ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | አዳማ የሊጉን መሪነት ሲረከብ ሀዋሳ እና ባንክ ነጥብ ተጋርተዋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ከአንድ ወር መቋረጥ በኋላ በአምስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሲቀጥል ዛሬ ሁለት ተጠባቂ መርሐ ግብሮች ተስተናግደውበት አዳማ አሸንፏል፤ ሀዋሳ እና ንግድ ባንክ ያደረጉት ጨዋታ ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

አዳማ ከተማ 2-0 መከላከያ
(ዳንኤል መስፍን)

ሁለት መልክ በነበረው የሁለት ቡድኖች ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ አዳማዎች በሁለተኛው አጋማሽ መከላከያዎች ብልጫ ወስደው ተጫውተዋል። አዳማዎች በፍጥነት ወደ መከላከያ የግብ ክልል ደጋግመው እንደመድረሳቸው ግልፅ የማግባት አጋጣሚ መፍጠር ቢቸገሩም 21ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት የተሻገረውን አልፍያ ጃርሶ በግንባሯ በመግጨት የአዳማን ቀዳሚ ጎል አስቆጥራለች።

ከጎሉ መቆጠር በኃላ መከላከያዎች በመልሶ ማጥቃት ምላሽ ለመስጠት ሞክረዋል።አረጋሽ ከርቀት መታ ግብጠባቂዋ እምወድሽ እንደምንም ወደ ውጭ በማውጣት ያዳነችው እና ሄለን እሸቱ ከመሐል ሜዳ አንስታ ተጫዋቾችን በማለፍ ወደ በመስመር ገብታ መዲና ጀመል የተቀበለችውን ኳስ በመቀስ ምት መታ ኳሱ በግብጠባቂዋ ፊት ለፊት በመሆኑ በቀላሉ የያዘችባት መከላከያዎች በተወሰደባቸው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ውስጥ የፈጠሯቸው የጎል አጋጣሚዎች ነበሩ።

የጨዋታው እንቅስቃሴ ቀጥሎ በ30ኛው ደቂቃ አልፍያ ጃርሶ ከርቀት የመታችው ኳስ የግቡ አግዳሚ የመለሰውን ነፃ አቋቋም ላይ የነበረችው የውድድሩ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነትን እየመራች የምትገኘው ሴናፍ ዋቁማ ለአዳማ ሁለተኛ ጎል አስቆጥራለች።

በመከላከያ በኩል በማጥቃቱም በመከላከሉም ረገድ ክፍተት የነበረበት የግራ መስመሩን ለማስተካከል አሰልጣኙ በወሰዱት ማስተካከያ ዘቢባ ኃይለሥላሴን በመቀየር ሄለን እሸቱን ወደ ኃላ በማድረግ አይዳ ኡስማንን በማስገባት የጀመረሩት የሁለተኛ አጋማሽ እንቅስቃሴ መከላከያዎችን የተሻሉ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። በ56ኛው ደቂቃም መዲና አወል ከግብጠባቂዋ እምወድሽ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝታ ኳሱን ሳትጠቀምበት ቀርታ ወደ ውጭ የወጣው፣ ዳግመኛ ሄለን እሸቱ ከግራ መስመር የጣለችላትን በድጋሚ መዲና ተንሸራታ ኳሱ የወጣበት እና ተቀይራ የገባችው የመከላከያ አጥቂ አይዳ ለጎል የቀረበ ሙከራ ብታደርግም መረቧን ላለማስደፈር በንቃት ስትጠብቅ የቆየችው የአዳማዋ ግብጠባቂ እምወድሽ ያዳነችባት ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥሩ እድል የፈጠሩበት አጋጣሚ ነው።

የመጨረሻዎቹን 15 ደቂቃዎች መከላከያዎች ደከም ሲሉ በአንፃሩ አዳማዎች ምርቃት ፈለቀ እና ተቀይራ የገባችው ሰርካዲስ ጉታ ከግብጠባቂዋ ታሪኳ በርገና ጋር ብቻቸውን ተገናኝተው ያልተጠቀሙበት ኳሶች የጎል መጠን ከፍ ማድረግ በቻሉ ነበር። ጨዋታውም በመጀመርያ አጋማሽ ባስቆጠራቸው ሁለት ጎሎች አማካኝነት አዳማ ከተማ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቆ ደረጃውን በማሻሻል ሊጉን መምራት ችሏል።

ሀዋሳ ከተማ 1-1 ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
(ቴዎድሮስ ታከለ)

ተመጣጣኝ እንቅስቃሴን ባየንበት የመጀመሪያ አጋማሽ ከቅብብል ስህተት አልያም ደግሞ ከቆሙ ኳሶች ከሚደረጉ ሙከራዎች በስተቀር የጎላ የእንቅስቃሴም ሆነ አስጨናቂ የሚባሉ የግብ አጋጣሚዎችን ለመመልከት አልተቻለም፡፡ ሆኖም ሀዋሳ ከተማዎች ወጥነት ይጉደላቸው እንጂ ከንግድ ባንክ በተሻለ መልኩ ለመጫወት ሞክረዋል፡፡ 12ኛው ደቂቃ በንግድ ባንክ የግብ ክልል በቀኝ በኩል አጋድሎ የተገኘውን የቅጣት ምት ዙፋን ደፈርሻ በቀጥታ ወደ ግብ ስትመታ ግብ ጠባቂዋ ንግስቲ ስትመልሰው ፊት ለፊቷ የነበረችሁ ቅድስት ቴካ በድጋሚ መታ ለጥቂት የወጣባት አስቆጪ ሙከራ ሀዋሳዎችን ቀዳሚ ልታደርግ የተቃረበች ብትሆንም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ከዚህ ሙከራ በኋላ ወደ መልሶ ማጥቃት አጨዋወት የተሸጋገሩት ንግድ ባንኮች የሀዋሳን ተከላካይ የቅብብል ስህተት ተከትሎ ረሂማ ዘርጋው በፍጥነት አግኝታ ወደ ግብ ስትመታው ዓባይነሽ ኤርቄሎ እንደምንም አውጥታዋለች፡፡

ባንኮች 35ኛው ደቂቃ ላይ መሪ የሚያደርጋቸውን ግብ አግኝተዋል፡፡ ከመሀል ሜዳው ወደ ቀኝ ባዘነበለ ቦታ የተገኘውን ቅጣት ምት ዓለምነሽ ገረመው ወደ ሀዋሳ የግብ ክልል በረጅሙ አሻግራ አምበሏ ረሂማ ዘርጋው በግንባሯ ጨረፍ በማድረግ የግብ ጠባቂዋ ዓባይነሽ የአቋቋም ስህተት ታክሎበት ከመረብ አርፋ ባንክን ቀዳሚ አድርጋለች፡፡

ግብ ካስተናገዱ በኋላ ወደ ማጥቃቱ አዘንብለው ለመጫወት መነቃቃት ሲታይባቸው የነበሩት ሀዋሳዎች ከአማካዮቻቸው ሲነሱ የነበሩ ኳሶች የተቆጠቡ ካለመሆናቸው የተነሳ እና አጥቂዎቹ ኳሶቹን ቢያገኙም ተረጋግቶ ወደ ግብነት ለመለወጥ ግን ችኮላዎች በመታየታቸው ለማስቆጠር ተቸግረዋል፡፡ 43ኛው ደቂቃ ገነሜ ወርቁ ከቅጣት ምት አክርራ መታ ዓባይነሽ ኤርቄሎ ካወጣች በኃላ ተጨማሪ ሙከራን ሳንመለከት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

ከእረፍት መልስ አሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድ አከታትለው አራት ተጫዋቾችን ለውጠው ካስገቡ በኃላ ሀዋሳ ከተማዎች በንግድ ባንክ ላይ ብልጫን እንዲያሳይ አድርገዋል፡፡ መቅደስ ማሞ፣ አረጋሽ ፀጋ፣ ዓይናለም አሳምነው እና ቅድስት ቴካን አስወጥተው ወርቅነሽ መሰለ፣ ዓይናለም አደራ፣ ምስር ኢብራሂም እና ትውፊት ካዲኖን ካስገቡ በኋላ ቡድኑ ቅርፅ ይዞ ለመጫወት አልተቸገረም፡፡ በተለይ አማካይ ክፍሉ ላይ ትውፊት ካዲኖ ኳሶች ወደፊት ቶሎ ቶሎ እየተሻገሩ ለአጥቂዎቹ ምስር ኢብራሂም እና መሳይ ተመስገን በማድረሱ ረገድ የተዋጣለት ነበረች፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ ለንግድ ባንክ መልሶ ማጥቃት ምቹ የነበሩት ሀዋሳ ከተማዎች ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ሜዳውን አጥብበው መጫወት በመቻላቸው ንግድ ባንኮችን ወደ ኃላ አፈግፍገው ኃላቸውን ለመዝጋት በማሰብም ወደ ፊት ተስቦ ከመጫወት ይልቅ ተጫዋች ቅያሪ በማድረግ መከላከል ላይ አተኩረዋል፡፡

ተደጋጋሚ ጫናዎችን ሲያሳድሩ የነበሩ ሀዋሳዎች ተሳክቶላቸው ግብ አስቆጥረዋል፡፡ 64ኛው ደቂቃ ላይ ወርቅነሽ እና ነፃነት በግሩም ሁኔታ ተቀባብለው ነፃነት የሰጠቻትን ኳስ መሳይ ተመስገን ወደ ሳጥኑ ገፋ ካደረገች በኃላ ግብ አስቆጥራ 1ለ1 አድርጋለች፡፡

ከግቧ በኃላ ሀዋሳዎች በምስር ኢብራሂም እና መሳይ ተመስገን ያለቀላቸውን ዕድሎች ቢያገኙም ንግስቲ መዓዛ አውጥታባቸዋለች፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ በሀዋሳ ለመበለጥ የተገደዱት የአሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ንግድ ባንኮች 86ኛው ደቂቃ ታሪኳ ዴቢሶ በቀኝ በኩል በቀጥታ ወደ ግብ መታ ዓባይነሽ ኤርቄሎ እንምንም አድናባታለች፡፡ ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ መቆጠር ሳይችል 1ለ1 ተጠናቋል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ