በአዲስ አበባ ስታድየም በተካሄዱ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ 7ኛ ሳምንት ቀሪ ሁለት ጨዋታዎች ጌዲኦ ዲላ እና መከላከያ ተጋጣሚያቸውን ማሸነፍ ችለዋል።
09:00 የጀመረው የአቃቂ ቃሊቲ እና የጌዲኦ ዲላ ጨዋታ እንግዶቹ የመጀመርያው አጋማሽ ባስቆጠሯቸው ሁለት ጎሎች 2-1 አሸንፈው ሊወጡ ችለዋል። ተመሳሳይ የእግርኳስ ክህሎት ያላቸው ተጫዋቾች የተገናኙበት እና ተመጣጣኝ ፉክክር በተመለከትንበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የአቃቂዋ አጥቂ ሠላማዊት ጎሳዬ የተጣለላትን ኳስ ይዛ በመግባት በቀጥታ ወደ ጎል የመታችውን የጌዲኦ ግብጠባቂ ቤተልሔም ዮሐንስ አድናባታለች።
በጨዋታው ጅማሬ የመጀመርያ የጎል ሙከራቸው ማድረጋቸውን ተከትሎ በተሻለ ሁኔታ ጨዋታውን ይቆጣጠራሉ ቢባልም የጨዋታው ሚዛን ወደ እንግዶቹ ጌዲኦ ዲላዎች አመዝኖ ተደጋጋሚ ግልፅ የማግባት አጋጣሚዎች መፍጠር ችለዋል። ድንቅነሽ በቀለ የአቃቂ ተከላካዮች ኳሱ ከጨዋታ ውጭ ነው በማለት በተዘናጉበት አጋጣሚ ጎል መሆን የሚችል ዕድል ቢፈጠርላትም ግብጠባቂዋ ሽብሬ ካኮ ያዳነችባት፣ ከደቂቃዎች በኃላ በድጋሚ ጌዲኦዎች ከቀኝ መስመር ወደ ሰጥኑ የገባች የመስመር አጥቂዋ ቤተልሔም አስረሳኸኝ በቀጥታ ወደ ጎል መታ ለጥቂት የወጣባት ተጠቃሽ የጎል ሙከራዎች ነበሩ።
36ኛው ደቂቃ ግን ጥረታቸው ተሳክቶ ከተከላካዮች መሐል አፈትልካ የወጣችው ድንቅነሽ በቀለ ከግብጠባቂ ሽብሬ ጋር ተገናኝታ ስትመታው የተመለሰባትን ኳስ በድጋሚ አግኝታ ባስቆጠረችው ጎል ጌዲኦዎችን ቀዳሚ ማድረግ ችላለች። በሁለት ሦስት ኳሶች ንኪኪ ወደ ፊት የሚሄዱበትን ፍጥነት መቆጣጠር ያቃታቸው አቃቂዎች ሁለተኛ ጎል ለማስተናገድ ተገደዋል። 45ኛው ደቂቃ ላይ ፈጣኗ አጥቂ ረድኤት አስረሳኸኝ ፍጥነቷን ተጠቅማ ወደ ፊት በመግባት መሬት ለመሬት በጠንካራ ምቷ መሪነታቸውን በሁለት ጎል ከፍ ያደረጉበትን ጎል አስቆጥራለች።
ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ማድረግ የጀመሪት አቃቂዎች በ63ኛው ደቂቃ ፀባኦት መሐመድ ከርቀት ባስቆጠረችው ግሩም የቅጣት ምት ጎል ልዩነቱን አጥብበዋል። ሆኖም ደስታዋን ገልፃ ሳትጨርስ መቀየሯ አስገራሚ አጋጣሚ ሆኖ አልፏል።
በሁለተኛው አጋማሽ ተዳክመው የገቡት እና ተደጋጋሚ በሆነ የጨዋታ አቋቋም ስህተት እየሰሩ ከእንቅስቃሴ ውጪ የነበሩት ጌዲዮዎች ውጤቱን አሳልፈው ለመስጠት ተቃርበው ነበር። በተለይ ወደ መጨረሻዎቹ ደቂቃዎች አቃቂዎች ጫና ፈጥረው ሲጫወቱ 85ኛው ሠላማዊት ኃይሌ በጥሩ ሁኔታ ወደ ጎል መታ የግቡ ቋሚ የመለሰበት አቻ መሆን የሚችሉበት የሚያስቆጭ አጋጣሚ ሆኖ አልፏል። ተቀይራ የገባቸው የጌዲኦ አጥቂ ትዝታ ፈጠነ በመልሶ ማጥቃት ግልፅ አጋጣሚ አግኝታ ሳትጠቀምበት ቀርታ ጨዋታው በጌዲኦ ዲላ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
11:00 በቀጠለው ሁለተኛ ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪክን ከመከላከያ አገናኝቶ መከላከያዎች በሁለተኛው አጋማሽ ድክመታቸውን አርመው በመግባት ባስቆጠሯቸው አራት ጎሎች 4-1 በሆነ ውጤት አሸንፈው ሊወጡ ችለዋል።
ቀዝቀዝ ብሎ የጀመረው እና 10ኛው ደቂቃ በኃላ የተነቃቃው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የኢትዮ ኤሌክትሪክ የመስመር አጥቂ መሳይ ተመስገን ከሳጥን ውጭ በጠንካራ ምቷ የፈጠረችው የጎል ዕድል እና ግብጠባቂዋ ታሪኳ በርገና ያዳነችው የጨዋታው የመጀመርያ ሙከራ ነበር። ኤሌክትሪኮች በኳስ ቁጥጥሩ የተሻሉ ይሁኑ እንጂ መከላካዮች ግልፅ የማግባት አጋጣሚ በመፍጠር ረገድ ጥሩ ነበሩ። 15ኛው ደቂቃ መዲና ዐወል ለጎል የቀረበ ኳስ አግኝታ ከእርሷ በተሻለ አቋቋም ለምትገኘው አረጋሽ ካልሳ ማቀበል ስትችል ራሷ ለመጠቀም አስባ ያመከነችው እንዲሁም 22ኛው ደቂቃ ሄለን እሸቱ ያልተጠቀመችበት ኳስ ለመከላከያዎች የተፈጠሩ ጥሩ የጎል እድሎች ነበሩ።
ጥሩ ፉክክር እያስመለከተን በየቀጠለው ጨዋታ እጅግ ለጎል የቀረበ ኳስ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች መፍጠር ችለዋል። 27ኛው ደቂቃ መሳይ በጠንካራ ምቷ በግራ እግሯ የመታችውን ግብጠባቂዋ ታሪኳ በርገና ኳሱን ለማዳን የተፋችውን ኳስ በድጋሚ አግኝተው ሲመቱ እንደምንም ዘቢባ ኃ/ሥላሴ ተደርባ አውጥታባቸዋለች።
ወደ መከላከያ የግብ ክልል ይደርሱ የነበሩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች 40ኛው ደቂቃ የተሰጠውን ቅጣት ምት መሳይ ተመስገን በቀጥታ ወደ ጎል የመታችው ቀላል ኳስ ግብጠባቂዋ ታሪኮ በርገና ስህተት ታክሎበት ኢትዮ ኤሌክትሪክን ቀዳሚ መሆን የቻሉበትን ጎል አስቆጥረዋል።
ከእረፍት መልስ ሙሉ ለሙሉ የጨዋታው መልክ ተቀይሮ የመከላከያ ፍፁም የበላይነት ታይቶበታል። በተለይ የፊት መስመር አጥቂዎቹ ሄለን እሸቱ፣ መዲና ዐወል እና አረካሽ ካልሳ አስፈሪ ጥምረት ቡድኑን ውጤታማ አድርጎታል። 47ኛው ደቂቃ ግልፅ የማግባት አጋጣሚ አረጋሽ ካልሳ ፈጥራላት መዲና ዐወል ወደ ጎል ብትመታውም የግቡ አግዳሚ የመለሰባት ብዙም ሳይቆይ በአንድ ሁለት ቅብብል በፍጥነት የገቡት መከላካያዎች ሄለን እሸቱ በተከላካዮች መሐል የጣለችላትን መዲና ዐወል በአስገራሚ ሁኔታ በግብጠባቂዋ ትዕግስት አናት ላይ አሾልካ መከላከያን አቻ ማድረግ ችላለች።
ከጎሉ መቆጠር በኃላ የኢትዮ ኤሌክትሪክን የመስመር ተከላካዮችን ክፍተት ሲጠቀሙ ያመሹት መከላከያዎች በተደራጀ ሁኔታ መዲና ዐወል ከግራ መስመር ያሳለፈችላትን በግራ እግሯ መሬት ለመሬት አጠንክራ በመምታት የግቡን ቋሚ ገጭቶ ሁለተኛ ጎል በ60ኛው ደቂቃ አረጋሽ ካልሳ አስቆጥራለች።
የሰሚራ ከማል በጉዳት መውጣት የቡድኑን ሚዛን ያፋለሰው የኢትዮ ኤሌክትሪክ እንቅስቃሴ ብዙም የተጠና አጨዋወት ሳንመለከት ቀጥሎ 80ኛው ደቂቃ ሌላ ጎል ሊቆጠርባቸው ቸሏል። ከእረፍት መልስ በተሻለ መንቀሳቀስ የቻለችው አረጋሽ ለቡድኗ ሦስተኛ ለራሷ ሁለተኛ ጎል አስቆጥራለች።
በመጨረሻም 87ኛው ደቂቃ የኢትዮ ኤሌክትሪክን ተከላካዮች የሰሩት ስህተት ተጠቅማ አረጋሽ በግሏ ሐት-ትሪክ መስራት የቻለችበትን አራተኛ ጎል ለመከላከያ አስቆጥራ ጨዋታው በመከላከያ 4-1 በሆነ ውጤት አሸናፊነት ተጠናቋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ