በ3ኛ ቀን የ13ኛ ሳምንት የሊጉ መርሃ ግብር የሚደረገው የሲዳማ ቡና እና የአዳማ ከተማ ጨዋታን እንደሚከተለው ተመልክተነዋል።
አዲስ አበባ ላይ በቅዱስ ጊዮርጊስ አሰቃቂ ሽንፈት ያስተናገዱት ሲዳማ ቡናዎች ከደረሰባቸው ሽንፈት ለማገገም እና በተከታታይ ሁለት የሜዳ ላይ ጨዋታቸው ያገኙትን ድል ለመድገም 9 ሰዓትን ይጠባበቃሉ።
የሲዳማ ቡና ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ) | ||||
ተሸነፈ | አሸነፈ | ተሸነፈ | ተሸነፈ | አሸነፈ |
እስካሁን ምንም ጨዋታ አቻ ያልወጣው ቡድኑ (በሊጉ ብቸኛው ነው) የሚያደርገው የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ተጋጣሚን ሰከረብሽ ይታያል። በተለይ ቡድኑ በአብዛኛው ጨዋታዎች ላይ በአጥቂዎቹ ፍጥነት፣ ቅልጥፍና እና ታታሪነት ታግዞ የተጋጣሚን የተከላካይ መስመር ለመጫን ይሞክራል። ነገር ግን ይህ የቡድኑ በጎ ጎን በአንዳንድ ጨዋታዎች ላይ ፍሬያማ ሲሆን በአንዳንድ ጨዋታዎች ላይ ደግሞ መባከንን ብቻ ይዞ ሲመጣ ይስተዋላል። ቢሆንም ግን ነገ ቡድኑ በሜዳው እንደመጫወቱ ጨዋታውን ለማሸነፍ እንቅስቃሴዎቹን በፍጥነት አጅቦ ወደ ሜዳ ሊገባ እንደሚችል ይገመታል።
ፊት መስመር ላይ ከሚሰለፉት ሀብታሙ፣ አዲሰ እና ይገዙ ፈጣን እንቅስቃሴ በተጨማሪ ቡድኑ በአማካኝ መስመር ተጨዋቾቹ ታታሪነት እድሎችን ሲፈጥር ይታያል። በዚህም ነገ ቡድኑ በተለይ በአበባየሁ ተከላካይ ሰንጣቂ ኳሶች አዳማዎችን ሊፈትኑ ይችላሉ። ከአበባየሁ በተጨማሪ ባሳለፍነው ሳምንት ድንቅ ጎል ጊዮርጊስ ላይ ያስቆጠረው ዮሴፍ ዮሐንስ ወደ መስመር የሚልካቸው ኳሶች ጠጣሩን የአዳማ የተከላካይ ክፍል ሊበታትን ይችላል። በዚህ እንቅስቃሴ ደግሞ በተከላካዮች መካከል በመገኘት ግቦችን ለማግባት ተዘጋጅተው የሚጠብቁት የሲዳማ ቡና አጥቂዎች ምቹ አጋጣሚ ሊፈጠርላቸው ይችላል።
በሊጉ ሁለተኛው ብዙ ጎል ያስተናገደው ሲዳማ ቡና (22) አሁንም የተከላካይ መስመሩ አለመረጋጋት ዋጋ እያስከፈለው ይገኛል። በተለይ ከፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ወደ መከላከል በሚደረጉ ሽግግሮች የሚሰሯቸው ስህተቶች ቡድኑን እጅ እንዲሰጥ ያደርጉታል። ስለዚህ ነገ ቡድኑ የመከላከል ቅርፁን በሚገባ አሻሽሎ ካልቀረበ በአዳማ የወገብ በላይ ተጨዋቾች ሊቀጣ ይችላል።
ባለሜዳዎቹ ሚሊዮን ሰለሞንን እና መሳይ አያኖን በጉዳት ምክንያት በነገው ጨዋታ አያገኙም።
የአዳማ ከተማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ) | ||||
አሸነፈ | ተሸነፈ | አሸነፈ | ተሸነፈ | አቻ |
ባሳለፍነው ሳምንት በሜዳቸው ኢትዮጵያ ቡና ላይ ሦስት ጎል እና ሦስት ነጥብ ያስመዘገቡት አዳማዎች የመጀመሪያ የሜዳ ውጪ ድል ለማግኘት ሀዋሳ ገብተዋል።
ከደሞዝ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የሜዳ ውጪ ጥያቄዎች በዝተውበት የከረመው ቡድኑ አሁንም ወጣ ገባ አቋሙን ማሳየት ቀጥሏል። እርግጥ ቡድኑ ባሳለፍነው ሳምንት በሜዳው ሲጫወት ፍጥነት ላይ የተመረኮዘ አጨዋወት በመተግበር ተጋጣሚን ሲረብሽ ቢስተዋልም የነገ አቀራረቡ ግን ለመገመት ይቸግራል። ምናልባት ግን ቡድኑ ከሜዳው ውጪ እንደመጫወቱ ወደ ኋላ በማፈግፈግ የሲዳማ ቡናን ክፍተት በማጥናት ጎሎችን ለማስቆጠር እንደሚጥር ይታሰባል።
ከወገብ በላይ ያሉት የቡድኑ ተጨዋቾች አንዳንዴ የሚያሳዩት የሚገርም እንቅስቃሴ ነገ ሲዳማን ችግር ውስጥ ሊከት ይችላል። በተለይ ደግሞ በበረከት አማካኝነት ቡድኑ ብዙ በጎ ነገሮችን ለማምጣት ይጥራል። ስለዚህ ነገም ይህ ተጨዋች ለቡድን አጋሮቹ ከሚያቀብላቸው ቁልፍ ኳሶች ውጪ በመስመሮች መካከል በመገኘት የሚያደርገው አደገኛ እንቅስቃሴ ይጠበቃል።
ከሲዳማ ቡና በተቃራኒ ከፍተኛ የአቻ ውጤቶችን በሊጉ ያስመዘገበው አዳማ (6) ያለው የሜዳ ውጪ አይናፋርነት ነገም ችግሮች ውስጥ እንዳይከቱት አስግቷል። ከዚህ በተጨማሪ ለቡድኑ 5 ግቦችን በ12 የሊጉ ጨዋታዎች ያስቆጠረው ዳዋ ሆቴሳ አለመኖር ሊፈትነው ይችላል።
አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ዳዋ ሆቴሳ እና ከነዓን ማርክነህ በጉዳት ምክንያት ሳይዙ ወደ ሀዋሳ እንዳመሩ ተሰምቷል።
እርስ በርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች 18 ጊዜ በሊጉ ተገናኝተው ሲዳማ 7 በማሸነፍ የበላይነቱን ሲይዝ አዳማ 5 አሸንፏል። በቀሪዎቹ 6 ጨዋታዎች ደግሞ አቸመ ተለያይተዋል።
– 30 ጎሎች በተስተናገዱበት የሁለቱ ግንኙነት ሲዳማ 14 ሲያስቆጥር አዳማ 16 አስቆጥሯል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ሲዳማ ቡና (4-3-3)
ፍቅሩ ወዴሳ
ዮናታን ፍሰሃ – ግርማ በቀለ – ሰንደይ ሙቱኩ – ተስፉ ኤልያስ
አበባየሁ ዮሀንስ – ዮሴፍ ዮሐንስ – ዳዊት ተፈራ
ሀብታሙ ገዛኸኝ – ይገዙ ቦጋለ – አዲስ ግደይ
አዳማ ከተማ (4-3-3)
ጃኮ ፔንዜ
ሱሌይማን ሰሚድ – ምኞት ደበበ – ቴዎድሮስ በቀለ – ሱሌይማን መሐመድ
አዲስ ህንፃ – እስማኤል ሳንጋሪ – ፉአድ ፈረጃ
በረከት ደስታ – ቡልቻ ሹራ – ዱላ ሙላቱ
© ሶከር ኢትዮጵያ