ሴቶች 2ኛ ዲቪዝዮን | ባህር ዳር ከተማ ሲያሸንፍ መሪው ሻሸመኔ ነጥብ ጥሏል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር 2ኛ ዲቪዚዮን ስድስተኛ ሳምንት ዛሬ ሦስት ጨዋታዎች ሲደረጉ ባህር ዳር ፋሲልን አሸንፏፍ። ሁለቱ ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል።

ባህር ዳር ላይ ፋሲልን የገጠመው ባህር ዳር ከተማ 2-1 አሸንፏል። በርከት ያሉ ደጋፊዎች በታደመበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ባህር ዳሮች በመጀመሪያው አጋማሽ ፋሲሎች ደግሞ በሁለተኛው አጋማሽ ተሽለው ተንቀሳቅሰውበታል። ባለሜዳዎቹ ባህር ዳር ከተማዎች በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በተሻለ በመንቀሳቀስ ግቦችን ለማስቆጠርም ሞክረዋል። በዚህም ጨዋታው በተጀመረ በ4ኛው ደቂቃ መንደሪን ታደሰ ከርቀት ጥሩ ሙከራ አድርጋ ወጥቶባታል። መንደሪን ይህንን ሙከራ ካደረገች ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ቡድኑ በድጋሜ ወደ ፋሲሎች የግብ ክልል በማምራት ግብ አስቆጥሯል። በዚህ ደቂቃ በጨዋታው ጥሩ ስትንቀሳቀስ የነበረችው ትዕግስት ወርቄ ከርቀት የተላከላትን ኳስ ከተከላካይ ጋር ታግላ ግብ አስቆጥራለች።

ገና በጊዜ መሪ የሆኑት ባህር ዳሮች ረጃጅም ኳሶችን አጠናክረው በመጠቀም ተጨማሪ ግቦችን ለማስቆጠር ጥረዋል። የመጀመሪያውን ግብ ያስቆጠረችው ትዕግስት በድጋሜ ከሰብለወንጌል ጥሩ ኳስ ተሰንጥቆላት ወደ ግብ የመታችው ኳስ ለጥቂት ወጥቶባታል። አሁንም ጥቃት መሰንዘራቸውን አጠናክረው የቀጠሉት ባህር ዳሮች በ17ኛው ደቂቃ እጅግ ለግብነት የቀረበ እድል አምልጧቸዋል። ሰብለወንጌል በድጋሜ ከግራ መስመር ያሻገረችውን ኳስ ትዕግስት በግንባሯ በጥሩ ሁኔታ ወደ ግብ መትታው ወጥቶባታል።

በጨዋታው ጅማሮ እጅግ ተዳክመው የታዩት ተጋባዦቹ ፋሲል ከነማዎች ከ20ኛው ደቂቃ በኋላ የተሻለ ለመንቀሳቀስ ጥረዋል። በ22ኛው ደቂቃም ቡድኑ የመጀመሪያውን ሙከራ በታደለች ዳያ አማካኝነት ሞክሮ ወጥቶበታል። ከዚህ ሙከራ ውጪ ብዙም የጠራ ሙከራ ማድረግ የተሳናቸው ፋሲሎች በኳስ ቁጥጥር ረገድ ተሽለው ታይተዋል። ነገር ግን ቡድኑ ወደ ግብ በመድረስ ሙከራዎችን ማድረግ ተስኖት ታይቷል።

በተቃራኒው ባህር ከተማዎች ረጃጅም ኳሶችን አዘውትረው በመጠቀም ተጨማሪ ግቦችን መፈለግ ተያይዘዋል። በ36 እና በ37ኛው ደቂቃም ቡድኑ በቤዛዊት እና በሊዲያ አማካኝነት ጥሩ ጥቃት ሰንዝሯል። የመጀመሪያውን ጎል ያስቆጠረችው ትዕግስት የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ በተጨመረው 1 ደቂቃ ለቡድኗ እና ለሯሳ 2ኛ ግብ አስቆጥራለች። አጋማሹም በባለሜዳዎቹ 2-0 መሪነት ተጠናቋል።

በመጀመሪያው አጋማሽ ተዳክመው የታዩት ፋሲሎች በሁለተኛው አጋማሽ ጫና መፍጠር ጀምረዋል። ገና አጋማሹ በተጀመረ በ1ኛው ደቂቃም ቡድኑ በቅድስት ገነነ አማካኝነት ሙከራ አድርጓል። በተጨማሪም በ55ኛው ደቂቃ ረድኤት ላይ የተሰራን ጥፋት ተከትሎ የተገኘን የቅጣት ምት ትዕግስት ዳልጋ ወደ ግብ በጥሩ ሁኔታ መትታ መክኖባታል። በእነዚህ ሁለት ጥሩ ጥሩ አጋጣሚዎች ጥቃት መሰንዘራቸውን ያላቆሙት ፋሲሎች በ60ኛው ደቂቃ እጅግ የሚያስቆጭ እድል አምልጣቸዋል። በዚህ ደቂቃ ቤተልሄም አምሳሉ በግራ መስመር ያገኘችውን ኳስ እየገፋች ሄዳ ወደ ግብ ስትሞክረው የግቡ አግዳሚ መልሶባታል።

በዚህኛው አጋማሽ ጉልበታቸው የከዳቸው ባህር ዳሮች የፋሲልን ጥቃት መመከት ላይ ተጠምደው ታይተዋል። በአጋማሹም የመጀመሪያ ሙከራ በ70ኛው ደቂቃ በትዕግስት አማካኝነት ሰንዝረው መክኖባቸዋል። ወደ ጨዋታው ለመመለስ እጅግ ፈልገው የተንቀሳቀሱት ፋሲሎች ጨዋታው በእንቅስቃሴ የበላይነት ቀጥለዋል። በ80ኛው ደቂቃም ቡድኑ በቤተልሄም የርቀት ኳስ ግብ ለማስቆጠር ሞክሮ መክኖበታል። የጨዋታው ሙሉ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ ጭማሪ ደቂቃዎች በሚታዩበት ቅስበትም ቡድኑ ግብ አስቆጥሮ የግቡን ልዩነት አጥቧል። ቤተልሄም አምሳሉ ከተከላካዮች መሃል ፈጥና በመውጣት ያገኘችውን ኳስ እየገፋች ሄዳ መረብ ላይ አሳርፋለች። በጨዋታው መገባደጃ ላይ ግብ ያስቆጠሩት ፋሲሎች ከጨዋታው አንድ ነጥብ ይዘው ለመውጣት ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ቀርቶ በባህር ዳር ከተማ 2-1 ተሸንፈው ወጥተዋል።

ዛሬ በተደረጉት ሌሎች ጨዋታዎች ለገጣፎ ላይ ለገጣፎ ለገዳዲ ከ ጥሩነሽ ዲባባ እንዲሁም ወጣቶች አካዳሚ ከ ሻሸመኔ ከተማ በተመሳሳይ 1-1 ሲለያዩ ትላንት በተደረጉ ጨዋታዎች ቦሌ ንፋስ ስልክን 3-0፤ ልደታ ቂርቆስን 3-1 አሸንፈዋል።

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ