የአሰልጣኞች አስተያየት | መቐለ 70 እንደርታ 0-2 ፋሲል ከነማ

በ13ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በትግራይ ስታዲየም ተጠባቂው የመቐለ 70 እንደርታ እና የፋሲል ከነማ ጨዋታ በፋሲል ከነማ 2-0 አሸናፊነት ከተጠናቀቀ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች እንደሚከተለው አስተያየተቻውን ሰጥተዋል ።

“የያዝነውን ውጤት እንዳናጣ በሚል በተጫዋቾች ላይ ትልቅ ጫና ስለነበር ውጤት መያዛችን ትልቅ ነገር ነው” ሥዩም ከበደ (ፋሲል ከነማ)

ስለ ጨዋታው

የመጀመርያ የሜዳ ውጪ ድላችንን አሳክተናል። ሜዳችን ላይ ስድስት ጨዋታ አድርገን ስድስቱንም አሸንፈናል። ከሜዳ ውጭ ያደረግናቸው ጨዋታዎች ላይ ግን አንዳንዱ ላይ ጥሩ እየሄድን የተበላሸብን ጨዋታዎች አሉ። ከነዚህም ውስጥ ከሰበታ ከነማ እና ጅማ አባጅፋር ያደረግናቸውን መጥቀስ ይቻላል። ሰበታ ላይ አራት ደቂቃ ሲቀር ነው አቻ የወጣነው። ከዚህ ሽረ ጋር ደግሞ ከ86ኛ ደቂቃ በኋላ ነው ሁለት ግብ የገባብን። በተመሳሳይ በዛሬውም ጨዋታ የያዝነውን ውጤት እንዳናጣ በሚል በተጫዋቾች ላይ ትልቅ ጫና ስለነበር ውጤት መያዛችን ትልቅ ነገር ነው። መቐለዎች የሚችሉትን ያህል ሞክረዋል። የሚችሉትን ያህል ጫና አድርገዋል። እኛም ያገኘነውን አስጠብቀን ለመሄድ ጥሩ ነገር አድርገናል።

በአንደኛው ዙር ቀሪ አንድ በሜዳችን አለን፤ አንዱ ከሜዳ ውጪ ነው። በነዚህም ጨዋታዎች ውጤት አስጠብቀን መውጣት ማለት ደረጃችን ከፍ አድርገን አንደኛ ዙር መጨረስ እንችላለን። በአጠቃላይ ይሄ ጨዋታ ለኛ ትልቅ ውጤት ነው። ደጋፊዎቻችንም ብዙ ነገር ይሉ የነበረው ከሜዳ ውጭ ባለን አቋም ስለነበር ዛሬ ተሳክቶልናል። በአጠቃለይ ጥሩ ጨዋታ ነው ብዬ አስባለሁ።

ፋሲል ከነማ ላይ ሁለተኛው አጋማሽ ላይ የተከላካይ ክፍተት ይታያል። በግብ ጠባቂ ጥንካሬ እንጂ በርካታ ግቦች ባስተናገደ ነበር…?

አዎ። በተቃራኒው ግን አንዳንድ ጊዜ በበረኛው ምክንያት ያጣናቸው ነጥቦች አሉ። ለምሳሌ ሰበታ እና ሽረ ላይ መጨረሻ ደቂቃ ላይ የገባበት ግብ ከሱ የሚጠቅ አይደለም። በጣም ጥሩ በረኛ ነው። ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል እናም እነዚህ ስህተቶቹ ትምህርት ሆነውታል። በተለይ ዛሬ እሱ የቡድናችን 50% ነው ማለት እችላለሁ።

ስለ ደጋፊዎች ?

የደጋፊው ድባብ በጣም ጥሩ ነው። በጣም ደስ ይላል። ከዚህ በፊትም አይቸዋለሁ። ግን ዛሬ ስሜታዊ ሆነዋል። ይሄም ደግሞ ኳስ ነው፤ ገና አንደኛ ዙርም አላለቀም። መቐለ ገና የሚመጣ ቡድን ጠንካራ ቡድን ነው። በትዕግሥት መጠበቅ ያስፈልጋል ።

” እንቅስቃሴው ስርዐቱን ጠብቆ በሚሄድበት ሰዓት ነው ግብ የተቆጠረብን” ገብረመድን ኃይሌ (መቐለ 70 እንደርታ)

ሰለ ጨዋታው

እንደ ጨዋታ ስናየው ጨዋታው ጥሩ ነው። እንደ ውጤት ለኛ ጥሩ አይደለም፤ እኛ ጥሩ ሆነን በምንሄድበት እና እንቅስቃሴው ስርዐቱን ጠብቆ በሚሄድበት ሰዓት ነው ግብ የተቆጠረብን። በፋሲል ጥንካሬ ሳይሆን በፈጠርናቸው ጥቃቅን ስህተቶች ግብ ሊያስቆጥሩብን ችለዋል። የመጀመሪያው ግብ ትኩረት የማጣት ችግር ነበር። ሁለተኛው ሙሉ አቅማችንን ተጠቅመን ለማጥቃት በምናደርገበት ወቅት በተገኘ መልሶ ማጥቃት የተገኘ ግብ ነው። የብልጠት ችግር ይታይብን ነበር።

የጨዋታ ፍልስፍናዬን ያልተገበሩልኝ ተጫዋቾች ነበሩ። የፍፁም ቅጣት ምት በምናገኝበት ወቅትም አጋጣሚውን አለመጠቀማችን የፈጠረብን ተፅዕኖ ነበር። አማኑኤል ወደ ጨዋታ መመለስ አልቻለም። እና ሌሎች ነገሮች ተጨማምረው ለሽንፈት ዳርገውናል። ግን ቡድናችን በእንቅስቃሴ ደረጃ ጥሩ ነበር ።

ስለ አጨዋወት ለውጥ

እንግዲህ በዚህ ጨዋታ ላይ እንደ ብልጫችን ብዙ አጋጣሚዎችን አለመፍጠር ነበር። ጥቅጥቅ ብለው በመከላከል የያዙትን ውጤት አስጠብቆ ለመውጣት በመፈለግ ሙሉ አቅማቸው መከላከል ላይ ስለነበሩ እና የሚመጡት ኳሶች ደግሞ አየር ላይ በመሆናቸው ለሚከላከል ቡድን አመቺ ስለነበርና የምንመጣባቸው ወይም የምንሄድባቸው ሰብሮ የመግባት መንገድ የኛ የአየር ላይ ብቻ ስለነበር ስህተቶች ነበሩ። ከዛውጭ ግን ጥሩ ነገር ነበር። ያው እግር ኳስ ላይ ሊያጋጥም የሚችለው ነገር ነው የገጠመን።

© ሶከር ኢትዮጵያ