በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የምድብ ሐ አንድ ጨዋታ ዛሬ ሀዋሳ ላይ ተደርጎ ደቡብ ፓሊስ ተቸግሮም ቢሆን ቂርቆስ ክፍለ ከተማን 2ለ1 አሸንፏል፡፡
አሰልቺ በነበረው እና ለዕይታ ፍፁም ማራኪ ባልነበረው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ደቡብ ፖሊሶች ረጃጅም ወደ መስመር አልያም ደግሞ ወደ አጥቂ መስመሩ ከሚሻገሩ ኳሶች ለማጥቃት ቢሞክሩም ኳሶቹ ስኬታማ ሆነው ለውጤት የሚያበቁ ሳይሆኑ አብዛኛዎቹ ብኩኖች ሲሆኑ እንግዳው ቡድን የተጋጣሚውን እንቅስቃሴ በሚገባ እየተከታተለ ለስህተት የተጋለጠውን የተከላካይ ክፍል ለማስጨንቅ አልተቸገሩም፡፡
4ኛው ደቂቃ ምትኩ ማመጫ መሀል ለመሀል በተከላካዮች እግር ስር አሾልኮ የሰጠውን ኳስ ሁለት ጊዜ ወደ ሳጥኑ ገፋ በማድረግ የኃላሸት ሰለሞን ወደ ግብነት ቀይሯት ደቡብ ፖሊስን መሪ አድርጓል፡፡ ከግቧ በኃላ ቢጫ ለባሾቹ ተጭነው በመጫወት አስከፍተው ወደ ሳጥን ለመግባት በተለይ በቀኝ በኩል በተሰለፈው ያሬድ መሀመድ፣ ብሩክ ኤልያስ እና የኃላሸት ሰለሞን አማካኝነት ጥረት ቢያደርጉም ተጫዋቾቹ በቀላሉ ወደ ግብነት መለወጥ እየቻሉ በግድ የለሽነት በተደጋጋሚ አምክነውታል፡፡
የፖሊስን ክፍተት በመረዳት ከግብ ክልላቸው በፍጥነት ወጥጦ ጫናን መፍጠር የቻሉት ቂርቆሶች በደቡብ ፖሊስ ተጫዋቾች አቋቋም ስህተት ግብ አግብተዋል፡፡ 14ኛው ደቂቃ ሙባረክ ከድር የሰጠውን ኳስ ልዑል ኃይለጊዮርጊስ ብስለቱን በሚገባ ያሳየበትን ግብ ከተከላካዮች መሀል ሾልኮ ወጥቶ በማስቆጠር አቻ አድርጓቸዋል፡፡ ግብ ለማስተናገድ የተገደዱት ፖሊሶች መሪ ለመሆን በተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርጉም ወደ ግብነት ለመለወጥ በደንብ ተቸግረዋል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ አሁንም ተመሳሳይ አሰልቺ የሆነ እንቅስቃሴን ያየን ሲሆን ከመሀል ብልጭ ብለው ከሚጠፉ የነጠሩ አጋጣሚዎች ውጪ የጎሉ ሳቢ ነገሮች አላየንበትም፡፡ ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ወደ ግብ በመድረሱ ከባለሜዳው ይልቅ ቂርቆሶች ሻል ብለው ቀርበዋል፡፡ በአንፃሩ በሂደት ወደ መሪነት ለመሸጋገር የታተሩት ፖሊሶች ኤሪክ ሙራንዳን ቀይረው ካስገቡ በኃላ የሚገኙ ኳሶችን በአግባቡ ለመጠቀም በተወሰነ መልኩ ቢሞክሩም ብዙዎቹ ፍርያማ አልነበሩም፡፡
ደቂቃዎች እየገፉ ሲመጡ ቂርቆሶች ያለቀላቸውን ዕድሎች አግኝተው አልተጠቀሙም። በተለይ ቢኒያም ገሰሰ ያመከናቸው የማይታመኑ ሁለት ኳሶች ቡድኑን ዕድለኛ አላደረጉትም እንጂ እጅግ ለግብ የቀረቡ ነበሩ፡፡ በሌላ በኩል ቢጫ ለባሾቹ በበብሩክ ኤልያስ፣ ያሬድ እና የኃላሸት ግብ ለማግኘት ጥረታቸውን ቀጥለዋል፡፡ 85ኛው ደቂቃ ላይእ የቂርቆስ ተከላካዮችን መዘናጋት ተከትሎ ከቀኝ በኩል ሲሻገር የኃላሸት አመቻችቶ ሰጥቶት ኤሪክ ሙራንዳ ወደ ግብነት ለውጧት ዳግም ቡድኑ መሪ አድርጓል፡፡ እስከ ጭማሪ ደቂቃው ድረስ ቂርቆሶች ብልጫን ወስደው ግብ ለማስቆጠር ቢታገሉም ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠር 2ለ1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል፡፡
የዘጠነኛ ሳምንት ጨዋታዎች
ምድብ ሀ | ||
እሁድ የካቲት 1 ቀን 2012 | ||
ፌዴራል ፖሊስ | 9:00 | ለገጣፎ ለገዳዲ |
ኢትዮ ኤሌክትሪክ | 9:00 | አክሱም ከተማ |
ወሎ ኮምቦልቻ | 9:00 | ወልዲያ |
ሶሎዳ ዓድዋ | 9:00 | ሰ/ሸ/ደ/ብርሃን |
ሰኞ የካቲት 2 ቀን 2012 | ||
ደደቢት | 7:00 | ደሴ ከተማ |
አቃቂ ቃሊቲ | 9:00 | ገላን ከተማ |
ምድብ ለ | ||
እሁድ የካቲት 1 ቀን 2012 | ||
ነቀምቴ ከተማ | 9:00 | ሀምበሪቾ ዱራሜ |
ጅማ አባ ቡና | 9:00 | ሻሸመኔ ከተማ |
ሰኞ የካቲት 2 ቀን 2012 | ||
ኢኮሥኮ | 7:00 | አዲስ አበባ ከተማ |
ጋሞ ጨንቻ | 9:00 | ቤንች ማጂ ቡና |
ማክሰኞ የካቲት 3 ቀን 2012 | ||
ሀላባ ከተማ | 9:00 | ካፋ ቡና |
መከላከያ | 9:00 | ወላይታ ሶዶ |
ምድብ ሐ | ||
ቅዳሜ ጥር 30 ቀን 2012 | ||
ደቡብ ፖሊስ | 2-1 | ቂርቆስ ክ/ከተማ |
እሁድ የካቲት 1 ቀን 2012 | ||
ነገሌ አርሲ | 9:00 | ኢት. መድን |
ጌዴኦ ዲላ | 9:00 | ኮልፌ ቀራኒዮ |
ስልጤ ወራቤ | 9:00 | የካ ክ/ከተማ |
ባቱ ከተማ | 9:00 | አርባምንጭ ከተማ |
ከምባታ ሺንሺቾ | 9:00 | ቡታጅራ ከተማ |
© ሶከር ኢትዮጵያ