የአሰልጣኞች አስተያየት | ሀዋሳ ከተማ 1-0 ጅማ አባጅፋር

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አስራ ሦስተኛ ሳምንት ሀዋሳ ከተማ በሜዳው ጅማ አባ ጅፋርን 1ለ0 ካሸነፈ በኋላ የሁለቱ ክለብ አሰልጣኞች ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

“ትንሽ ክፍተት ቢኖር የሆነ ችግር ይፈጠር ነበር” አዲሴ ካሳ (ሀዋሳ ከተማ)
ስለ ጨዋታው?

ጨዋታው ጥሩ ነው። ጎል ለማግባት በሚኖር ሂደት ላይ እንዲህ አይነት ነገር ይፈጠራል። እነሱም አጋጣሚዎች አግኝተዋል፤ እኛ ለማጥቃት ስንሄድ እነሱ በመልሶ ማጥቃት ይመጡብን ነበር፡፡ ያው ካለፈው የሆነ ነገር ወስደናል። ኃላ መስመራችን በጥንቃቄ ነበር ሲጠብቅ የነበረው። ትንሽ ክፍተት ቢኖር የሆነ ችግር ይፈጠር ነበር።

ጨዋታው ከባድ ነው፡፡ በእንደዚህ አይነት ሁኔታ በተለይ ለእንደኛ አይነት ቡድን። አጥቂው መስመር ላይ ኳስ በሌለበት ቦታ ላይ ሄኖክ አየለ ነው እኛ ጋር ያለው። ሄኖክ መጫወትን ነው እያሰበ ያለው። በፊት ኳሶችን ጠብቆ ይጨርፋል ይጨርሳል፡፡ አሁን ግን ከዛ ወጥቷል። ተሻጋሪ ኳሶች በጣም ዋጋ እያስከፈሉን ነበር፤ እየተጠቀምንባቸው አይደለም። እነሱ ቆመው ስለሚጠብቁ ለማውጣት ነው የሚያመቸው። እንደዚህ አይነት ኳሶች ሲመጡ ሄዶ የሚጋጭና ቀድሞ ለመግጨት የሚዘጋጅ ተጫዋች ያስፈልጋል። እና ሄኖክ እየጠበቃቸው ስለነበረ እሱን ማድረግ አልቻልንም። ከእረፍት በኃላ ልናረግ የፈለግነውን ቆርጠን ለመግባት ነበር ያም ሆኗል፡፡

ተጋጣሚ በቀይ ወጥቶባቸው ብልጫን መውሰድ አለመቻላችሁ?

ብልጫ አልነበረም ማለት አይቻልም፤ ብልጫማ ነበር፡፡ በጨዋታው በሙሉ እኮ ሁለቱንም ጊዜ (ልጁም ከወጣ በኃላ) በይበልጥ የማጥቃት እንቅስቃሴ ነበረን። በግራም በቀኝም የዳኒን ኳሶች ብናይ የነ ተስፋዬን ብናይ የተሻልን ነን። የቁጥር ብልጫ ጉዳይ አይደለም፤ የኳስ ጨዋታው ሲስተም ነው፡፡ እነሱ በመከላከል ላይ ስለነበሩ ያንን ቦታ አይለቁትም። ያን ቦታ ካለቀቁት የቁጥር ብልጫው ለውጥ ብዙም አይሆንም። ሁለቱንም አርባአምስት ደቂቃዎች እነሱ ሜዳ ላይ ነው ያሳለፍነው። ቆመህ የምትጫወት ከሆነ ከባድ ነው፡፡ አንዳንዴ ደግሞ መነሳሳት ይፈልጋል፡፡ ውጪ ላይ ያለውን ነገር ታዳምጣለህ። ከጎል ማስቆጠር በራቅክ ቁጥር ከምትጫወተው ቅኝት ትወጣለህ፡፡

“ጨዋታ እንዲያምርም ሆነ እንዳያምር የሚያደርጉትም ዳኞች ናቸው” ጳውሎስ ጌታቸው (ጅማ አባጅፋር)

ስለጨዋታው?

በቅድሚያ ጨዋታውን ላሸነፈው ቡድን ሀዋሳ ላመሰግን እወዳለሁ። በመቀጠል ጨዋታው እንዳያችሁት ሳቢ ነበር፡፡ እዚህም ሲሞከር እዛም ሲሞከር ብዙ ነገሮች አይታችዋል፡፡ ቀይ ካርድም ነበረው ገና ጨዋታው እንደተጀመረ። በአስር ልጅ ነበር የጨረስነው። ከእኛ ግን ልጅ የወጣ አይመስልም፤ መልሶ ማጥቃትን ነበር ቡድናችን የተጫወተው።

ከአሁን በኃላ ስለዳኛ ማውራት አልፈልግም። ማውራት የምፈልገው ስለራሴ እና ስለ ልጆቼ ነው፡፡ ተጫዋቾቼ ዘጠናውን ደቂቃ የሚደረገውን አድርገዋል። መጨረሻ ላይም የተፈጠረችው ፔናሊቲ ነው፤ እንደዚህ ነው አልልም፤ ፍርዱን ለምታዩት ለእናንተ ትቻለሁ። በአጠቃላይ ግን የጨዋታው እንቅስቃሴ አስደሳች ነበር። ጨዋታ እንዲያምርም ሆነ እንዳያምር የሚያደርጉት ዳኞች ናቸው፡፡ ሌላ ግን ምንም ማለት አልፈልግም። ይሄ ሲስተም ነው አይደለም ብዬም ልል አልችልም፡፡

ስለታየው ስሜታዊነት?

የተመለከታችሁት የልጆቹን ስህተት ነው፡፡ እነዚህ ልጆች ገና ወጣቶች ናቸው። ስሜታዊ ነው የሚሆኑት። መጀመሪያ መቅረፍ ያለበት የሜዳው ስህተት ነው፡፡ የሜዳው ስህተት ቢቀረፍ በትክክል የተጫወተ ያሸንፋል። ለኢትዮጵያ ስፖርት ማደግ የተጫወተ ቡድን ያሸንፍ። እንዳያችሁት ጎረምሶች ናቸው፤ ወጣት ናቸው፡፡ በሙሉ ከአካባቢው እና አዳዲስ ወጣቶች ሰብስበን ነው የመጣነው። ይሄ ሊበረታታ ይገባል፡፡ ይህ የዳኛ ውሳኔ ነው፤ ያሰጣል አያሰጥም የራሱ ጉዳይ። እናንተ ጋዜጠኞች ይሄንን ነው ያያችሁት። አጠቃላዩን ግን ልትናገሩ ይገባል፡፡ ስለተሸነፍኩ አይደለም እኔም ጅማ ላይ ቡድን ሲመጣ እንዲህ ማድረግ አለብኝ ወይ? ማንም ቡድን የትም ሜዳ ይሂድ ከተጫወተ ያሸነፍ። ቤንች ላይ ስለነበሩ እና ስለታየው ነገር ብታወሩኝ ይከብደኛል፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ