ምንተስኖት አሎ ሙከራውን አጠናቆ ዕሁድ ይመለሳል

በቱርኩ ክለብ አንታናይስፓር ለሳምንታት የሙከራን ጊዜን ያሳለፈው ምንተስኖት አሎ ዕሁድ ወደ ኢትዮጵያ ይመለሳል፡፡

ለተጫዋቹ የሙከራ እድል ያመቻቹለት በቱርክ ከተጫዋቾቹ ጋር የሚገኙት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ማኔጀር አቶ እንዳለየሱስ አባተ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለፁት የተጫዋቹ የሙከራ ጊዜ በተሳካ ሁኔታ የተጠናቀቀ ሲሆን የክለቡ ሰዎች በተጫዋቹ ደስተኛ የነበሩ ቢሆንም የዝውውር ቀኑ መዘጋቱ በተጫዋቹ ላይ እክል ሆኗል ይላሉ፡፡ “የሙከራ ጊዜው በጥሩ መልኩ ተጠናቋል። ሒደቱ ጥሩ ነበር፤ ነገር ግን ምንተስኖት ወደዚህ ሲመጣ ዝውውሩ ሊጠናቀቅ አራት ቀን ብቻ እየቀረው ነበር። ያ ደግሞ እንደሌሎች እንዳደጉ ሀገሮች ምስል ስለሌለን በአካል የሚያዩበት ጊዜም ሊረዝም ችሏል፡፡ ስለ ኢትዮጵያ ኳስ ለማወቅ በጣም ይቸግራል። ነገር ግን ስለውጪዎቹ ተጫዋቾች በቀላሉ የፈለከውን በጊዜ ታገኛለህ። ያም አንዱ እክል ነበረ” ብለዋል።

አቶ እንዳለየሱስ ተጫዋቹ በቀጣዩ የዝውውር ጊዜ በድጋሚ ተመልሶ በመምጣት ሊፈርም እንደሚችል የተናገሩ ሲሆን ክለቡ እዛው ልምምድ እየሰራ እንዲቆይ ቢፈልግም በሽረ ውል ስላለውና ለሀገሩም መጫወት ስላለበት ዕሁድ ይመለሳል ብለዋል፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ