በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 13ኛ ሳምንት ሁለተኛ የጨዋታ ቀን ድሬዳዋ ላይ የአሰልጣኝ ለውጥ ያደረገው ድሬዳዋ ከተማ እና ጥሩ የውጤት ጉዞ ላይ የሚገኘው ስሑል ሽረን ያገናኘው ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።
ብርቱካናማቹ ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ሶዶ አቅንተው ከወላይታ ድቻ ጋር ሽንፈት ከተለያየው የቡድን ስብስብ ጊዜያዊው አሰልጣኝ ፍስሀ ጥዑመልሳን ሁለት ለውጥ በማድረግ ወደ ሜዳ ገብተዋል። በዚህም ዘሪሁን አንሼቦን በያሬድ ዘውድነህ፣ አማኑኤል ተሾመን በቢንያም ፆመልሳን ለውጠው ሲቀርቡ በአንፃሩ ስሑል ሽረዎች ደግሞ በሜዳው ሀዋሳ ከተማን ካሸነፈው የቡድን ስብስብ ውስጥ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ አድርጓል። በዮናስ ግርማይ፣ ሙሉዓለም ረጋሳ እና ሰዒድ ሀሰን ምትክም በበረከት ተሰማ፣ ክፍሎም ገብረህይወት እና ያስር ሙገርዋ በመጀመርያ አሰላለፍ ተካተው ነበር የዛሬውን ጨዋታ ያደረጉት።
ባለሜዳዎቹ ቶሎ ቶሎ ወደ ጎል በመድረስ በፍጥነት ጎል ለማግኘት ጥረት አድርገዋል። ገና በ4ኛው ደቂቃ ላይም ሪቻሞንድ ኦዶንጎ ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ በጭንቅላቱ በመግጨት የግብ ሙከራ ማድረግ የቻለ ሲሆን ሽረዎችም ለጢፍ ከመስመር አሻግሮለት ሳሊፍ ፎፋና ሞክሮ ሳምሶን አሰፋ ባወጣበት ሙከራ ምላሽ መስጠት ችለው ነበር።
በ6ኛው ደቂቃ ድሬዳዋዎች መሪ ያደረጋቸውን ጎል አስቆጥረዋል። ከመሐለኛ የሜዳ ክፍል ያሬድ ታደሰ በጥሩ ሁኔታ ያሻገረውን ኳስ ወጣቱ አጥቂ ሙህዲን ሙሳ ከተከላካዮች አፈትልኮ በመውጣት ብርቱካናማዎቹን ቀዳሚ ያደረገች ጎል ማስቆጠር ችሏል።
ከጎሉ በኋላ ባለሜዳዎቹ በኳስ ቁጥጥሩ የተሻለ የተንቀሳቀሱ ቢሆንም ለጎል የቀረቡ ጠንከር ያሉ ሙከራዎች ግን ማድረግ አልቻሉም። በአማካዩ ኤልያስ ማሞ እና ሙህዲን ወደ ግብ ያደረጓቸው ሙከራዎች ግን በሙከራ ደረጃ የሚጠቀሱ ነበሩ። ከጅምሩ ጎል ያስተናገዱት ሽረዎች በአንፃሩ በመጀመርያው አጋማሽ በቶሎ ወደ ጨዋታው ቅኝት ለመግባት የተቸገሩ ሲሆን ይባሱኑ በ35ኛው ደቂቃ ጨዋታውን የሚያከብድ ክስተት አስተናግደዋል። ሙህዲን ሙሳ ወደ ጎል በሚያመራበት ወቅት የሽረው ግብ ጠባቂ ወንድወሰን አሸናፊ ከግብ ክልሉ ውጪ በሰራበት ጥፋት በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ በመውጣቱ ቀጣዮቹን 55 ደቂቃዎች በጎዶሎ የተጫዋቾች ቁጥር ለመጫወት ተገደዋል። ተጠባባቂው ጎል ጠባቂ ዋልታ አንደይም ክፍሎምን ተክቶ ወደ ሜዳ የገባ ሲሆን ያሬድ ታደሰ የመታውን ቅጣት ምት በማዳን ፈተናውን ጀምሯል።
ከቀይ ካርዱ በኋላ ሽረዎች በአብዱለጢፍ መሐመድ በ40ኛው እንዲሁም በሳሊፍ ፎፋና በጭማሪ ደቂቃ ላይ የግል ጥረት የጎል እድሎች መፍጠር ችለዋል። ድሬዳዋዎችም በሪችሞንድ አዶንጎ በተመሳሳይ የግል ጥረት የጎል አጋጣሚ ፈጥረው ወደ ግብነት ሳይቀየር የመጀመርያው አጋማሽ በድሬ መሪነት ተጠናቋል።
በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ከመጀመሪያው በተሻለ የማጥቃት ፍላጎት የተስዋለበት ነበር። በተለይ ድሬዎች አጋማሹ በመጀመርያ ደቂቃዎች መሪነታቸውን አስተማማኝ ለማድረግ አጋጣሚዎችን መፍጠር ችለው ነበር። በ47ኛው ደቂቃ ሬችሞንድ አዶንጎ አመቻችቶ የሰጠውን ኳስ ያሬድ ለጥቂት ያመለጠው እንዲሁም በ51ኛው ደቀቃ ቢኒያም ፆመልሳን ለሙህዲን ያሳለፈለትን አጥቂው ግብ ጠባቂውን አልፎ መትቶ የጎሉን ብረት ታካ የወጣችበት ለዚህ ማሳያ የሚሆኑ ነበሩ። በ60ኛው ደቂቃ ላይ በርከት ሳሙኤል ከርቀት ወደ ግብ አክርሮ መትቶ ዋልታ ያወጣበት አጋጣሚም የድሬዳዋን የግብ መጠን ከፍ ማድረግ የተቃረበ ነበር።
በሒደት የጨዋታውን ሚዛን ወደ ራሳቸው ለማምጣት ጥረት ያደረጉት ሽረዎች ከርቀት በሚያደርጓቸው ሙከራዎች እና በመስመር በኩል ጥሩ ሲንቀሳቀስ በዋለው አብዱለጢፍ መሐመድ ጥረት በሚፈጥሯቸው ጫናዎች ጎል ለማስቆጠር የሞከሩ ሲሆን አማካዩ ሀብታሙ ሸዋለም ከርቀት ሞክሮ ወደ ውጪ የወጣበትም የሚጠቀስ ሙከራ ነበር። ከደቂቃዎች በኋላም በ75ኛው ደቂቃ ወደ አቻነት የተሸጋገሩበትን የፍፁም ቅጣት ምት በረከት ሳሙኤል አብዱለጢፍ ላይ በሰራው ጥፋት አግኝተው በሊጉ ምርጥ ከሚባሉ መቺዎች አንዱ የሆነው ሀብታሙ ሸዋለም በአግባቡ በመጠቀም አቻ አድርጓል።
የአቻነት ግብ ከተቆጠረ በኋላ የመጨረሻዎቹን ደቂቃዎች በድሬዳዋ በኩል ውጤቱን ለመቀልበስ የአጥቂ ቁጥር በማብዛት ጫና መፍጠር ሙከራዎችን ቢያደርጉም ሳይሳካ ቀርቷል። በጎዶሎ እየተጫወቱ የነበሩት ሽረዎች ደግሞ ውጤታቸውን ለማስጠበቅ በማፈግፈግ በመልሶ ማጥቃት ተጫውተዋል። በዚህም ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠር ጨዋታው 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተገባዷል።
ውጤቱን ተከትሎ ሽረ በ20 ነጥቦች አራተኛ ደረጃቸው ላይ ሲረጉ ድሬዳዋ ከተማ አሁንም በወራጅ ቀጠናው ውስጥ ይገኛል።
© ሶከር ኢትዮጵያ