በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 12ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ፈረሰኞቹ የሰንጠረዡን አናት ሲቆናጠጡ መቐለ መሸነፉን ተከትሎ ፋሲል ከምዓም አናብስት በነጥብ መስተካከል ችሏል። ኢትዮጵያ ቡና ወደ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ሲገባ ሀዲያ ሆሳዕና ብቸኛው ባለ አንድ አሀዝ ነጥብ የሰበሰበ ክለብ ሆኖ አሁንም በሊጉ ግርጌ ይገኛል። እኛም በዚህኛው ሳምንት የተከሰቱ ትኩረት የሚሹ ክለብ ነክ ጉዳዮችን በቀጣዩ መልኩ አሰናድተናል።
👉 ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ከፍታው…
በፕሪምየር ሊጉ ያለፉት ጥቂት ሳምንታት ከጨዋታ ጨዋታ እያሳዩት ባለው መሻሻል ረገድ ከፈረሰኞቹ ልቆ የሚቀመጥ ክለብን መፈለግ እጅግ ከባድ ነው። ወትሮውንም በመከላከሉ ረገድ ጠንካራ የሆነው ቡድኑ አሁን ላይ ደግሞ በተለይ በአጥቂዎች ተደጋጋሚ ጉዳት እና በቀደመ የብቃት ደረጃቸው ላይ ያለመገኘት ስልነት ጎድሎት የነበረው የአጥቂ መስመራቸው ያለ ሳልሀዲን ሰዒድ ከፍተኛ መሻሻሎችን እያሳየ ይገኛል።
ቡድኑ በመጨረሻ ካደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች ላይ አስራ አንድ ግቦችን ማስቆጠር ችሏል። ይህም እንደ ጊዮርጊስ ላሉ በመከላከሉ ረገድ ጠንካራ አደረጃጀት ላለው ቡድን መሰል ግቦች መቆጠራቸው ላለፉት ሁለት ዓመታት ያጡትን ዋንጫ ለማስመለስ በሚያደርጉት ጥረት ትልቅ አስተዋፅኦ አለው። ከትላንት በስቲያ ሲዳማ ቡናን ከፍፁም የጨዋታ ብልጫ ጋር 6-2 ያሸነፉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በሸገር ደርቢ ሁለተኛ አጋማሽ በአጨዋወት ረገድ የታየውን መሻሻል እሁዱ ጨዋታ በሁለቱም አጋማሾች መደገም መቻላቸው የአሰልጣኝ ሰርዳን ዝቪጂኖቨ ቡድን የሚገኝበትን ከፍ ያለ ወቅታዊ ብቃትን ማሳያ ነው።
ዋነኛ ችግራቸው የነበረውን ግብ የማስቆጠር ችግርን ተወሰነ መልኩ እየቀረፉ የሚገኙት ጊዮርጊሶች በቀጣይ የጨዋታ ሳምንት ወደ ትግራይ ተጉዘው ከወልዋሎ ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ ከሜዳ ውጭ ከአቻ ያልዘለለውን ደካማ የሜዳ ውጭ ውጤታቸውን የመቀልበስ ኃላፊነትን ተሸክመው የሚያደርጉት ጨዋታ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። ይህም ወቅታዊ ድንቅ አቋማቸው በሜዳቸው ብቻ ነው ወይስ ከሜዳ ውጪ ጨዋታዎች ላይም ይቀጥላል ለሚለው ጥያቄ የመጀመርያ መልስ የሚሰጥበት ይሆናል።
👉 ራሱን የገለፀው ፈጣኑ አዳማ ከተማ
በ12ኛው ሳምንት በሜዳው ኢትዮጵያ ቡናን ያስተናገደው አዳማ ከተማ 3-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ደጋፊዎቹን አስፈንጥዟል። አሰልጣኝ አሸናፊ ከሚታወቁበት ጥንቃቄ መር አጨዋወት በተወሰነ መልኩ ተላቀው ለተጫዋቾች የተሻለ የማጥቃት ነፃነት ሰጥተው በተመለከትንበት በዚሁ ጨዋታ የተከላካይ አማካዮችን ቁጥር ቀንሶ የተሻለ የማጥቃት ባህሪን የተላበሱ አማካዮችን ከፈጣኖቹ አጥቂዎች ጀርባ መጠቀም የቻለው ቡድኑ በእሁዱ ጨዋታ ምርጥ የሚባል እንቅስቃሴን ማሳየት ችሏል።
በመጀመሪያው አጋማሽ ኢትዮጵያ ቡናዎች ኳስን እንዳይመሰርቱ ከፍተኛ ጫና በሜዳው የላይኛ ክፍል ላይ ማሳደር የቻሉት አዳማዎች የኢትዮጵያ ቡናን የኳስ ምስረታ ሒደትን ሙሉ ለሙሉ ማበላሸት ችለዋል። ከዚህ በዘለለ በመጀመሪያው አጋማሽ የተቆጠሩት ሁለት ግቦች የተቆጠሩባቸው ሒደት መነሻ የሆኑት ኳሶች የተገኙት በእነዚሁ በሜዳው የላይኛው ክፍል ከተደረጉ ከፍተኛ ጫናዎች ነበር።
በሁለተኛው አጋማሽ በመጠኑም ቢሆን ወደ ኃላ ያፈገፈጉት አዳማዎች ባሰቡት የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ውስጥ በራሱ ለተጋጣሚያቸው የሚቀመሱ አልነበሩም። በመልሶ ማጥቃት ሂደት አራት ግሩም አጋጣሚዎችን ቢፈጥሩም በተጫዋቾች ደካማ ውሳኔ አሰጣጥ የተነሳ ባክነው ቀሩ እንጂ ቡድኑ በጣም አስፈሪ ነበር።
በአስተዳደራዊ ጉዳይ እየታመሰ የሚገኘው ቡድኑ ከያዘው የተጫዋቾች ጥራት አንፃር ቡድኑ ለወትሮው ከሚከተለው ጥንቃቄ መር አጨዋወት ወጥቶ እንደ እሁዱ ጨዋታ በይበልጥ ተጫዋቾች ራሳቸውን ለመግለፅ በሚያስችል አጨዋወት ስልት ቢቃኝ ቡድኑ ከሊጉ አናት ከሚገኙ ቡድኖች ለመፎካከር የሚያንስ አለመሆኑን በትላንቱ ጨዋታ በሚገባ ማስመስከር ችሏል።
👉 የወልቂጤ ከተማ በአስደናቂ ሰሞነኛ ብቃት
ከሦስት የጨዋታ ሳምንታት በፊት በሊጉ ግርጌ የነበሩት ወልቂጤ ከተማዎች በተከታታይ ባስመዘገቧቸው ድሎች በመታገዝ በ17 ነጥቦች ወደ አምስተኛ ደረጃ ከፍ ማለት ችለዋል። በተከታታይ በወራጅ ቀጠና ውስጥ የነበሩትን ድሬዳዋ ከተማና ሀዲያ ሆሳዕናን ያሸነፉት ወልቂጤዎች በዚህኛው ሳምንት በሰንጠረዡ ከወገብ በላይ የሚገኘውን የአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝን ባህርዳር ከተማን 2-0 ማሸነፍ ችለዋል።
ከቀደመው ኳስ ቁጥጥር ላይ ካተኮረው አጨዋወት በመጠኑም ቢሆን ወጥተው እንደሁኔታው የሚቀያየርን አጨዋወት እየተከተሉ የሚገኘው ቡድኑ ስጋት ውስጥ ገብተው የነበሩትን የክለቡ አመራሮችና ደጋፊዎች በተከታታይ ባስመዘገቧቸው ውጤቶች ከስጋት አላቀው የተሻለ ነገር እንዲያልሙ ማድረግ ችለዋል።
👉 የመቐለ ሽንፈት
ላለፉት ሳምንታት ሊጉን ከአናት ሆነው ሲመሩ የሰነበቱት መቐለዎች በስተመጨረሻ ደረጃቸው ለቅዱስ ጊዮርጊስ አስረክበው ወደ ሦስተኛ ደረጃ ለመንሸራተት ተገደዋል። የሊጉን ክብር ወዳሳኩበት የቀድሞ ቤታቸው የተመለሱት አሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌ ስብስብ በ30ኛው ደቂቃ ብዙዓየሁ እንደሻው ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ ከጅማ ያለነጥብ ለመመለስ ተገደዋል።
ከሰሞኑ ጥሩ ብቃት ላይ የነበረው ናይጄሪያዊ አጥቂያቸውን ኦኪኪ አፎላቢን ጨምሮ የአማካዮቹን ያሬድ ከበደና ዮናስ ገረመውን ግልጋሎት በዚህ ሳምንት ማግኘት ያልቻሉት መቐለዎች ከሜዳቸው ውጭ ባደረጓቸው የመጨረሻ ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች በወላይታ ድቻና ጅማ አባጅፋር ሽንፈትን አስተናግደዋል። እንዲሁም የስብስብ ጥልቀት ችግር የሚነሳበት ቡድን በውድድር አጋማሹ በሚከፈተው የዝውውር መስኮት ላይ ጥገናዎችን ማድረግ ካልቻሉ የዐምናውን ክብራቸውን ለማስጠበቅ የሚያደርጉት ጥረት እክል እንዳይገጥመው የሚያሰጋ ነው።
👉 ስሑል ሽረ ወደ አሸናፊነት መመለስ
ባሳለፍነው ወር ከፍተኛ መሻሻሎችን አሳይተው ወደ ሰንጠረዡ አናት ተጠግተው የነበሩት ሽረዎች ባሳለፍነው ሳምንት በመቀለ ከደረሰባቸው ሽንፈት በማገገም ሀዋሳ ከተማ ላይ ጣፋጭ የ3-0 ድል ማስመዝገብ ችለዋል። ከጨዋታው በፊት በነበሩት ቀናት ከዋና አሰልጣኛቸው ሳምሶን አየለ ጋር ባልተከፈለ ደሞዝ ጉዳይ አለመግባባት ውስጥ ገብተው ለነበሩት ስሁል ሽረዎች ባለፈው ወር ድንቅ ጊዜ ያሳለፉት ነፃነት ገ/መድህንና አብዱለጢፍ መሀመድ ግብ ሲያስቆጥሩ በሒደት እየተሻሻለ የመጣው አጥቂው ሳሊፍ ፎፋና ቀሪዋን አንድ ግብ ማስቆጠር ችለዋል። በ12 ሳምንት የሊጉ ጉዞ በ19 ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አሁን ባለው አያያዙ እንደአምናው ላለመውረድ የሚታገልበት ሂደት እንደማይኖር ምልክቶች እየታዩ ይገኛል።
👉 እንደ ሁኔታው የማይለዋወጠው የካሳዬው ቡና እና የአዳማው ተቃውሞ
ለሀገራችን እግርኳስ የተለየ የአጨዋወት መንገድ ይዞ ብቅ ያለው የዘንድሮው ኢትዮጵያ ቡና ምንም እንኳን ገና እየተገነባ የሚገኝ ቢሆንም በተወሰኑ የቡድኑ ደጋፊዎች ዘንድ ግን ያለው ከልክ ያለፈ የውጤት ጉጉት ቡድኑ ላይ ጫና እንዳይፈጥር ያሰጋል። በነጥብ መቀራረቦች የተነሳ በአንድ ድል ብዙ የሰንጠረዥ መዘበራረቆቾ በሚስተዋልበት ሊጉ ከእሁዱ ሽንፈት በኃላ ኢትዮጵያ ቡና በ13 ነጥቦች በወራጅ ቀጠና ውስጥ በ14ኛ ደረጀ ላይ ለመቀመጥ ተገዷል። በዚህም ደስተኛ ያልሆኑ የተወሰኑ ደጋፊዎች ከአዳማ ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
ቡድኑ ባመነበት መንገድ እየተመራም ቢሆን ለመቀጠል በተጫዋቾቹ ዘንድ የነበረው የራስ መተማመን የደጋፊዎች ጫና በቀላሉ ተፅዕኖ ያሳርፍባቸዋል ለሚባሉት የሀገራችን ተጫዋቾች ጥሩ ማሳያ ቢሆንም ቡድኑ እንደ ቡድን አማራጭ የጨዋታ እቅዶች እንዳሉት ግን ያጠያይቃል። ለዚህም አሰልጣኙ በተደጋጋሚ በድህረ ጨዋታ ቃለ መጠይቆቻቸው ላይ ሲናገሩ እንደሚደመጡት የያዝነው መንገድ ውጤት ያመጣልናል ብለው የፀና እምነት ስላላቸው ስለአማራጭ መንገዶች ከማሰብ ይልቅ የያዙትን ነገር ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረጉ ላይ እንደሚያተኩሩ ሲናገሩ የሚደመጠው።
ቡድኑ ለመከተል በሚያስበው በኳስ ቁጥጥር ብልጫ የመጫወት ሀሳብ ውስጥ ኳስን ከኃላ ለመመስረት የሚደረገው ጥረት በሚፈለገው ደረጃ እስኪዳብር ስህተቶች መኖራቸው የግድና የማይቀር ነገር መሆኑ የማያጠያይቅ ሀቅ ሆኖ ሳለ በዚህ ሂደት በትላንቱ ጨዋታ በጫና ውስጥ ኳስን ለማቀበል ባደረጉት ሂደት ኳስን በተነጠቁ ተጫዋቾች እንዲሁም ቡድኑ እየተመራም ቢሆን ተጫዋቹ ቡድኑ በአመነበት መንገድ ፀንተው ኳስን በመቀባበላቸውና በተጨማሪም በከፍተኛ ደረጃ በሚገኙ ክለቦች የመጫወት ልምድ በሌላቸው ተጫዋቾች የተገነባው የፊት መስመር ላይ አጥቂዎች በግብ አቅራቢያ ኳስን በማንሸራሽራቸው መነሾነት ከቡድኑ ተከታታይ ሽንፈት ጋር ተዳምሮ የተወሰኑ ተቃውሞዎች ከትላንቱ ጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ ተደምጠዋል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የተወሰኑ የቡድኑ ደጋፊዎች የቡድኑ አባላት ላይ ባሰሙት ተቃውሞ የቡድኑ አባላት ረዘም ላሉ ደቂቃዎች በመልበሻ ቤት ለመቆየት የተገደዱ ሲሆን በተያያዘም አሰልጣኙ ካሳዬ አራጌ ከነበረው ነገር መነሻነት ድህረ ጨዋታ ቃለ ምልልስ መስጠት ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ ምንም እንኳን ደጋፊዎች ለክለባቸው አብዝተው ከመጨነቃቸው የተነሳ በመሰል ውጤት አልባ ጉዞዎች ላይ ተቃውሞዎች የሚጠበቁ ቢሆንም ከክለቡ ቦርድ ታሞኖበት ቡድኑን የመገንቢያ አንድ ዓመት የእፎይታ ጊዜ የተሰጠውን አሰልጣኝን ስራ በዚህ መልኩ መቃወም ወቅታዊነት ላይ ጥያቄ የሚያስነሳነው።
👉 የሀዲያ ሆሳዕና ውጤት አልባ ጉዞ
ዘንድሮ ዳግም ሊጉን ከተቀላቀሉ ወዲህ አስከፊ አጀማመር ቢያደርጉም ባለፉት ሳምንታት ውጤት ማስመዝገብ ጀምረው የነበሩት ነብሮቹ አሁንም ተከታታይ ሽንፈቶችን እያስተናገዱ ይገኛል። በ9 ነጥቦች 16ኛ ደረጃ የሚገኙት ሆሳዕናዎች ትላንትም በአዲስአበባ ስታዲየም በሰበታ በተሸነፉበት ጨዋታ በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ጥሩ ጥሩ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን ቢያገኙም መጠቀም ሳይችሉ ለሽንፈት ተዳርገዋል። በጨዋታው በሳምንቱ አጋማሽ በወልቂጤ ከተማ ሽንፈት በኃላ በነበረው ደረጃ ባይሆንም የቡድኑ ተጓዥ ደጋፊዎች ቡድኑ ሲከተለው በነበረው አጨዋወት ላይ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ተደምጠዋል።
ምንም እንኳን ገና የውድድር ዘመኑ እኩሌታ ላይ ያልደረስን ቢሆንም ቡድኑ ካለው ከፍ ያለ የተጫዋቾች ጥራት አንፃር አሁን ያለበት ደረጃ የሚገባው አይደለም። በመሆኑም በሁለተኛው የውድድር አጋማሽ ውድድሩ እየከበደ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ሀዲያ ሆሳዕናዎች ለውጦችን ማድረግ ካልቻሉ በቀጣይ ዓመት የከፍተኛ ሊግ ተሳታፊ የመሆናቸው ነገር የሚቀር እውነታ አይመስልም። (ክቡ የአሰልጣኝ ቡድኑን ከሰዓታት በፊት ከሥራ አግዷል፡፡)
© ሶከር ኢትዮጵያ