በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 13ኛ ሳምንት መቐለ ላይ በተደረገው ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወልዋሎን 4-1 በማሸነፍ በውድድር ዓመቱ የመጀመርያ የሜዳ ውጪ ድል አስመዝግቧል። ለ24 ሰዓታት የተነጠቀውን መሪነትም መልሶ ተረክቧል።
ወልዋሎዎች ባለፈው ሳምንት በፋሲል ከነማ ሽንፈት ከገጠመው ስብስብ ጃፋር ደሊልን አስወጥተው በአብዱልአዚዝ ኬታ ተክተው ሲገቡ ፈረሰኞቹ ሲዳማን ካሸነፈው ስብስብ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ጨዋታውን ጀምረዋል።
ሁለቱም ቡድኖች ባደረጓቸው ፈጣን የማጥቃት አጨዋወቶች የጀመረው ጨዋታው ግብ የተቆጠረበት ገና በሁለተኛው ደቂቃ ነበር። አቤል ያለው ከመስመር የተሻገረውን ኳስ የግብ ጠባቂውን ስህተት ተጠቅሞ በግንባሩ ገጭቶ ግብ በማስቆጠር ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።
ከግቡ መቆጠር በኋላ ፈረሰኞቹ ተዳክመው የታዩ ሲሆን ወልዋሎዎች በአንፃሩ በርካታ የግብ ዕድሎች ፈጥረው በአጥቂዎቹ የውሳኔ አሰጣጥ ችግር እና በኬንያዊው የጊዮርጊስ ግብ ጠባቂ ጥንካሬ ግብ ከመሆን ተርፈዋል። ቢጫ ለባሾቹ ከፈጠሯቸው ዕድሎች መካከል ጁንያስ ናንጂቡ በሁለት አጋጣሚዎች የሞከራቸው እና ኢታሙና ኬይሙኔ ያመከነው ወርቃማ ዕድል ይጠቀሳሉ።
ጁንያስ ናንጂቡ ብሩክ ሰሙ ያሻማውን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ሞክሯት ለጥቂት ስትወጣበት በተመሳሳይ ቦታ አጥቂው ሳሙኤል ዮሐንስ ያሻማውን ኳስ በግንባር ገጭቶ ፓትሪክ ማታሲ ያዳናት ሙከራ እና ኢታሙና ኬይሙኔ በሳጥን ውስጥ ያገኛትን ኳስ መቶ ተከላካዮች እንደ ምንም ተደርበው ያወጧት ኳስ ቡድኑ ብልጫ በወሰደባቸው ደቂቃዎች የተፈጠሩ ዕድሎች ናቸው።
በአጋማሹ ሙሉ ብልጫ የነበራቸው ባለሜዳዎቹ ከተደጋጋሚ ሙከራዎቹ በኋላ በሰላሳ አምስተኛው ደቂቃ አቻ መሆን ችለዋል። በሳጥን ውስጥ በተሰራ ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ዳዊት ወርቁ ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል።
ወልዋሎዎች ከአቻነት ግቡ በኋላም መሪ ለመሆን ተቃርበው ነበር። ጁንያስ ናንጂቡ ከቅጣት ምት ያደረገውን ሙከራ ፓትሪክ ማታሲ አድኖበት የመጀመርያው አጋማሽ በአንድ አቻ ተጠናቋል።
በመጀመርያው አጋማሽ ጥሩ መንቀሳቀስ ያልቻሉት ፈረሰኞቹ በሁለተኛው አጋማሽም እምብዛም አመርቂ እንቅስቃሴ ባያሳዩም በተጋጣሚ የጎል ክልል የነበራቸው ደካማ እንቅስቃሴ ላይ በርካታ መሻሻሎች አድርገው ወደሜዳ ገብተዋል። ባለሜዳዎቹ ወልዋሎዎችም በርካታ ያለቀላቸው ኳሶች ያባከኑበት አጋማሽ ነበር።
ፈረሰኞቹ እንደመጀመርያው አጋማሽ ሁሉ በዚ አጋማሽም ገና በመጀመርያው ደቂቃ ነበር ግብ ያስቆጠሩት። ጋዲሳ መብራቴ ከመሀል ሜዳ በግሩም ሁኔታ የተሻገረለትን ኳስ ለጌታነህ ከበደ አመቻችቶለት አጥቂው በጥሩ አጨራረስ ግብ አስቆጥሮ ቡድኑ በድጋሚ መሪ ማድረግ ችሏል።
ፈረሰኞቹ ከግቧ መቆጠር በኋላም በሀይደር ሸረፋ እና ጋዲሳ መብራቴ ጥሩ መናበብ ጥሩ የግብ ዕድል ፈጥረዋል። ሆኖም አቡበከር ሳኒ በጥሩ መንገድ የመጣችውን ኳስ መትቶ ግብ ጠባቂው አድኖበታል።
በአጋማሹ የመጀመርያው ደቂቃ ግብ ያስተናገዱት ወልዋሎች አቻ የምታደርጋቸው ግብ ለማግኘት በቀጥተኛው አጨዋወታቸው በርካታ ዕድሎች ፈጥረዋል። ከነዚህም ኢታሙና ኬይሙኔ ሄኖክ መርሹ ያሻማትን ኳስ ተጠቅሞ በግንባር ያደረጋት እና ራምኬል ሎክ ከመዓዝን አሻምቷት ምስጋናው ወልደዮሐንስ በግንባሩ ጨርፎ ከግቡ አፋፍ የነበረው ኢታሙና ኬይሙኔ መትቶ ፓትሪክ ማታሲ በሚያስደንቅ ብቃት ያዳናት እጅግ ለግብ የቀረበች ሙከራ ወልዋሎን አቻ ለማድረግ ከተቃረቡት ሙከራዎች መካከል ይጠቀሳሉ።
ወልዋሎዎች ከተጠቀሱት ሙከራዎች ውጭም ተጨማሪ እድሎችን በሄኖክ መርሹ እና ጁኒያስ ናንጂቡ አማካኝነት መፍጠር ችለው ነበር። ሄኖክ ከርቀት አክርሮ መትቶ የግቡ አግዳሚ ሲመልሰው ጁንያስ ናንጂቡ ከሳጥኑ ጠርዝ የመታው ኳስ በኬንያዊው ግብ ጠባቂ ድንቅ ብቃት ተመልሷል።
በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ፈረሰኞቹ በወልዋሎ የጎል ክልል በተሰሩ ጥፋቶች በተገኙ ሁለት የፍፁም ቅጣት ምቶች አማካኝነት የግብ ልዩነቱን ማስፋት ችለዋል። በሰማንያ ስምንተኛው ደቂቃ የተገኘውን ጌታነህ ከበደ በአግባቡ ተጠቅሞ ሦስተኛውን ግብ ሲያስቆጥር በተጨማሪ ደቂቃ የተገኘውን ሁለተኛ ፍፁም ቅጣት ምት ደግሞ አቤል ያለው ተጠቅሞ የቡድኑን አራተኛ ግብ በማስቆጠር ጨዋታው በፈረሰኞቹ 4-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
በጨዋታው መጠናቀቅያ አከባቢ የወልዋሎ ደጋፊዎች በቡድናቸው ላይ ጠንከር ያለ ተቃውሞ ሲያሰሙ የተስተዋለ ሲሆን ሁኔታው የፀጥታ አስከባሪዎች ሊያረጋጉት ችለዋል። በዚህም በነበረው ግርግር ምክንያት የአሰልጣኞች አስተያየት ሳይሰጥ ቀርቷል።
ውጤቱን ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ የሜዳ ውጪ ድሉን በማስመዘገብ መሪነቱን መልሶ ሲረከብ በ15 ነጥቦች የወራጅ ቀጠናው አፋፍ ላይ ይገኛል።
© ሶከር ኢትዮጵያ