የአሰልጣኞች አስተያየት | ሰበታ ከተማ 2-1 ሀዲያ ሆሳዕና 

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 12ኛ ሳምንት ሰበታ ከተማ ሀዲያ ሆሳዕናን 2-1 ከረታበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ውበቱ አባተ አስተያየት ሲሰጡ በሀዲያ ሆሳዕና በኩል ሳይሰጡ ቀርተዋል።


” አንዳንዴ ጨዋታዎች ባሰብከው መንገድ ላይሄዱ ይችላሉ፤ ያም ቢሆን ግን ውጤቱን ይዘን መውጣታችን ጥሩ ነገር ነው”- ውበቱ አባተ /ሰበታ ከተማ/

ስለ ጨዋታው

“ተከታታይ ጨዋታ ሽንፈት በማስተናገዳቸውና ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት እንደመጫወታቸው ጨዋታውን ከባድ አድርጎብናል። በተጨማሪም የጨዋታዎች መደራረብ ልጆቻችን ላይ ድካም ፈጥሯል። በእኛ በኩል በርካታ ልጆች በጉዳት አልነበሩም በተለይ መሀል ተከላካይ ስፍራ ላይ መሳሳቶች ነበሩ። ውጤት ያስፈልገን ስለነበር ከዚህ አንፃር ውጤቱን መያዛችን ትልቅ ነገር ነው። አንዳንዴ ጨዋታዎች ባሰብከው መንገድ ላይሄዱ ይችላሉ፤ ያም ቢሆን ግን ውጤቱን ይዘን መውጣታችን ጥሩ ነገር ነው።”

ስለቡድኑ የውድድር ዘመኑ እቅድ

“የደረጃ ሰንጠረዡን ስትመለከተው በታችኛው እና ከአናት በሚገኙ ቡድኖች መካከል ያለው ልዮነት ጠባብ ከመሆነ የተነሳ ውድድሩ ለሁሉም ክፍት ነው። እንደ ቡድን ግን ከእለት ወደ እለት የተሻሻሉ ነገሮች አሉ ፤ እንደቡድን መጫወት በምንፈልገው መንገድ ላይ ወጥነት ቢጎለንም መሻሻሎች አሉ ነገርግን አሁን ላይ ሆኖ ዓመቱ መጨረሻ ላይ የሚሆነውን መተንበይ ቢከብድም መንገዱ በፈቀደልን ልክ በጥሩ ጨዋታ እስከዓመቱ መጨረሻ ለመዝለቅ እናስባለን። እንደአጠቃላይ ግን በዘንድሮው የውድድር አመት ከስጋት የነፃ ቡድን ለመገንባት እየጣርን እንገኛለን። ምን አልባት አሁንም ለምንገኝበት ደረጃ የእኔ ስህተት ነው ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም ሁሌም የምንጫወተው ከሜዳችን ውጭ ቢሆንም ሁልጊዜም አቀራረባችን ለማሸነፍ ነው። ይህም በራሱ በቀላሉ ነጥቦችን እንዳናስመዘግብ እያደረገን ይገኛል። በቀጣይ ይህን ማስተካከል ከቻልን የተሻለ ከስጋት ነፃ የምንሆንበትን እድል መፍጠር እንችላለን። ”

*የሀዲያ ሆሳዕናው አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ ሀሳባቸውን ሳይሰጡ ቀርተዋል።

© ሶከር ኢትዮጵያ