ቅድመ ዳሰሳ | ባህር ዳር ከተማ ከ ሰበታ ከተማ

በእኩል ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ሰባተኛ እና ስድስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ባህር ዳር ከተማ እና ሰበታ ከተማ የሚያደርጉትን የነገ ጨዋታ እንደሚከተለው ተመልክተነዋል።

በሜዳቸው ላይ የሚደረግ ጨዋታን ብቻ እያሸነፉ የሚገኙት ባህር ዳር ከተማዎች ወልቂጤ ላይ ከደረሰባቸው ሽንፈት ለማገገም እና ከመሪዎቹ ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ ወደ ሜዳ ይገባሉ።

የባህር ዳር ከተማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
ተሸነፈ አሸነፈ ተሸነፈ አሸነፈ ተሸነፈ

በአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የሚመራው ቡድኑ አሁን አሁን በየጨዋታዎቹ እያሳየ የሚገኘው የጨዋታ አቀራረብ እየተቀያየረ መጥቷል። እርግጥ ቡድኑ (በተለይ በሜዳው ሲጫወት) ኳስን መቆጣጠር ዋነኛ አላማው ቢመስልም ፈጣን የመስመር ላይ ሽግግሮችን እና ተሻጋሪ ኳሶችን በመጠቀም ፍሬያማ ለመሆን ይጥራል። በነገውም ጨዋታ ቡድኑ በተመሳሳይ የሰሞንኛ አቀራረቡ ሊቀርብ እንደሚችል ይገመታል። በዋናነት ግን ተጋጣሚው ሰበታ ከተማ ሊከተል ከሚችለው የጨዋታ አቀራረብ መነሻነት ቡድኑ ነገ ቀጥተኝነትን ሊመርጥ ይችላል።

በግራ መስመር በኩል በይበልጥ አጋድሎ ጥቃቶችን በፈጣን ሽግግር የሚሰነዝረው ቡድኑ ነገም በዚህ መስመር ስል ሆኖ ወደ ሜዳ ሊገባ ይችላል። ከዚህ ውጪ ከጉዳት አገግሞ የተመለሰው ፍፁም ዓለሙ ለቡድኑ የፊት መስመር ጥሩ ብርታት ይለግሳል ተብሎ ይጠበቃል። በተለይ ተጨዋቹ በነፃ ሚና የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች የተጋጣሚን የኋላ መስመር ወደ ኋላ ሲጎትት ይታያል። ከዚህ የተነሳ ሰበታዎች እንደ ከዚህ ቀደሞቹ ጨዋታዎች የተከላካይ መስመራቸውን ወደ ፊት ላያስጠጉ ይችላሉ። ይህ ደግሞ የቡድኑን (ሰበታ) የኳስ ፍሰት ሊቀንስ እንዲሁም ከተከላካይ እስከ አጥቂ ያለውን ስፋት ሊያረዝም ይችላል።

ከፍተኛ ግብ የማስተናገድ አባዜ ያለበት ባህር ዳር ነገም ይህ የኋላ መስመሩ ችግር ላይ እንዳይጥለው አስግቷል። በተለይ ቡድኑ ከማጥቃት ወደ መከላከል በሚያደርገው የዘገየ የሽግግር ጊዜ ስህተቶች ግቦችን ያስተናግዳል። ስለዚህ ነገም ቡድኑ በዚህ ችግሩ ሊፈተን ይችላል።

በጉዳት እየታመሰ የሚገኘው ባህር ዳር አሁንም ወሳኝ ተጨዋቾቹን ሙሉ ለሙሉ አላገኘም። ማማዱ ሲዲቤ፣ አዳማ ሲሶኮ፣ ወሰኑ ዓሊ፣ ፍቅረሚካኤል ዓለሙ እና ሳላምላክ ተገኝ ከጉዳታቸው ባለማገገማቸው ከስብስቡ ውጪ ሆነዋል። በተጨማሪም የወጣቱ አጥቁ ስንታየሁ መንግስቱም ወደ ሜዳ መግባት አጠራጣሪ ነው ተብሏል። ነገር ግን አቤል ውዱ እና ፍፁም ዓለሙ ከጉዳታቸው በማገገማቸው ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው። ከዚህ ውጪ በ10ኛ ሳምንት የሊጉ መርሃ ግብር ቀይ ካርድ ያየው(ከጨዋታው መጀመር በፊት) የሃሪሰን ሄሱ ጉዳይ ውዝግብ ፈጥሯል። ተጨዋቹ በእለቱ የቀይ ካርድ ቢያይም ተጨማሪ ቅጣት ይጣልበት አይጣልበት በትክክል በፌደሬሽኑ ባለመረጋገጡ በነገው ጨዋታ መሰለፉ አጠራጥሯል። ነገር ግን ከክለቡ ስራ አስኪያጅ ባገኘነው መረጃ ፌደሬሽኑ ምንም የውሳኔ ደብዳቤ በይፋ ለክለቡ ባለመላኩ ነገ ተጨዋቹ ሊሰለፍ ይችላል ተብሏል።

የሰበታ ከተማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አሸነፈ ተሸነፈ አሸነፈ ተሸነፈ አሸነፈ

እንደ ተጋጣሚያቸው ባህር ዳር ከተማ ሁሉ ከሜዳቸው ውጪ ጨዋታ ማሸነፍ የሚከብዳቸው ሰበታዎች ታህሳስ 11 ወልቂጤ ላይ ያስመዘገቡትን ብቸኛ የዓመቱን የሜዳ ውጪ ድል ለመድገም እና በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ለመቆየት ነገን ይጠባበቃሉ።

አጀማመራቸው ብዙም አመርቂ ያልነበረው ሰበታዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ውጤት እያስመዘገቡ በጥሩ ግስጋሴ ጨዋታዎችን እያደረጉ ይገኛሉ። በተለይ በሜዳቸው ላይ የሚደረጉ ጨዋታዎችን (በአዲስ አበባ ስታዲየም መሆኑ ሳይዘነጋ) በማሸነፍ ወደ ደረጃ ሰንጠረዡ አናት ተጠግተዋል። ለዚህ ደግሞ በዋናነት ለቡድኑ 6 ጎሎችን ያስቆጠረው ፍፁም ገ/ማርያም የቡድኑን ጉዞ ከፊት እየመራ ይገኛል። በተለይ ተጨዋቹ የሚያስቆጥራቸው ወሳኝ ጎሎች ቡድኑን ሲጠቅሙ ይታያል። ነገም ተጨዋቹ እንደለመደው የቡድኑ የብዙ ነገር መፍትሄ ሊሆን ይችላል።

በርከት ባሉ ጨዋታዎች ለኳስ ቁጥጥር ቅድሚያ በመስጠት ሲጫወቱ የነበሩት ሰበታዎች ነገም ከባህር ዳር ስታዲየም ምቹነት አንፃር አላማቸውን በቀላሉ ይተገብራሉ ተብሎ ይጠበቃል። በተለይ ቡድኑ በሶስት የአማካኝ ተጨዋቾች ጥምረት በመታገዝ በቀላሉ የኳስ ፍሰቱን ለማፋጠን ይጥራል። ከዚህ ውጪ ቡድኑ በአንዳንድ አጋጣሚዎች የሚጠቀማቸው ቀጥተኛ አጨዋወቶች ፍሬያማ ሲያደርጉት ይታያል። በዚህም ፍፁምን ያነጣጠሩ የአየር ላይ ኳሶች በግራ እና በቀኝ መስመር በመላክ የተጋጣሚን ጊዜ ከባድ ለማድረግ ሊጥሩ ይችላል።

ተጋጣሚ ቡድን ላይ ካገባው 14 ጎል እኩል ግብ ያስተናገደው ቡድኑ እንደ ባህር ዳር ሁሉ ያለው የተከላካይ መስመር የራስ ምታት ሆኖበታል። እርግጥ ለረጅም ጊዜ ጉዳት አስተናግዶ የነበረው አንተነህ ተስፋዬ ከጉዳቱ ማገገሙ ለተከላካይ መስመሩ ጥሩ ዜና ቢሆንም ቡድኑ እንደ ቡድን ያለው የመከላከል መዋቅር ችግሮች ይስተዋሉበታል። ነገም አሰልጣኝ ውበቱ ይህንን የመከላከል አደረጃጀት በአግባቡ ለመጠገን መፍትሄዎችን ካላዘጋጁ በሜዳቸው እጅግ ጠንካራ ለሆኑት ባህር ዳሮች እጅ ሊሰጡ ይችላሉ።

በቡድኑ በኩል አዲሱ ተስፋዬ ከቅጣት ሲመለስ አስቻለው ግርማ፣ ዳዊት እስጢፋኖስ እና በሀይሉ አሰፋ በጉዳት ምክንያት ወደ ባህር ዳር እንዳልተጓዙ ተሰምቷል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ባህር ዳር ከተማ (4-3-3)

ፅዮን መርዕድ

ሚኪያስ ግርማ – ሰለሞን ወዴሳ – አቤል ውዱ – ሳሙኤል ተስፋዬ

ሳምሶን ጥለሁን – ዳንኤል ኃይሉ – ፍፁም ዓለሙ

ግርማ ዲሳሳ – ስንታየሁ መንግስቱ – ፍቃዱ ወርቁ

ሰበታ ከተማ (4-3-3)

ዳንኤል አጃይ

ጌቱ ኃ/ማርያም – አንተነህ ተስፋዬ – አዲስ ተስፋዬ – ኃ/ሚካኤል አደፍርስ

ደሳለኝ ደባሽ – መስዑድ መሐመድ – ታደለ መንገሻ

ናትናኤል ጋንቹላ – ፍፁም ገ/ማርያም – ባኑ ዲያዋራ

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ