“የውጭ ግብ ጠባቂዎች እያመለከ ለሚገኘው ሊጋችን የምንተስኖት የሙከራ ዕድል ለሁላችንም የማንቂያ ደውል ነው” መክብብ ደገፋ (ወላይታ ድቻ)

የእግርኳስ ህይወቱ ከዱራሜ የተነሳው መክብብ ወላይታ ድቻ በ2006 ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንዲቀላቀል ትልቅ አስተዋፆኦ ካበረከቱ ተጫዋቾች አንዱ የነበረ ሲሆን በወቅቱም የውድድሩ ኮከብ ግብ ጠባቂ በመሆን ተሸልሟል። እንደመነሻ ከነበረው ጥሩ አቋሙ ከወላይታ ድቻ ጋር ከተለያየ በኃላ አብዛኛው ጨዋታዎች ላይ ብዙም የመሠለፍ ዕድል ወዳላገኘባቸው ሀዋሳ ከተማ እና አዳማ ከተማ አምርቶ እድገቱ ተጓትቷል። ከሀምበሪቾ ጋር በከፍተኛ ሊግ የተሳካ ቆይታ በኃላ ወደ ደቡብ ፖሊስ በማምራት በፕሪምየር ሊግ እንዲገባ ትልቅ አበርክቶ አድርጓል። ዘንድሮ ደግሞ ወደ አሳዳጊው ክለብ በመመለስ እስከ አስራ ሁለተኛ ሳምንት ባሉት የወላይታ ድቻ የሊጉ ጨዋታዎች በዘጠኙ ላይ መሳተፍ ችሏል። ከወቅታዊ አቋም መዋዥቅ በኃላ ያለፉትን ጨዋታዎችን በማሸነፍ በተወሰነ መልኩ ከወራጅ ቀጠና የወጣበትን መሻሻል እንዲያሳይ ካስቻሉ ተጫዋቾች መካከል ግብጠባቂው መክብብ ደገፋ አንዱ ነው። መክብብ በወቅታዊ አቋሙ ዙርያ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።

ወደ ወላይታ ድቻ ካመራህ በኃላ በአመዛኙ ጨዋታዎች ላይ እየተጫወትክ ትገኛለህ

በደቡብ ፖሊስ አብሮኝ እየሰራ ከነበረው አሰልጣኝ ገብረክርስቶስን ተከትዬ ነው የመጣሁት እስካሁን ባለው የሊጉ አስራ ሁለት ጨዋታዎች ውስጥ በዘጠኙ ተሰልፌ በመጫወት ቡድኑን በምችለው አቅም እያገለገልኩ ነው። በሁሉም ነገር በድቻ ቤት ደስተኛ ነኝ፡፡ ከዚህ በኃላም ክለቡ ካለበት ደረጃ ለማሻሻል ከቡድን አጋሮቼ ጋር የምንችለውን አደርጋለው።

ወላይታ ድቻ የአሰልጣኝ ለውጥ ካደረገ በኃላ ጨዋታዎችን እያሸነፈ ደረጃውን እያሻሻለ ይገኛል ይህ በቡድኑ ውስጥ የተፈጠረው መነቃቃት እንዴት ይገለፃል።

አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ሊተገብረው የፈለገው አጫዋወት ቢኖርም ውጤት ሊቀናው አልቻለም ነበር። እኛም ቡድኑን ውጤታማ ለማድረግ ብንጥርም በጥቃቅን ስህተቶች ሳይሳካልን ቀርቶ ነበር። አሁን ወደ ምንፈልገው ውጤት መተናል። ደጋፊውም ከሜዳ ተደስቶ እየወጣ ይገኛል። አንዳንዴ ከሜዳ ውጭ የምንጥላቸውን ነጥቦችን ለማስተካከል በርትተን መስራት ይጠብቅብናል።

ኢትዮጵያውያን ግብጠባቂዎች ከሚገኝባቸው ጥቂት ክለቦች ከሆነው በወላይታ ድቻ እየተጫወትክ ነው። እስካሁንም ወደ ዘጠኝ ጨዋታዎች ላይ የመሰለፍ እድል እያገኘህ ነው ይህ የሰጠህን ልምድ አጋራኝ

ኢትዮጵያ ውስጥ የውጭ ግብጠባቂዎችን እያመለኩ የሚገኙ ክለቦች በዝተዋል፡፡ ታችኞቹ ሊጎች ሳይቀር እየተመለከትን ነው። ይሄ በጣም አሳሳቢ ነው፡፡ እንደነ ሱሑል ሽረ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ድሬዳዋ ከተማ እና የእኛንም ቡድን ጨምሮ ያሉት አመራሮች በዚህ ሊመሠገኑ ይገባል። ኢትዮጵያውያን በረኞች ከየት መተን እዚህ እንደደረሰን እኛ እናውቀዋለን። በብዙ ልፋት ሰርተን ወደ በፕሪምየር ሊጉ መጫወት እየቻልን ታፍነን እንገኛለን። ሁሉም ነገር እኛ ላይ ይበረታል። እኔ አሁን በድቻ ቤት በምችለው መጠን ቡድኑን እየረዳው ነው። ግብ ጠባቂነት ተቀያሪ ውንበር ላይ ቁጭ ብለህ የምታመጣው ብቃት አይደለም። ከጨዋታ ጨዋታ ልምድ የምታገኝበት ነው። ብዙ በተጫወትክ ቁጥር ብዙ ስህተቶችን ትቀንሳለህ። ድቻ ቤት በሚገባ የመጫወት ዕድል እያገኘው ነው ይህ ደግሞ እራሴን እንዳሻሽል ይረዳኛል።

በኢትዮጵያ እግርኳሳችን ብዙም ባልተለመደ ሁኔታ ግብጠባቂ ወደ ውጭ በመሄድ ምንተስኖት አሎ የሙከራ ጊዜ እያሳለፈ ይፈኛል። ይህ ለኢትዮጵያውያን አሰልጣኞች እንዲሁም ለእናተ የሚሰጠው ተስፋ አለ?

በሚገባ እንጂ፣ እንግዲህ ተመልከት እኛ እዚህ ሆነን እድል አጥተን እየተቸገርን ምንተስኖት በውጭ ሀገር ሊግ በሚገኝ ያውም በአውሮፓ ክለቦች ተፈልጎ ለሙከራ መሄዱ መሰማቱ በራሱ ምንም ሳልናገር ይሄ ብቻ ምን ያህል ኢትዮጵያውያን በረኞች አቅም እንዳላቸው በቂ ምስክር ነው። የውጭ ሀገር በረኛ እያመለክን ለሚገኘው ሊጋችን የምንተስኖት የሙከራ ጊዜ ለሁሉም የማንቂያ ደውል ነው። ለእኔ ይሄንን ዜና ስሰማ በጣም ነው የተደሰትኩት እኔም ብቻ ሳልሆን ሌሎችም ጭምር ደስተኛ ይሆናሉ ብዬ አስባለው። የምንተስኖት እዚህ ደረጃ መድረስ ለእኛ ትልቅ ብርታት የሚሰጠን ወደፊትም ግብጠባቂ ለመሆን ለሚያስቡትም ትልቅ መነሳሳት የሚፈጥር ጉዳይ ነው። በዚህ አጋጣሚ ለምንቴ መልካም ዕድል እንዲገጥመው እመኛለው።

ወደ ወላይታ ድቻ ልመለስና ጥያቄዬን ላጠቃልል። ለጊዜውም ቢሆን ከወራጅ ቀጠናው ሸሽታችኃል በቀጣይ ወላይታ የመውድ ስጋት ይጋረጥበት ይሆን?

በፍፁም አይታሰብም። ምክንያቱ ድቻ ውስጥ ከታዳጊ እስከ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች የተሰባሰቡበት ቡድን ነው። አንዳንዴ ከጥንቃቄ እና ከትኩረት ማጣት የሚፈጠሩ ስህተቶች ነው ውጤት እንድናጣ ያደረገን። አሁን ላይ በከፍተኛ መነቃቃት ላይ እንገኛለን። ትንሽ ያለፉትን ሳምንታት ከተለያዮ ነገሮች ጋር ተያይዞ ተረብሸን ነበር።ከዚህ በኃላ ሁላችንም ሜዳ ውስጥ የምንችለውን ሰጥተን እነዚህን በርካታ ደጋፊዎችን እያስደሰትን ደረጃችንን እያሻሻልን እንቀጥላለን ብዬ አስባለው።


© ሶከር ኢትዮጵያ