ቅድመ ዳሰሳ | ሀዋሳ ከተማ ከ ጅማ አባ ጅፋር

በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ ላይ የሚደረገውን የሀዋሳ ከተማ እና የጅማ አባ ጅፋር ጨዋታን እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

በደረጃ ሰንጠረዡ አጋማሽ ላይ የሚገኙት ሀዋሳ ከተማዎች ወደ መቐለ አምርተው በስሑል ሽረ ሦስት ለምንም ከተሸነፉበት ጨዋታ ለማገገም እና ከቅርብ ጊዜ ወዲያ ያገኙትን የሜዳቸው ላይ ጥንካሬ ለማስቀጠል ነገ ጅማን ይገጥማሉ።

የሀዋሳ ከተማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
ተሸነፈ አሸነፈ ተሸነፈ አሸነፈ አቻ

በአሰልጣኝ አዲሴ ካሳ የሚመራው ሀዋሳ እስካሁን በውል የሚከተለው የጨዋታ መንገድ ተለይቶ አልታወቀም። በተለይ ቡድኑ በሜዳው እና ከሜዳው ውጪ የሚጫወትበት መንገድ ፍፁም መለያየቱ የቡድኑን አጨዋወት በግልፅ እንዳይታወቅ አድርጎታል። ነገር ግን በአንፃራዊነት ቡድኑ በሜዳው ሲጫወት የሜዳውን ምቹነት በመጠቀም ኳሶችን በጎንዮሽ እና ወፊት ሲያንሸራሽር ይታያል። ነገም ተጋጣሚው ለኳስ ቁጥጥር ካለው ያነሰ ፍላጎት አንፃር ቡድኑ ኳስን በቁጥጥሩ ስር ሊያደርግ ይችላል። በዋናነት ደግሞ ቡድኑ ጥሩ ጥምረት እያስመለከቱ በሚገኙት ዘላለም እና ሄኖክ አማካኝነት የመሃል ሜደውን የኃይል ሚዛን ወደ ራሱ ሊያደርግ ይችላል።

በእንቅስቃሴ ውስጥ ፈጣን እና ተከላካይ ሰንጣቂ ኳሶችን ወደ ብሩክ አየለ እና ሄኖክ አየለ የሚልኩት ሀዋሳዎች በዚህ አጨዋወት በመጠኑ ተጠቃሚ ሲሆኑ ይታያል። ነገም ይህንን አጨዋወት በማጠናከር የጅማዎችን የኋላ መስመር በተደጋጋሚ ሊጎበኙ ይችላሉ። ነገር ግን ቡድኑ በከፍተኛ ሁኔታ በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎች ሲቸገር ስለሚስተዋል ዋጋ እንዳይከፍል አስግቷል። በተለይ ጅማ ሊከተለው ከሚችለው አጨዋወት አንፃር ቡድኑ ሚዛኑን ጠብቆ ካልተንቀሳቀሰ ችግሮች ውስጥ ሊገባ ይችላል።

ባለሜዳዎቹ እስራኤል እሸቱ እና መስፍን ታፈሰን በጉዳት ምክንያት በነገው ጨዋታ አይጠቀሙም።

የጅማ አባ ጅፋር ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አሸነፈ አቻ አቻ ተሸነፈ ተሸነፈ

በተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች ከሊጉ መሪ ክለቦች ጋር (ሽረ፣ ፋሲል እና መቐለ) የተጫወቱት ጅማ አባጅፋሮች በእነዚህ ከባድ ጨዋታዎች ያሳዩትን ጥንካሬ ለመድገም እና ከተደቀነባቸው የወራጅነት ስጋት ለመላቀቅ 9 ሰዓትን ይጠባበቃሉ።
በጥብቅ የመከላከል አደረጃጀት ጨዋታዎችን እያደረጉ የሚገኙት ጅማዎች ዋነኛ የጨዋታ አላማቸው የተጋጣሚን የጨዋታ መንገድ ማበላሸት እየሆነ መጥቷል። በተለይ ቡድኑ ወደ ራሱ የግብ ክልል በመጠጋት የተጋጣሚን የማጥቃት ምቾት በመረበሽ ከጨዋታው የተሻሉ ነገሮችን ለመያዝ ይጥራል። ነገም ቡድኑ በተመሳሳይ የጨዋታ አቀራረብ ወደ ሜዳ በመግባት ከሜዳው ውጪ በጎ ነገሮችን ይዞ ለመመለስ እንደሚጥር ይገመታል።

ከወገብ በታች ጠጣር ቡድን የገነቡት አሰልጣኝ ጳውሎስ ከወገብ በላይ ግን የፈጠሩት ያልተዋሃደ ጥምረት ቡድኑን በተገደቡ እንቅስቃሴዎች ብቻ (በመልሶ ማጥቃት እና በቆሙ ኳሶች) ተንጠልጥሎ ግቦችን እንዲያገኝ አድርጎታል። በተለይ ቡድኑ የፈጠራ አቅሙ የደከመ በመሆኑ በራሱ መንገድ ጨዋታዎችን መወሰን እየተሳነው ይታያል። ነገር ግን በዚህ የተገደበ አጨዋወት ውስጥ ጎልቶ የሚታየው ኤሊያስ አህመድ በግሉ ለቡድኑ መፍትሄዎችን ለማምጣት ይታትራል። እርግጥ ተጨዋቹ ከሚሰጠው አድካሚ ሃላፊነት (ሜዳውን የማካለል) አንፃር ፍሬያማነቱ የወረደ ቢሆንም ቡድኑን ለመጥቀም የሚያደርገው ጥረት ለሃዋሳዎች አደጋን ይዞ ሊመጣ ይችላል።

ጅማዎች አምረላ ደልታታን ብቻ በጉዳት ምክንያት ሳይዙ ወደ ሀዋሳ አምርተዋል።

እርስ በርስ ግንኙነት

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ አራት ጊዜ ተገናኝተው ሁለቱን ሀዋሳ ሲያሸንፍ አንዱን ጅማ አሸንፎ በቀሪው አቻ ተለያይተዋል። ሀዋሳ 5፤ ጅማ 4 ጎሎችን አስቆጥረዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሀዋሳ ከተማ (4-2-3-1)

ቢሊንጋ ኢኖህ

ዳንኤል ደርቤ – መሳይ ጳውሎስ – ላውረንስ ላርቴ – ያኦ ኦሊቨር

ተስፋዬ መላኩ – አለልኝ አዘነ

ሄኖክ ድልቢ – ዘላለም ኢሳያስ – ሄኖክ አየለ

ብሩክ በየነ

ጅማ አባ ጅፋር (4-2-3-1)

ሰዒድ ሀብታሙ

ወንድማገኝ ማርቆስ – መላኩ ወልዴ – አሌክስ አሙዙ – ጀሚል ያቆብ

ንጋቱ ገ/ሥላሴ – አብርሀም ታምራት

ሱራፌል ዐወል – ኤልያስ አህመድ – ብሩክ ገብረአብ

ብዙዓየሁ እንደሻው

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ