ባህር ዳር ከተማ በሜዳው ሰበታ ከተማን 3-2 ካሸነፈበት ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
“ተጨዋቾቼ ደጋፊዎች ተደስተው ከሜዳ እንዲወጡ ያደረጉበትን መንገድ ማድነቅ እፈልጋለሁ” ፋሲል ተካልኝ (ባህር ዳር ከተማ)
ጨዋታውን እንዴት አገኘኸው?
በጨዋታው አጥቅተን ለመጫወት እና ለማሸነፍ ነበር ወደ ሜዳ የገባነው። በመጀመሪያው 30 ደቂቃ ቡድናችን በምናስበው መንገድ ተጫውቶ ጎሎችን አስቆጥሯል። ነገር ግን በመጀመሪያው አጋማሽ የመጨረሻ 15 ደቂቃዎች እና በሁለተኛው አጋማሽ የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ ያሳየነው ደካማ የመከላከል ቅርፅ ዋጋ ሊያስከፍለን ነበር። ይህም የሆነው በተጨዋቾች ጉዳት ምክንያት አማራጮችን ስላጣን ነው። የሆነው ሆኖ ግን ጨዋታውን ማሸነፍ በመቻላችን ደስ ብሎኛል።
ቡድኑ ጎሎችን ስላስቆጠራችሁበት መንገድ?
በእግር ኳስ የምታሸንፈው ተጋጣሚ ቡድን ከተሳሳተ ነው። ሰበታዎችም እኛ ላይ ግብ ያስቆጠሩት እኛ በፈጠርናቸው የመከላከል ሚዛን ስህተት ነው። እነሱ ኳሱን ከኋላ መስርተው እንደሚጫወቱ ስለምናቅ መሃል ላይ የነበረውን ቦታ ዘግተን ለመጫወት እና ለማጥቃት ነበር የሞከርነው። ጎሎቹንም ያገባነው በዚሁ መንገድ ነው። በአጠቃላይ ባሰብነው መንገድ ነው ጎሎችን ያስቆጠርነው። ነገር ግን በጨዋታው እኛም የመከላከል ስህተቶችን ሰርተን ነበር።
ስለ ባህር ዳር ከተማ የጨዋታ አቀራረብ መዘበራረቅ?
ውድድሩ ሲጀመር የነበረው እና አሁን ያለው ቡድን የተለያየ ነው። ዓመቱ መጀመሪያ ላይ እንደተመለከታችሁት የተሟላ ቡድን ነበረኝ። በዛም ጊዜ በምንፈልገው መንገድ ነበር ስንጫወት የነበረው። ነገር ግን ከሶስት እና ከአራት ሳምንታት በፊት በርከት ያሉ ተጨዋቾችን በጉዳት እያጣሁ ስለሆነ ለቡድኔ የሚያዋጣውን የጨዋታ መንገድ እያሰብኩ ነው ወደ ሜዳ የገባሁት። በብዛት በሜዳችን ስንጫወት በፍጥነት ላይ የተመረኮዘ አጨዋወት በመከተል ጎሎችን ለማስቆጠር እንሞክራለን። ነገር ግን በዋናነት የተጨዋቾች ጉዳት የምንፈልገውን የጨዋታ መንገድ እንዳንከተል አድርጎናል።
ቡድኑ አሁንም ግብ እያስተናገደ ስለመጣበት ምክንያት?
እውነት ነው። ግን እኔ በተጨዋቾቼ ጠንካራ ጎን ላይ ነው ብዙ ማተኮር የምፈልገው። በእርግጥ ግን በመከላከል ላይ ያለብንን ስህተቶች ማስተካከል ይኖርብናል። ይህንን ለማድረግ ደግሞ ወይ በመስራት ችግርክን ትቀርፋለህ ወይንም ደግሞ አዲስ ተጨዋች በማስፈረም ለችግሩ መፍትሄ ትሰጣለህ። ከምንም በላይ ግን ዛሬ ወሳኝ ተጨዋቾቼ ሜዳ ላይ አልነበሩም። ተጨዋቾቼ ግን ይህን ነገር ሳይበግራቸው ደጋፊያቸውን ተደስተው ከሜዳ እንዲወጡ ያደረጉበትን መንገድ ማድነቅ እፈልጋለሁ።
“ከእንቅስቃሴያችን መነሻነት ቢያንስ አቻ መውጣት ይገባን ነበር” ውበቱ አባተ (ሰበታ ከተማ)
ጨዋታው እንዴት ነበር?
ከሜዳ ውጪ ጨዋታ እንደመሆኑ የተንቀሳቀስነው ከበቂ በላይ ነው። ምክንያቱም በብዙ ነገሮች ጥሩ ስለነበርን። ነገር ግን በራሳችን ስህተት ሁለት ጎሎችን አስተናግደናል። ይህም ነገር ትንሽ አውርዶን ነበር። ነገር ግን አገግመን በጥሩ ለመንቀሳቀስ ሞክረናል። በአጠቃላይ ከሜዳ ውጪ ወጥተክ 2 ጎል ማስቆጠርክ መጥፎ አደለም። ነገር ግን በጊዜ የገቡን ጎሎች ዋና አስከፍሎናል። ከእንቅስቃሴያችን መነሻነት ግን ቢያንስ አቻ መውጣት ይገባን ነበር።
ስለ ተጋጣሚ ቡድን እንቅስቃሴ?
ባህር ዳር ጥሩ ቡድን ነው። በተለይ በመልሶ ማጥቃት የነበራቸው ነገር መልካም ነበር። እኛ ግብ ካስተናገድን በኋላ ወደ ፊት ተጠግተን ነበር ስንጫወት የነበረው። ይህንን ተከትሎ እነሱ የተውነውን ቦታ ለመጠቀም ያደርጉት የነበረው ነገር ጥሩ ነበር። በማሸነፋቸው እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ።
ስለ ዳኝነት?
እኔ በዳኝነት ሰበብ አቅርቤ አላቅም። ዛሬም ተሸንፈናል፤ ይህንን እቀበላለሁ። ነገር ግን ለእግር ኳሱ ውበት እና ለተመልካቹ ክብር ሲባክ የሚወሰኑ ውሳኔዎች መስተካከል አለባቸው። በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ተጨዋቾች ሜዳ ላይ ሲተኙ ነበር። ከዚህ በተጨማሪም ስድስት ተጨዋቾች ተቀይረው ወጥተዋል። ነገር ግን ዳኛው አራት ደቂቃ ብቻ ነው የጨመረው። እዚህ ላይ ተቃውሞ ነበረኝ። ከዚህ በተጨማሪም ዳኛው የተጨመረውንም አራት ደቂቃ አላጫወተንም። በተጨመሩት አራት ደቂቃዎችም ተጨዋች ተጎድቶ ነበር። ነገር ግን ዳኛው ይህንን ታሳቢ ሳያደርግ ጨዋታውን ቋጭቶታል። ሌሎቹ ጥቃቅን ነገሮች ግን አላነሳቸውም። ዳኛው የአቅሙን ነው ያጫወተው።
ስለ ፍፁም ዓለሙ የደስታ አገላለፅ?
በቅድሚያ እንደ ኢትዮጵያዊ እኛ ባህል ያለን ሰዎች ነን። ማንም ቢሆን እንግዳን ማክበር አለበት። ተጨዋቹ ጎሉን ካገባ በኋላ ወደ እኛ መጥቶ አንገቱን እንደ ማረድ ነው ያሳየው። ይህ ደግሞ በጣም ነውር ነው። በጣም የሚገርመው ደግሞ ዋና ዳኛውም ሆነ ረዳት ዳኞቹ ደስታ አገላለፁን አይተውታል። ነገር ግን በካርድ አልገፀሱትም። እኔ በግሌ ተጨዋቹ በውስጡ ምን እንዳለው አላቅም። የቀድሞ ጥሩ ተጨዋቼ ነበር። አሁንም ጥሩ ተጨዋች ነው። ነገር ግን ለራሱ ይህንን የብልግና ተግባር ማረም አለበት።
© ሶከር ኢትዮጵያ