ቅድመ ዳሰሳ | ወልዋሎ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

ቢጫ ለባሾቹ በትግራይ ስታዲየም ፈረሰኞቹን የሚያስተናግዱበትን ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

በ7ኛ ሳምንት የሊጉ መርሃ ግብር ወደ ድሬ አቅንተው ድሬዳዋ ከተማን 2-0 ካሸነፉ በኃላ ላለፉት አምስት ሳምንታት ሙሉ ሦስት ነጥብ ማግኘት ተስኗቸው ወደ ደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ የተንሸራተቱት ወልዋሎዎች ፈረሰኞቹን በሚያስተናግዱበት የነገ ጨዋታ ወደ አሸናፊነት መንገድ መመለስ የግድ ይላቸዋል።

የወልዋሎ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
ተሸነፈ ተሸነፈ አቻ ተሸነፈ ተሸነፈ

በርካታ ወሳኝ ተጫዋቾቻቸውን በጉዳት ያጡት ቢጫ ለባሾቹ በነገው ጨዋታም በተመሳሳይ በጉዳት ላይ ያሉ ተጫዋቾቻቸው ግልጋሎት አያገኙም። በውድድር ዓመቱ መጀመርያ በቀጥተኛ አጨዋወት ጥሩ የሚባል የአጥቂ ጥምረት ፈጥረው የነበሩት ወልዋሎዎች ከጨዋታ ጨዋታ ባሳዩት የብቃት መውረድ እና የተጫዋቾች ጉዳት ጉዟቸውን ከባድ ሆኖባቸዋል። ከዚህ በተጨማሪ የቡድኑ ተገማች አቀራረብ እና ጠባብ የተጫዋቾች አማራጭ ለውጤቱ መጥፋት እንደ ምክንያትነት ቢጠቀሱም የቡድኑ ተገማች የማጥቃት አጨዋወት ግን እንደ ዋነኛ ምክንያት ማስቀመጥ ይቻላል። በተለይም ቡድኑ በሜዳው ነጥብ የጣለባቸው ጨዋታዎች በተጠቀሰው ምክንያት መነሻነት የመጡ ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪ በሊጉ መጀመርያ ላይ የሚገኙትን ጥቂት የግብ ዕድሎች ወደ ግብነት በመቀየር ውጤታማ የነበረው የቡድኑ የአጥቂ ክፍል ከግብ ማስቆጠር መራቁ እና የቡድኑ ተከላካይ ክፍል በጉዳት መሳሳቱ በቡድኑ ውጤት መራቅ የራሳቸው ድርሻ አላቸው።

ወልዋሎዎች በነገው ጨዋታ በአቀራረብም ሆነ በተጫዋቾች ምርጫ ረገድም ለውጦች ያደርጋሉ ተብሎ አይጠበቅም። ሆኖም ግን ቡድኑ በጥሩ ወቅታዊ ብቃት የሚገኙትን የቅዱስ ግዮርጊስ አጥቂዎች ለመከላከል ከመቼውም ጊዜ በላይ ጠንክሮ መቅረብ የግድ ይለዋል።

ወልዋሎዎች በነገው ጨዋታ ዓብዱልዓዚዝ ኬይታ ፣ ዓይናለም ሀይሉ ፣ ፍቃዱ ደነቀ እና ካርሎስ ዳምጠውን በጉዳት ምክንያት ሲያጡ የሰመረ ሀፍታይ መሰለፍም አጠራጣሪ ነው ተብሏል።

የቅዱስ ጊዮርጊስ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አሸነፈ አሸነፈ አሸነፈ አቻ አሸነፈ

ከጊዜ ወደ ጊዜ አስፈሪ የማጥቃት ጥምረት ያለውን ቡድን መገንባት የቻሉት ፈረሰኞቹ የሊጉን መሪነት በተረከቡበት ማግስት መሪነታቸውን ለማስጠበቅ ወደ መቐለ ተጉዘዋል።
ባለፉት ሁለት ሳምንታት በብዙ ረገድ ማሻሻሎች ያሳዩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከጥሩ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴዎቻቸው በተጨማሪ ከዚህ በፊት ይታይባቸው የነበረውን የተነሳሽነት ችግር በማስተካከል ወደ ጥሩ የማሸነፍ መንገድ መጥተዋል። ሆኖም ግን በዚህ የውድድር ዓመት ከሜዳው ውጭ ሶስት ነጥብ ይዞ መመለስ ያልቻለው ቡድኑ ከሜዳው ውጭ ያለውን ክብረ ወሰን እንደ ሜዳው ላይ ጨዋታዎች ማስተካከል አልቻለም።

ባለፈው ጨዋታ ሲዳማ ቡናን በሰፊ የግብ ልዩነት ማሸነፍ የቻሉት ፈረሰኞቹ በሂደት በፊት መስመር ላይ የፈጠሩት የሰመረ ጥምረት እና አቀራረብ በነገው ጨዋታም ይዘው ይገባሉ ተብሎ ይታመናል። በዚህም የአቤል ያለው እና የጌታነህ ከበደ የማጥቃት ጥምረት በነገው የቡድኑ አጨዋወት ወሳኝ ሚና ሊኖረው ይችላል ተብሎ ይጠበቃል።

ፈረሰኞቹ በነገው ጨዋታ የሳልሀዲን ስዒድ ፣ ናትናኤል ዘለቀ ፣ አስቻለው ታመነ እና ለዓለም ብርሃኑን ግልጋሎት አያገኙም።

እርስ በርስ ግንኙነት

በሊጉ ለሦስት ጊዜያት ሲገናኙ ዐምና በሁለተኛው ዙር ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ ሳይከናወን ቀርቷል። በግንኙነቶቹ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሁለቱን ሲያሸንፍ አንድ አቻ ተለያይተዋል። ፈረሰኞቹ 2 ሲያስቆጥሩ ቢጫ ለባሾቹ ምንም አላስቆጠሩም።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወልዋሎ (4-2-3-1)

ጃፋር ደሊል

ምስጋና ወልደዮሐንስ – አቼምፖንግ አሞስ – ዳዊት ወርቁ – ሄኖክ መርሹ

ገናናው ረጋሳ – ሳሙኤል ዮሐንስ

ብሩክ ሰሙ – ራምኬል ሎክ – ኢታሙና ኬይሙኔ

ጁንያስ ናንጂቡ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-3-3)

ፓትሪክ ማታሲ

ደስታ ደሙ – ኤድዊን ፍሪምፖንግ – ምንተስኖት አዳነ – ሄኖክ አዱኛ

የአብስራ ተስፋዬ – ሙሉዓለም መስፍን – ሀይደር ሸረፋ

ጋዲሳ መብራቴ – ጌታነህ ከበደ – አቤል ያለው

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ