ወልዋሎዎች በሳሙኤል ዮሐንስ አስተባባሪነት ድጋፍ አደረጉ

ወልዋሎዎች የጣና ሞገዶቹን ለመግጠም ወደ ባህር ዳር ባቀኑበት ወቅት የቅዱስ ሚካኤል የህፃናት ማሳደግያ ማዕከል ጎበኝተው የነበረ ሲሆን ከቀናት በፊትም ቃል በገበቡት መሰረት ድጋፍ አድርገዋል።
በማዕከሉ ባደገው ሳሙኤል ዮሐንስ አስተባባሪነት የተደረገው ይህ ድጋፍ የአሰልጣኞች ቡድን አባላትን ጨምሮ ሙሉ የቡድኑ ተጫዋቾች ያሳተፈ ሲሆን አባላቶቹም በየአቅማቸው ከደሞዛቸው በየወሩ ለማዕከሉ ድጋፍ ለማድረግ ነው ቃል የገቡት።

የበጎ አድራጎቱ ሀሳብ አመንጪ ሳሙኤል ዮሐንስ ከሶከር ኢትዮጵያ ባደረገው ቆይታ ለበጎ አድራጎቱ እንዲሳካ በጎ ፍቃዳቸው ያሳዩት የወልዋሎ እግር ኳስ ክለብ አባላትን አመስግኗል። “ሀሳቡን ሳመጣው መጀመርያ የቡድኑ አባላት ማዕከሉን እንዲጎበኙት እና ካዩት በኃላ የአቅማቸው እንዲደግፉ ነበር። ሀሳቤ ተሳክቶም መላ የቡድናችን አባላት ሁኔታውን አይተው በየወሩ እንደየ አቅማቸው እንዲደግፉ ቃል ገብተዋል ፤ ብዚህም በጣም አመሰግናቸዋለው” ብሏል።

ተጫዋቹ ጨምሮም ክለቦች ፣ ደጋፊዎች እና በእግር ኳሱ ዙርያ ያሉ አካላት ህልውናው አደጋ ላይ ላለው ይህ የህፃናት ማሳደግያ እንዲጎበኙት እና የአቅማቸው ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪውን አቅርቧል። “ክለቦች በማሕበረሰባዊ የበጎ ስራዎች ላይ መሳተፍ አለባቸው ፤ እኛ ተጫዋቾችም ከሚከፈለን ክፍያ አንፃር በየአቅማችን ብንደግፍ ጥሩ ነው።

” ይህ ማእከል እንደ ሌሎች የበጎ አድራጎት ማዕከላት በቂ ትኩረት እና ድጋፍ አላገኘም በዚህም ህልውናው ከጊዜ ወደ ጊዜ አደጋ ላይ እየወደቀ ነው ፤ በዚ አጋጣሚ ሌሎች ክለቦችም ተመሳሳይ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪየን አደርጋለው” ብሏል።

በ1973 በጀርመን አጋር ድርጅቶች ድጋፍ የተጀመረው ይህ ማዕከል በአሁኑ ወቅት ከአጋር ድርጅቶች ያገኝ የነበረው ድጋፍ በመቋረጡ እንደከዚህ ቀደሙ ሰፊ ሥራዎች ለመስራት እንደተቸገረ እና የፋይናንስ እጥረት ህልውናው ላይ ፈተና እንደሆነበት ከማዕከሉ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።


©ሶከር ኢትዮጵያ