ሪፖርት | ዐፄዎቹ የዓመቱ የመጀመርያ የሜዳ ውጪ ድላቸውን የቅርብ ተቀናቃኛቸው ላይ አስመዝግበዋል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 13ኛ ሳምንት ዛሬ በተደረገ አንድ ጨዋታ ሲጀመር የሰንጠረዙ አናት ላይ ተፎካካሪ የሆኑት መቐለ እና ፋሲልን ያገናኘው የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ትግራይ ስታዲየም ላይ ተከናውኖ ፋሲል ከነማዎች ጣፋጭ የ2-0 ድል አስመዝግበዋል።

መቐለዎች ባለፈው ሳምንት በጅማ ሽንፈት ከደረሰበት ስብስብ ታፈሰ ሰርካ፣ ላውረንስ ኤድዋርድ፣ አሸናፊ ሀፍቱ እና ክብሮም አፅብሀን በማሳረፍ በቢያድግልኝ ኤልያስ፣ አስናቀ ሞገስ፣ ሥዩም ተስፋዬ እና ኦኪኪ ኦፎላቢ ተክተው ሲገቡ ዐፄዎቹ በበኩላቸው ወልዋሎን ካሸነፈው የመጀመርያ አሰላለፍ ኪሩቤል ኃይሉን በሀብታሙ ተከስተ ብቻ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ብዙም ሳቢ ባልነበረው ጨዋታ በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ ተከላካይ ክፍላቸውን ወደ መሀል ሜዳው አስጠግተው በመጫወታቸው በቀጠናው በነበረው በርካታ የሰው ቁጥር ምክንያት አንዳቸውም የተሳካ ቅብብል ሳያደርጉ ቀርተዋል።

በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ባለሜዳዎቹ ከክፍት የጨዋታ እንቅስቃሴ እና ከቆሙ ኳሶች የግብ ዕድሎች ቢፈጥሩም ኳስና መረብ ማገናኘት አልቻሉም። አማኑኤል ገብረሚካኤል ከርቀት አክርሮ መትቶ ሳማኪ ያዳነው እና ዳንኤል ደምሴ ከሳሙኤል ሳሊሶ ጋር አንድ ሁለት ተቀባብሎ መቶ ማሊያዊው ግብጠባቂ የመለሰው ኳስ ይጠቀሳሉ።

በአንፃሩ ፋሲል ከነማዎች ወደ ግብ ያመሩበትን አጋጣሚ ወደ ግብነት በመለወጥ መምራት ችለዋል። በአስራ ሁለተኛው ደቁቃም ሰዒድ ሐሰን ከመስመር ያሻገረውን ኳስ ሽመክት ጉግሳ አመቻችቶት ሙጂብ ቃሲም በቀጥታ መትቶ ግሩም ግብ በማስቆጠር ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።

ከግቡ መቆጠር በኋላ ባለሜዳዎቹ አቻ ለመሆን የተሻለ ይንቀሳቀሳሉ ተብሎ ቢጠበቅም በአንፃሩ የዐፄዎቹ ብልጫ የታየበት ነበር። ያም ሆኖ መቐለዎች በቶሎ የአቻነት ግብ የሚያገኙበት አጋጣሚን አግኝተው አምክነዋል። በ17ኛው ደቂቃ ያገኙትን በፋሲል ሳጥን ውስጥ በተሰራ ጥፋት ፍፁም ቅጣት ምት አማኑኤል ገብረሚካኤል ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

ዐፄዎቹ በአጋማሹ ጥቂት የግብ ዕድሎች ቢፈጥሩም የተፈጠሩት ዕድሎች ግን ተጋጣሚያቸው ከፈጠራቸው ዕድሎች በተሻለ ግልፅ ዕድሎች ነበሩ። ከነዚህም መካከል ሱራፌል ዳኛቸው ከቅጣት ምት ሞክሯት ፊሊፕ ኦቮኖ ያዳናት ኳስ ትጠቀሳለች። መደበኛው የጨዋታ ሰዓት ተጠናቆ በተሰጠው ተጨማሪ ደቂቃም ዐፄዎቹ ተጨማሪ ግብ አስቆጥረዋል። ሱራፌል ዳኛቸው የተከላካዮች የአቋቋም ችግር አይቶ ለሙጂብ ቃሲም ያቀበለውን ኳስ አጥቂው በግሩም አጨራረስ አስቆጥሮ ነበር የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ የቻለው።

የባለሜዳዎቹ ፍፁም ብልጫ እና የዐፄዎቹ ግብ ጠባቂ ሳማኪ ሚኬል ድንቅ ብቃት የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ በመቐለዎች በኩል በርካታ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች የታዩበት ነበር። በተለይም የፋሲል ከነማው ግብ ጠባቂ በአጋማሹ ያሳየው ድንቅ ብቃት ቡድኑ ሙሉ ሥስት ነጥብ ይዞ እንዲወጣ አስችሏል።

በአጋማሹ መቐለዎች የተሻለ አጥቅተው በርካታ ሙከራዎች ሲያደርጉ ዐፄዎቹ የያዙትን መሪነት አስጠብቀው ለመውጣት አፈግፍገው ተጫውተዋል። መቐለዎች ካደረጓቸው ሙከራዎች መካከል አማኑኤል ገብረሚካኤል ከቀኝ መስመር በኩል አክርሮ መቶት ለጥቂት የወጣው ኳስ እና ቢያድግልኝ ኤልያስ ከቅጣት ምት ያደረገው ሙከራ ይጠቀሳሉ።

ባለሜዳዎቹ ከላይ ከተጠቀሱት ሙከራዎች ውጭም የጨዋታውን መልክ ሊቀይሩ የሚችሉ በርካታ ሙከራዎች አድርገው በጨዋታው ኮከብ በነበረው የዐፄዎቹ ግብ ጠባቂ ተመልሶባቸዋል። በሳማኪ ምርጥ ብቃት ከዳኑት ሙከራዎች ውስጥም ኦኪኪ ኤፎላቢ በግንባር ሞክሮት ግብ ጠባቂው እንደምንም ያዳነው፣ አማኑኤል ከመስመር የተሻማው ኳስ በግንባሩ ገጭቶ መቶት ግብ ጠባቂው ያዳነው ሙከራ እና አሸናፊ ሀፍቱ አክርሮ መቶት ከጎሉ ከመስመር የሚጠቀሱ ናቸው።

በአጋማሹ አብዛኛውን ጊዜ በራሳቸው የሜዳ ክልል ተገድበው አፈግፍገው የተከላከሉት ፋሲል ከነማዎች ኦሴይ ማውሊ ከርቀት ካደረገው ሙከራ ውጪ ይህ ነው የሚባል የጎል ዕድል መፍጠር አልቻሉም።

በጨዋታው የጭማሪ ደቂቃ ላይ የመቐለው ዳንኤል ደምሴ በሰራው ጥፋት በሁለት ቢጫ ከሜዳ ሊወጣ ችሏል።

ጨዋታው በዐፄዎቹ 2-0 አሸናፊነት መጠናቀቁ ተከትሎ ቡድኑ በዓመቱ የመጀመርያ የሜዳ ውጪ ድሉን በማስመዝገብ በጊዜያዊነት ሊጉን መምራት ሲጀምር መቐለዎች ተከታታይ ሁለተኛ ሽንፈታቸው አስተናግደዋል።

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ