተውሏል። 3ኛው ደቂቃ ላይ ሽመክት ጉግሳ በግራ በኩል ይዞት የገባውን ኳስ ለሙጅብ ቃሲም በሚያሸግርበት ወቅት ግብ ጠባቂው ያዳነበት ሲሆን 24ኛው ደቂቃ ላይ ግን ሽመክት ጉግሳ ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ሙጅብ ቃሲም ወደግብነት ቀይሮ ፋሲል ከነማን መሪ መድረግ ችሏል።

በሁለቱ ተጫዋቾች ጥምረት በተደረገ ሌላ ሙከራ 31ኛው ደቂቃ ላይ ሽመክት ጉግሳ በድጋሚ በቀኝ መስመር ወደ ሳጥን ጠርዝ ይዞት የተጠጋውን ኳስ ለሙጅብ ቃሲም ለማሻገር ሲሞክር በተከላካዮች ተጨርፎ ወጥቶበታል። ግብ ካገኙ በኋላ የተሻለ ለመንቀሳቀስ የሞከሩት አፄዎቹ በመጀመሪያው አጋማሽ ተጨማሪ  ግብ ማግኘት አልቻሉም ነበር።
በእንግዳዎቹ በኩል በተመሳሳይ የፋሲል ሳጥን ውስጥ መግባት ተስኗቸው የተሞከሩት አጋጣሚዎች በሙሉ ከሳጥን ውጪ የተደረጉ ነበር። በ2ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተሻገረ ኳስ ራምኬል ሎክ በጭንቅላት በመግጨት ኢላማውን ያልጠበቀ ሙከራ መድረግ ችሎ ነበር። ከደቂቃዎች በኋላ ከሳጥን ውጪ ጁኒያስ ናዲጂቦ ወደ ግብ አክርሮ የመታው ኳስም የርቀት ሙከራ ነበር። 9ኛው ደቂቃ ላይም ኢታሙና ማብሮዲጅኖ ተመሳሳይ ኳስ ከሳጥን ውጪ ወደግብ አክርሮ መትቶ ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል። በመጀመሪያው አጋማሽ መገባደጃ ደቂቃዎች ላይ ከምስጋና ወልደዮሐንስ የተሻገረለትን ኳስ ኢታሙና ወደ ግብነት ለመቀየር ያደረገውም ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።

በሁለተኛው አጋማሽ ወልዋሎዎች የተሻለ መንቀሳቀስ ቢችሉም ደጋግመው ወደ ሳጥን መግባት ላይ ተዳክመው ታይተዋል። ረጃጅም ኳሶችን የሚጫወቱት ዕንግዶቹ የሚያሸግሯቸው ኳሶች በያሬድ ባየህ እና በከድር ኩሊባሊ ሲጨናገፉ ተስተውሏል። ከመስመር እየተነሳ ኳሶችን ከርቀት ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርግ የነበረው ራምኬል ሎክ 48ኛው እና 67ኛው ደቂቃ ላይ ሁለት ሙከራዎችን ማድረግ የቻለ ሲሆን የመጀመሪያው ከቅጣት ምት የተገኘን ኳስ በቀጥታ ወደግብ እክርሮ መትቶ ግብ ጠባቂው አድኖበታል። በሁለተኛው ሙከራ ደግሞ ከሳጥን ጠርዝ በመስመር ይዞ የገባውን ኳስ በቀጥታ ሞክሮ ወደ ውጪ ወጥቶበታል።

በባለሜዳዎቹ በኩል ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ከመጀመሪያው ባነሰ መልኩ የተንቀሳቀሱ ሲሆን በሙከራ ደረጃ ከተጋጣሚያቸው ውልዋሎ ተሽለው ታይተዋል። ሆኖም ከጨዋታ ጨዋታ በሜዳቸው ግብ ማስቆጠር እየተቸገሩ የመጡት አፄዎቹ አልፎ አልፎ ወደ ግብ በሚደርሱበት ሰዓት የሚያገኟቸውን አጋጣሚዎች መጠቀም ሲቸገሩ ተስተውሏል። 46ኛው ደቂቃ ላይ ከተደረገ የረጅም ርቀት ሙከራ በኋላ 69ኛው ደቂቃ ላይ በግራ መስመር በዛብህ መለዮ ያቀበለውን ኳስ ኢዙ አዙካ ወደ ግብ አክርሮ የመታውን ኳስ ግብ ጠበቂ አድኖበታል። እዚሁ ሰዓት ላይ የተገኘውን የማዕዘን ምት ሰለሞን ሀብቴ አሻምቶት በተከላካዮች ተገጭቶ ሲመለስ በዛብህ መለዮ ያሻገረለትን ያሬድ ባየህ በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ በግብ ጠባቂው ተመልሶበታል። ጨዋታውም በባለሜዳዎቹ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ወጤቱን ተከትሎ ፋሲሎች ከመቐለ 70 እንደርታ በግብ ክፍያ በልጠው 22 ነጥቦች ሁለተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ በአንፃሩ ወልዋሎ ዓዲግራት ዮኒቨርስቲ በ15 ነጥብ 12ተኛ  ደረጃ ላይ ተቀምጧል ።

ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ ቋራ ከሚባለው የፋሲለደስ ስታድየም አካባቢ የተወሰኑ ደጋፊዎች በአሰልጣኝ ሥዩም ከበደ እና በክለቡ አጨዋወት ደስተኛ እንዳልሆኑ የሚገልፅ ተቃውሞ ሲያሰሙ ተስተውሏል።

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ