ብርቱካናማዎቹ በጥሩ መነቃቃት የሚገኙት ስሑል ሽረዎችን የሚያስተናግዱበት ጨዋታን እንደሚከተለው ዳሰነዋል።
ባለፈው ሳምንት ዋና አሰልጣኙ ስምዖን ዓባይን ያሰናበቱት ብርቱካናማዎቹ በአዲሱ ጊዜያዊ አሰልጣኝ እየተመሩ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት አልመው ወደ ሜዳ ይገባሉ።
የድሬዳዋ ከተማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ) | ||||
ተሸነፈ | አሸነፈ | ተሸነፈ | አሸነፈ | ተሸነፈ |
ባለፉት ጨዋታዎች አጥቂዎቹ ላይ ባነጣጠሩ ረጃጅም እና ቀጥተኛ ኳሶች የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ያደረጉት ድሬዳዋ ከተማዎች በአዲሱ አሰልጣኝ እየተመሩ ይዘውት የሚቀርቡት አጨዋወት ለመገመት ቢከብድ ከባለፉት ሳምንታት ብዙም ልዩነት ያለው አጨዋወት ይሆናል ተብሎ አይጠበቅም። በዚህም ቡድኑ ከአማካዮቹ በሚነሱ ረጃጅም ኳስ ከሬችሞንድ አዶንጎ እና በሙህዲን ሙሳ ጥምረት ግብ ለማግኘት አልሞ ወደ ሜዳ ይገባል ተብሎ ይገመታል።
ከዚህ በተጨማሪ ቡድኑ የተጋጣሚን የመስመር እና የመልሶ ማጥቃት አጨዋወትን ለመመከት በኋላ መስመር ላይ የተለየ አቀራረብ ይዞ መቅረቡ አይቀሬ ነው። በዚህም በሁለት የተከላካይ አማካዮች ጥምረት የሽረን የመስመር ላይ ፈጣን መልሶ ለመግታት ጥረት እንደሚያደርግ ይጠበቃል።
ብርቱካናማዎቹ በነገው ጨዋታ ረመዳን ናስር ፣ ምንያህል ተሾመ እና ያሬድ ታደሰን በጉዳት አየሰልፉም። የበረከት ሳሙኤል መሰለፍም አጠራጣሪ ነው።
የስሑል ሽረ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ) | ||||
አሸነፈ | ተሸነፈ | አቻ | አሸነፈ | አሸነፈ |
ከተከታታይ ሽንፈት አልባ ጨዋታዎች በኋላ በመቐለ ሽንፈት ገጥሟቸው ባለፈው ሳምንት ሀዋሳ ከተማን በማሸነፍ ወደ አሸናፊነት የተመለሱት ሽረዎች በአንፃራዊነት ከሌሎች ክለቦች ጋር ሲነፃፀር ከሜዳቸው ውጭ ያላቸውን ጥሩ ክብረ ወሰን ለማስቀጠል ወደ ድሬ አምርተዋል።
ለመጨረሻ ጊዜ ከሜዳቸው ውጭ ባደረጓቸው ጨዋታዎች በአሉታዊ አቀራረብ ነጥብ ይዘው የተመለሱት ስሑል ሽረዎች ከባለፉት የሜዳ ውጭ ጨዋታዎች ለየት ባለ አቀራረብ ወደ ጨዋታው ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል። ከቅርብ ጨዋታዎች በፊት ስል የመልሶ ማጥቃት ቡድን የሰሩት አሰልጣኝ ሳምሶን አየለ በነገው ጨዋታ ከመልሶ ማጥቃት አጨዋወታቸው ወጣ ያለ አቀራረብ ይኖራቸዋል ተብሎ አይጠበቅም።
ሆኖም ባለፉት ጨዋታዎች በአጨዋወቱ ወሳኝ ሚና የነበረው ዲዲዬ ለብሪን በቅጣት ያጣው ቡድኑ በቦታው ሁነኛ ተተኪ ይዞ ካልገባ እንደ ባለፈው ሳምንት ጨዋታ አጨዋወቱ በዓብዱለጢፍ መሐመድ ብቻ የተንጠለጠለ እንዳይሆን ያሰጋል።
በዚህም ቡድኑ በሁለቱም መስመሮች በሚዛናዊነት አጨዋወቱን መተግበር የሚችሉ ተጫዋቾች ይዞ መግባት የግድ ይለዋል።
ከዚ በተጨማሪ ቡድኑ በጥሩ ወቅታዊ ብቃት የሚገኘው ዮናስ ግርማይ በጉዳት ማጣቱ ከበርካታ ጨዋታዎች በኃላ ዋና አምበሉ በረከት ተሰማ በቋሚነት ጨዋታውን ይጀምራል ተብሎ ይገመታል።
በነገው ጨዋታ ወደ ቱርክ ከተጓዘው ምንተስኖት አሎ በተጨማሪ ዮናስ ግርማይ በጉዳት ቡድኑን አያገለግልም። በቅጣት ላይ የሚገኘው ዲዲዬ ለብሪም ወደ ድሬ ያልተጓዘ ሌላው ተጫዋች ነው።
እርስ በርስ ግንኙነት
እስካሁን 2 ጊዜ (ዐምና) ተገናኝተው ሁለቱንም በአቻ ውጤት ጨዋታቸውን ፈፅመዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ድራዳዋ ከተማ (4-2-3-1)
ሳምሶን አሰፋ
ፍሬዘር ካሳ – ያሬድ ዘውድነህ – ዘሪሁን አንሼቦ – ያሲን ጀማል
ፍሬድ ሙሸንዲ – አማኑኤል ተሾመ
ያሬድ ታደሰ – ኤልያስ ማሞ – ሙህዲን ሙሳ
ሬችሞንድ አዶንጎ –
ስሑል ሽረ (4-2-3-1)
ወንድወሰን አሸናፊ
ዐወት ገብረሚካኤል – በረከት ተሰማ – አዳም ማሳላቺ – ረመዳን የሱፍ
ሀብታሙ ሽዋለም – ነፃነት ገብረመድህን
ብሩክ ሐድሽ – ያሳር ሙገርዋ – ዓብዱለጢፍ መሐመድ
ሳሊፍ ፎፋና
© ሶከር ኢትዮጵያ