የከፍተኛ ሊግ 9ኛ ሳምንት የዛሬ ውሎ

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች ዛሬ ሲቀጥሉ 11 ጨዋታዎች ተከናውነዋል። የዛሬ ውሎንም እንዲህ አጠናቅረነዋል።

ምድብ ሀ

የምድቡ መሪ እና ወራጅ ቀጠና ያሉ ቡድኖችን ያገናኘው የፌደራል ፖሊስ እና የለገጣፎ ለገዳዲ ጨዋታ ለእግርኳሱ የማይጠቀም በርካታ ኩነቶችን አስመልክቶን በፌደራል ፖሊስ 1-0 በሆነ አሸናፊነት ተጠናቋል።

እጅግ የወረደ እንቅስቃሴ እና ረዣዥም ኳሶች በበዙበት የመጀመርያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ከመልስ ምት የተወረወረውን ኳስ የለገጣፎው ግብጠባቂ አንተነህ ሀብቴ መዘናጋትን ተከትሎ በደደቢት ተስፋ ቡድን ውስጥ ያደገው ፈጣኑ የመስመር አጥቂ ብሩክ ብርሀኑ በጭንቅላቱ ኳሱን ወደ ኃላ በመምታት የጨዋታውን ብቸኛ ጎል ለፌደራል ፖሊስ አስቆጥሯል።

በመጀመርያው አጋማሽ ቅርፅ የሌለው ቡድን ሆኖ የታየው የምድቡ መሪ ለገጣፎ በፍቃዱ ነጋሽ ከርቀት በመታው ለጎል ያልቀረበ ሙከራ ውጭ ይህ ነው ተብሎ የሚጠቀስ የጎል አጋጣሚ መፍጠር አልቻሉም። በአንፃሩ ባለሜዳዎቹ ፌደራል ፖሊሶች ጎል ያስቆጥሩ እንጂ በእንቅስቃሴ ረገድ ብዙም የተሻለ ነገር ማሳየት አልቻሉም።

ከእረፍት መልስ በአንፃራዊነት በመጀመርያው አጋማሽ የጎል ዕድል በመፍጠር በኩል የነበረባቸውን ድክመት አርመው የገቡት ለገጣፎዎች ወደ ጨዋታው ሊመልሳቸው የሚችሉበት ግልፅ የጎል አጋጣሚ በደቂቃዎች ልዮነት አንድ ከሳጥን ውጭ አንድ ደግሞ አምስት ከሀምሳ ውስጥ አጥቂው ዳዊት ቀለመወርቅ አግኝቶ በሚያስቆጭ ሁኔታ ሳይጠቀም ቀርቷል።

በጨዋታው 69ኛው ደቂቃ የፌደራል ፖሊስ ተጫዋች ሄኖክ ፍስሀ አስቀድሞ በጨዋታ እንቅስቃሴ የቢጫ ማስጠንቀቂያ ተመልክቶ ባለበት ሁኔታ ጉዳት ደርሶበት ሜዳ ውስጥ ህክምና አግኝቶ በቃሬዛ ተሸክመውት እየሄዱ ሳለ ከተኛበት ተነስቶ ሜዳው ውስጥ በመውረዱ የዕለቱ ዋና ዳኛ ሰዓት ለማባከን ነው በሚል በሁለተኛ ቢጫ ማስጠንቀቂያ በቀይ ካርድ ከሜዳ አስወጥተውታል። በዚህ ሰዓት የፌደራል ፖሊስ ተጫዋቾች እና የቡድኑ አባላት ውሳኔውን በመቃወም በዳኛው ላይ በፈጠሩት ግርግር ጨዋታው ለ13 ደቂቃ ያህል ተቋርጧል። ጨዋታው ከተቋረጠበት እንደጀመረም ወድያውኑ ፌደራል ፖሊሶች በአንበላቸው አማካኝነት የቴክኒክ ክስ አስይዘዋል።

ከዚህ ክስተት በኋላ የነበረው ቀሪ የጨዋታ ክፍለጊዜ እግርኳስ ሳይሆን ግርግር የበዛበት ገበያ ይመስል ነበር። በእያንዳዱ የዳኛው ውሳኔ ላይ ሁለቱም ቡድኖች ተቃውሞ እያሰሙ በተጨማሪም ፌደራል ፖሊሶች ውጤቱን ለማስጠበቅ የጨዋታውን እንቅስቃሴ ለማቋረጥ ሲሞክሩ በአንፃሩ ለገጣፎዎች ተረጋግተው መጫወት አቅቷቸው ምንም የተለየ ነገር ሳይፈጥሩ አሰልቺው ጨዋታ በፌደራል ፖሊስ 1-0 በሆነ ጠባብ ውጤት አሸናፊነት ተጠናቋል።

ጥሩ የውድድር ጊዜ እያሳለፈ የሚገኘው ወሎ ኮምቦልቻ በሜዳው ወልዲያን ገጥሞ 1-0 አሸንፏል። ለወሎ ኮምበልቻ አሰሀጋኝ ጴጥሮስ በሁለተኛው አጋማሽ ብቸኛዋን የድል ጎል አስቆጥሯል።

ዓድዋ ላይ ሶሎዳ ዓድዋ ከ ደብረ ብርሀን ያደረጉት ጨዋታ በባለሜዳዋቹ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። በዘንድሮ የውድድር ዓመት ክስተት ለሆነው ሶሎዳ አላዛር ታደሰ ያስቆጠረው ብቸኛ ግብ ሙሉ ሦስት ነጥብ እንዲያገኙ አስችሏል።

አዲስ አበባ ላይ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ አክሱም ከተማ ያለምንም ግብ የተጠናቀቀ ጨዋታ ሲሆን ቀሪ ሁለት መርሐ ግብሮች ነገ ቀጥለው መቐለ ላይ በ7:00 ደደቢት ከደሴ ከተማ፤ አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ አቃቂ ቃሊቲ ከ ገላን ከተማ 9:00 ላይ ይጫወታሉ።

ምድብ ለ

ዛሬ በምድቡ ሁለት ጨዋታ ብቻ የተከናከነ ሲሆን ተጠባቂ ጫዋታ በነቀምቴ አሸናፊነት ተጠናቋል። በሜዳው አይበገሪነቱን እያሳየ የሚገኘው መሪው ነቀምቴ ሀምበሪቾን አስተናግዶ በሁለተኘመው አጋማሽ በተቆጠሩ ጎሎች 4-1 አሸንፏል። በ46ኛው ደቂቃ ሙሉቀን አዲሱ ቀዳሚውን ግብ አስቆጥሮ መሪ ሲሆኑ ሀምበሪቾች በ62ኛው ደቂቃ ላይ ቢንያም ጌታቸው በፍፁም ቅጣት ምት ባስቆጠረው ጎል አቻ መሆን ችለው ነበር። ዘሪሁን ይልማ በ72ኛው፣ ኢብሳ በፍቃዱ በ79ኛው እንዲሁም ቻላቸው መንበሩ በጭማሪ ደቂቃ ላይ ያስቆጠሯቸው ጎሎችም ለነቀምቴ የ4-1 ድል አስገኝተዋል።

ወደ ጅማ ያቀናው ሻሸመኔ ከተማ ጅማ አባ ቡናን በ22ኛው ደቂቃ ቃላአብ ጋሻው ባስቆጠረው ጎል 1-0 አሸንፈዋል።

የምድቡ ቀሪ ጨዋታዎች ነገ እና ከነገ በስቲያ ሲደረጉ ነገ (ሰኞ) ኢኮስኮ ከ አዲስ አበባ ከተማ በአአ ስታዲየም 7:00 ላይ እንዲሁም ጋሞ ጨንቻ ከ ቤንችማጂ ቡና ጨንቻ ላይ በ9:00 ይጫወታሉ። ረቡዕ ደግሞ ሀላባ ከተማ ከ ካፋ ቡና እንዲሁም መከላከያ ከ ወላይታ ሶዶ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ምድብ ሐ

ዲላ ላይ ጌዴኦ ዲላ ላይ ከ ኮልፌ ቀራኒዮ ባደረጉት የደረጀ በላይ ቡድን ወደ አሸናፊነቱ የተመለሰበትን የ1-0 ድል አሳክቷል። የጌዴኦ ዲላን ብቸኛ የአሸናፊነት ግብ ታምሩ ባልቻ አስቆጥሯል።

ባቱ ላይ ባቱ ከተማ ከ አርባምንጭ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ በአዞቹ አሸናፊነት 1-0 ተጠናቋል። ፍቃዱ መኮንን የአርባምንጭ ብቸኛ ጎል ባለቤት ነው።

ወደ ሺንሺቾ ያመራው መሪው ቡታጅራ ከተማ ከምባታ ሺንሺቾን 2-0 በመርታት በግስጋሴው ቀጥሏል። የአስራት አባተው ቡድን ሁለቱንም ግቦች በላይ ገዛኸኝ ማስቆጠር ችሏል።

ወራቤ ላይ ስልጤ ወራቤ ከየካ ክፍለ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ በወራቤ 1-0 አሸናፊነት ሲጠናቀቅ አርሲ ነገሌ ከ ኢትዮጵያ መድን ያደረጉት ጨዋታ ያለ ግብ ተጠናቋል።

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ