ሀዲያ ሆሳዕና ፀጋዬ ኪዳነማርያምን የክለቡ አሰልጣኝ አድርጎ ሾመ

ከአሰልጣኝ ግርማ ታደሰ ጋር የተለያየው ሀዲያ ሆሳዕና ፀጋዬ ኪዳነማርያምን የክለቡ አሰልጣኝ በማድረግ ቀጥሯል፡፡

ክለቡ የአሰልጣኝ ቡድን አባላትን አግጃለሁ ቢልም ትላንት አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር በነበራቸው ቆይታ ከክለቡ ጋር መለያየታቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡ ክለቡ ከወልቂጤ ከተማ ጋር በሜዳው ሲጫወት ደጋፊዎች ባሳዩት የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ምክንያት በተላለተፈበት ቅጣትም ሀዋሳ ላይ የፊታችን ማክሰኞ ወላይታ ድቻን በህክምና ባለሙያው ቢኒያም ተፈራ እየተመራ ይገጥማል፡፡

ከዚህ ጨዋታ በመቀጠል በዋና አሰልጣኝነት ክለቡን እንዲረከቡ አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያምን ምርጫው አድርጓል፡፡ የቀድሞው የትራንስ፣ ሀረር ቢራ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ንግድ ባንክ፣ አርባምንጭ ከተማ እና ወልዋሎ አሰልጣኝ በክረምቱ ወደ ሰበታ ከተማ ለማምራት ከጫፍ ደርሰው የነበረ ቢሆንም ዕክል ገጥሞት ክለቡን መቀላቀል ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ ያለፉትን ሰባት ወራት ከአሰልጣኝነት ርቀው በእረፍት ያሳለፉት አሰልጣኙ ውጤት የራቀውን ክለብ በሊጉ ለማቆየት በአንድ ዓመት የውል ጊዜ ዛሬ በይፋ መቀላቀላቸውን የክለቡ ስራ-አስኪያጅ አቶ መላኩ ማደሮ በተለይ ለሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጠዋል፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ