ምዓም አናብስት በሜዳቸው ዐፄዎቹን የሚያስተናግዱበት የሳምንቱ ተጠባቂ እና የነገ ብቸኛ ጨዋታን እንደሚከተለው ዳሰነዋል።
በጅማ አባጅፋር ሽንፈት ከገጠማቸው በኋላ ከመሪነታቸው የወረዱት መቐለዎች ዳግም ወደ አሸናፊነት መንገድ ለመመለስ ከዚህ ጨዋታ ሦስት ነጥብ ያስፈልጋቸዋል።
የመቐለ 70 እንደርታ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ) | ||||
ተሸነፈ | አሸነፈ | ተሸነፈ | አሸነፈ | አሸነፈ |
ባለፈው ሳምንት ወሳኝ ተጫዋቾቻቸው በጉዳት ሳያካትቱ ወደ ጅማ ተጉዘው በጅማ አባጅፋር ሽንፈት የገጠማቸው 70 እንደርታዎቹ በዚህ ጨዋታ የተወሰኑ ተጫዋቾቻቸውን ከቅጣት እና ከጉዳት መልስ ማግኘታቸውን ተከትሎ በርካታ ለውጦች ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በሜዳቸው በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ቀጥተኛ አቀራረብ ያላቸው አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ በዚ ጨዋታም በማጥቃት አጨዋወታቸው ለውጥ ያደርጋሉ ተብሎ ባይጠበቅም ተጋጣምያቸው ፋሲል ከነማ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስዶ ለመጫወት የሚሞክር ቡድን እንደመሆኑ ለዐፄዎቹ የአማካይ ጥምረት በቀላሉ እጅ ላለመስጠት ከባለፉት ጨዋታዎች በተለየ ኳሱን ይዞ ለመጫወት ጥረት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። በዚህም ባለፉት ጨዋታዎች ለአጥቂዎች ኳስን በማሻገር ተወስኖ የነበረው የዳንኤል ደምሴ እና ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ ጥምረት በአጨዋወቱ ወሳኝ ሚና ይዞ ይገባል ተብሎ ሲገመት ቡድኑ በአማካይ መስመር ላይ ዮናስ ገረመው እና ያሬድ ከበደን ማጣቱን ግን አጨዋወቱን በሰመረ መንገድ ለመተግበር ይቸግረዋል ተብሎ ይገመታል።
አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ኦኪኪ ኦፎላቢ እና ሥዩም ተስፋዬን ከቅጣት እና ከጉዳት መልስ ማግኘታቸው ጥሩ ዜና ቢሆንም በተለይም በአማካይ ክፍል ላይ ያለው የጥራት እና የአማራጭ እጥረት የተለየ አቀራረብ ይዞ እንዲገባ ሊያስገድደውም ይችላል።
ምዓም አናብስት በነገው ጨዋታ ዮናስ ገረመው፣ ሚካኤል ደስታ እና ያሬድ ከበደን በጉዳት ሲያጡ ሥዩም ተስፋዬ እና አንተነህ ገብረክርስቶስ ከጉዳት ኦኪኪ ኦፎላቢ ከቅጣት መልስ ያገኛል።
የፋሲል ከነማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ) | ||||
አሸነፈ | አቻ | አሸነፈ | ተሸነፈ | አሸነፈ |
ከሜዳቸው ውጭ ባደረጓቸው ጨዋታዎች አሸንፈው ለመውጣት ሲቸገሩ የሚታዩት ዐፄዎቹ በነገው ዕለትም ከመቐለ ከባድ ፈተና ይጠብቃቸዋል።
በውድድር ዓመቱ ከሜዳቸው ውጭ ባደረጓቸው ጨዋታዎች እንደ አማካይ ክፍል ጥምረቱ የሚለያይ አቀራረብ የነበራቸው አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ በአመዛኙ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለመውሰድ የሚጥር ቡድን ገንብተዋል። ሀብታሙ ተከስተ ቋሚ ሆኖ በጀመረባቸው ጨዋታዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለመውሰድ ጋብርኤል አህመድን በሚጠቀሙበት ጨዋታ ደግሞ ለአጥቂዎች በሚሻገሩ ረጃጅም ኳሶችን የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የሚሞክሩት ዐፄዎቹ በነገው ዕለትም በውጤታማው አጥቂ ሙጂብ ቃሲም የሚመራው የሰላው የአጥቂ ክፍላቸው የተገኙ አጋጣሚዎችን ወደ ግብ የመቀየሩ ትልቅ ኃላፊነት ተሸክሞ ወደ ሜዳ ይገባል። በዚህም ቡድኑ በነገው ዕለት የጋብርኤል አሕመድን ግልጋሎት ስለማያገኝ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስዶ በሁለቱም መስመሮች በኩል ለማጥቃት አልሞ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።
ከዚህ በተጨማሪ ባለፉት ጨዋታዎች ጥያቄዎች ሲነሳበት የነበረው የቡድኑ የመከላከል ጥምረት ያሬድ ባየህ ከጉዳት መልስ ማግኘቱ ለአሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ትልቅ እፎይታ ነው። ከጉዳት መልስ ለጨዋታ ዝግጁ የሆነው እንየው ካሣሁን ከተሰለፈም በቡድኑ ጥሩ ማጥቃያ አማራጭ ይፈጥራል ተብሎ ይገመታል።
ዐፄዎቹ ጉዳት ካጋጠመው ከጋብሬል አህመድ በስተቀር ሙሉ ቡድናቸውን ይዘው ወደ መቐለ አምርተዋል።
እርስ በርስ ግንኙነት
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ አራት ጊዜ ተገናኝተው አንድ አንድ ጊዜ በየሜዳቸው የ1-0 ድል ሲያስመዘግቡ በገለልተኛ (አአ ስታዲየም) ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ የለ ጎል አቻ ተለያይተዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
መቐለ 70 እንደርታ (4-4-2)
ፊሊፕ ኦቮኖ
ሥዩም ተስፋዬ – ላውረንስ ኤድዋርዶ – አሌክስ ተሰማ – አንተነህ ገብረክርስቶስ
አሸናፊ ሀፍቱ – ዳንኤል ደምሴ – ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ – ሳሙኤል ሳሊሶ
አማኑኤል ገብረሚካኤል – ኦኪኪ ኦፎላቢ
ፋሲል ከነማ (4-3-3)
ሚካኤል ሳማኬ
እንየው ካሣሁን – ከድር ኩሊባሊ – ያሬድ ባየ – አምሳሉ ጥላሁን
በዛብህ መለዮ – ሀብታሙ ተከስተ – ሱራፌል ዳኛቸው
ሽመክት ጉግሳ – ሙጅብ ቃሲም – ኦሲ ማውሊ
© ሶከር ኢትዮጵያ