ሪፖርት | ባህር ዳር ከተማ አሁንም በሜዳው ማሸነፉን ቀጥሏል

በ13ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መርሐ ግብር ሰበታ ከተማን በሜዳው የጋበዘው ባህር ዳር ከተማ 3-2 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

ባለሜዳዎቹ ባህር ዳር ከተማዎች ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ወልቂጤ አምርተው 2-0 ከተሸነፉበት ጨዋታ 3 ተጨዋቾችን ለውጠዋል። በዚህም ሄኖክ አቻምየለህ፣ ደረጄ መንግስቱ እና ፍቃዱ ወርቁን በአቤል ውዱ፣ ፍፁም ዓለሙ እና ዜናው ፈረደ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል። ተጋባዦቹ ሰበታዎች በበኩላቸው በሜዳቸው ሀዲያ ሆሳዕናን 2-1 ከረቱበት የመጀመርያ 11 ጌቱ ኃ/ማርያም እና ናትናኤል ጋንቹላን በአዲስ ተስፋዬ እና ፍርዳወቅ ሲሳይ በመቀየር ለጨዋታው ቀርበዋል።

በጨዋታው ተጋባዦቹ ሰበታዎች ኳስን በእርጋታ ለመቀባበል በመሞከር የጨዋታውን የኃይል ሚዛን ወደ ራሳቸው ለማድድግ ጥረዋል። በተቃራኒው ባለሜዳዎቹ ባህር ዳሮች ረጃጅም ኳሶችን እና የቆሙ ኳሶችን ከስል የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎች ጋር በመደባለቅ ከጨዋታው ጎል ለማግኘት ጥረዋል። በዚህም አጨዋወት ባለሜዳዎቹ በ9ኛው እና በ11ኛው ደቂቃ ከመዓዘን ምት እና ከቅጣት ምት ጥሩ የግብ ሙከራ አድርገው መክኖባቸዋል። በቅድሚያ በ9ኛው ደቂቃ የተሻማን የመዓዘን ምት ከጉዳት የተመለሰው አቤል ውዱ በግንባሩ ሞክሮ ወጥቶበታል። በቀጣይ ደግሞ ፍፁም ላይ የተሰራን ጥፋት ተከትሎ የተገኘን የቅጣት ምት ግርማ ዲሳሳ አሻምቶት ዜናው ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

ከእነዚህ የቆሙ ኳሶች በተጨማሪ በእንቅስቃሴ ጫና ማድረግ (ፕሬስ) የጀመሩት ባህር ዳሮች በ14ኛው ደቂቃ በተፈጠረ የሰበታዎች የኳስ ቅብብል ስህተት ግብ አስቆጥረው መሪ ሆነዋል። በዚህ ደቂቃ ኳስ ይዞ የነበረው አንተነህ ተስፋዬ አቀብላለሁ ብሎ የተሳሳተውን ኳስ ባህር ዳሮች ተረክበው በስንታየሁ መንግስቱ አማካኝነት ጎል አስቆጥረዋል። ይህንን ጎል ያስቆጠረው ስንታየሁ ከ3 ደቂቃዎች በኋላ ዳግም ሳሙኤል ተስፋዬ ከግራ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ በግንባሩ ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር ሞክሯል።

የተረጋጋ ያልነበረው የሰበታ የተከላካይ ክፍል ዳግም በ20ኛው ደቂቃም በሰራው ሌላ ስህተት ሁለተኛ ግብ አስተናግዷል። በዚህ ደቂቃ የተገኘን ኳስ በግራ መስመር የነበረው ግርማ ለስንታየሁ በጥሩ ሁኔታ አመቻችቶለት ግብ ተቆጥሯል።

በራሳቸው ስህተቶች ሁለት ጎሎችን ያስተናገዱት ሰበታዎች ከ25ኛው ደቂቃ በኋለ በተሻለ ለመጫወት ሞክረዋል። በ28ኛው ደቂቃም ታደለ መንገሻ በቀኝ መስመር ያገኘውን ኳስ ወደ ግብ ሲመታው አቤል በግንባሩ አውጥቶበታል። ይህንን ሙከራ ያደረገው ታደለ ከ5 ደቂቃዎች በኋላ ቡድኑን ወደ ጨዋታው የሚመልስበትን ጎል ከመረብ አሳርፏል። በዚህ ደቂቃ ባኑ ዲያዋራ ወደ ጎል የመታው ኳስ በተከላካዮች ሲመለስ በጥሩ አቋቋም የነበረው ታደለ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል። ሁለት ጎሎችን አስቆጥረው መሪ የሆኑት ባህር ዳሮች ከሰበታዎች የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን ማክሸፍ እና ማምከን ላይ ተጠምደው ቀሪዎቹን ደቂቃዎች ተጫውተዋል። ሰበታዎችም በቀሪዎቹ የአጋማሹ ደቂቃዎች ከተለያዩ አቅጣጫዎች ጥቃቶችን ለመሰንዘር ቢጥሩን ሳይሳካላቸው ቀርቷል። የመጀመሪያው አጋማሽም ተጨማሪ ጎል ሳይስተናገድበት በባለሜዳዎቹ 2-1 መሪነት ተጠናቋል።

ሁለቱ ቡድኖች ለዕረፍት ወደ መልበሻ ክፍል ባመሩበት ጊዜም በህመም ላይ ለምትገኘው ተጨዋች ቤዛዊት ታደሰ የባህር ዳር ከተማ የሴቶች ቡድን ተጨዋቾች የገንዘብ ማሰባሰብ ሥራ አከናውነዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ በአንፃራዊነት ተሽለው ለመንቀሳቀስ የሞከሩት ሰበታዎች ጥሩ ጥሩ እድሎችን መፍጠር ጀምረዋል። በተቃራኒው ያገኙትን መሪነት አሳልፎ ላለመስጠት ወደ ራሳቸው የግብ ክልል አፈግፍገው የተጫወቱት ባህር ዳሮች መልሶ ማጥቃትን እንደ ዋነኛ አላማ በመያዝ ተንቀሳቅሰዋል። አጋማሹ በተጀመረ በ1ኛው ደቂቃም የቡድኑ አምበል ዳንኤል ኃይሉ ከመዓዘን የተሻገረን ኳስ በመጠቀም ወደ ግብ ጥሩ ኳስ ሞክሮ ወጥቶበታል።

በጥሩ ብቃት አጋማሹን የቀጠሉት ሰበታዎች ከአንድ ደቂቃ በኋላ በፍርዳወቅ ሲሳይ አማካኝነት ሌላ ጥሩ ሙከራ ሰንዝረዋል። ከዚህ ሙከራ በተጨማሪም ቡድኑ በ51ኛው ደቂቃ የአቻነት ጎል ፈልጎ አምልጦታል። ፍፁም የጨዋታ እቅዳቸውን ቀይረው ወደ ሜዳ የገቡት ባህር ዳሮች በ57ኛው ደቂቃ መሪነታቸውን አስፍተዋል። በዚህ ደቂቃ ራሱን ነጥሎ በጥሩ አቋቋም የነበረው ፍፁም ዓለሙ ከመሃል የተሰነጠቀለትን ኳስ ተጠቅሞ ጎል አስቆጥሯል።

በራሳቸው መንገድ ጨዋታውን የቀጠሉት ሰበታዎች የግቡ ልዩነት ቢሰፋባቸውም ተስፋ ሳይቆርጡ ሙከራዎችን ማድረግ ቀጥለዋል። በ62ኛው ደቂቃም ባኑ ዲያዋራ ከርቀት በመታው ኳስ ግብ ለማስቆጠር ሞክረዋል። ከዚህ በተጨማሪም ቡድኑ በ66ኛው ደቂቃ በተገኘ የታደለ መንገሻ ጥሩ እድል ወደ ግብ ደርሶ ነበር። በፈጣን ሽግግሮች ግቦችን ለማስቆጠር የታተሩት ባህር ዳሮች በ79ኛው ደቂቃ ያለቀለት እድል አምክነዋል። በዚህ ደቂቃ አዲሱ ተስፋዬ የተሳሳተውን ኳስ ያገኘው ግርማ ዲሳሳ በጥሩ ብቃት እየገፋ ሄዶ ሲሞክረው ተከላካዮች አውጥተውበታል። ከአራት ደቂቃዎች በኋላም ግርማ በተመሳሳይ መስመር (ግራ) ወደ ሰበታዎች የግብ ክልል በፍጥነት ሄዶ ለዳግማዊ ሙሉጌታ ያቀበለውን ኳስ ዳግማዊ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

እስከ መጨረሻው ደቂቃ ተስፋ ያልቆረጡት ሰበታዎች በ88ኛው ደቂቃ የግቡን ልዩነት አጥብበዋል። ተቀይሮ የገባው ሲይላ ዓሊ ከቀኝ መስመር የመጣን ኳስ ተጠቅሞ ግብ አስቆጥሯል። ባለቀ ደቂቃ ግብ ያገቡት ሰበታዎች በቀሩት 2 እና በተጨመሩት 4 ደቂቃዎች ነጥብ ለመጋራት ሞክረዋል። በዚህም ሳሙኤል ሳሊሶ ባህር ዳሮች ሳጥን ጠርዝ ላይ ያገኘውን ኳስ ወደ ግብ ሲመታው በጥሩ ንቃት ጨዋታውን ሲያከናውን የነበረው ጽዮን መርዕድ አምክኖበታል። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይስተናገድበት በባለሜዳዎቹ 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ 7 ደረጃ ላይ የነበሩት ባህር ዳሮች ነጥባቸውን ወደ 20 ከፍ በማድረግ 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ሰበታዎች በበኩላቸው ከነበሩበት ስድስተኛ ደረጃ 2 ደረጃዎችን ተንሸራተው 8ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

© ሶከር ኢትዮጵያ