የአሰልጣኞች አስተያየት | ድሬዳዋ ከተማ 1-1 ስሑል ሽረ

በአስራ ሦስተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ድሬዳዋ ከተማ ከስሑል ሽረ ጋር 1ለ1 ከተለያዩበት የዛሬው ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የሁለቱ ክለብ አሰልጣኞች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል፡፡


“ከወትሮው ጎል ላይ በመድረስ የተሻልን ነበርን” የድሬዳዋ ከተማ ጊዜያዊ አሰልጣኝ ፍሰሀ ጥዑመልሳን

ከወትሮው ጎል ላይ በመድረስ የተሻልን ነበርን የ። ከግብ ጠባቂ ተገናኝተንም ስተናል። የተሰጠብን ፍፁም ቅጣት ምት አይገባንም፤ በሱ ቅር ተሰኝቻለሁ፤ ተያይዘው ነው የወደቁት። ኳሷ ግን ወደ ኃላ ቀርታለች። ተመልሰው ተነሱ ኳሷን ቀድሞ በረከት ነው ያገኘው። በረከትን ሊያወጣ ሲል ነው እግሩን ያስገባበት እንጂ ፍ/ቅ/ም አይገባም፡፡ ከዚህ ውጪ ግን ዳኛ ያጠፋው ምንም ነገር የለም፤ ከነዳኛው ጭምር ማሸነፍ እንችል ነበር፡፡

ቡድኑ ላይ የሚታየው ተስፋ ጥሩ ነው። ውጤት ግን በእንዲህ አይነት ነገር ስታጣ ያናዳል፡፡ ቡድኑ ውስጥ ከፍተኛ መነቃቃት አለ። ግን አሰልጣኝ ለውጥ ጋር የሚገናኝ አይደለም፡፡ የሽረ አጥቂዎች ሦስቱም የውጪ ዜጎች ፈጣኖችና አስቸጋሪ ናቸው። እነሱን ግን አቁመናቸው ነበር፡፡ አሁንም አጨራረስ ላይ ግን መስራት አለብን፡፡

“ረጃጅም የሚለቋቸው ኳሶች አስቸጋሪዎች ነበሩ” ሳምሶን አየለ (ስሑል ሽረ)

ጨዋታው ድሬዳዋ ከተማ ካለበት ደረጃ አንፃር ከባድ ሊሆን እንደሚችል ገምተን ነበር፡ የመጣነው። ከዛ በተረፈ በቡድኑ ውስጥ ያለውን አንዳንድ ነገር በመጠቀም ከተሳካልን ሦስት ነጥብ ይዘን ለመሄድ ነበር የጨዋታ እቅድ የያዝነው። በተቻለ አማካይ እና አጥቂውን ወደነሱ እያስጠጋን ነበር ለመጫወት የሞከርነው። ነገር ግን ጨዋታው ብዙ ሳይጓዝ ተጫዋች በቀይ ካርድ ወጣብን። ያንን ተግባራዊ ማድረግ የማንችልበት ሁኔታ ነበር የተፈጠረው። በረኛችን ከወጣ በኃላ በተወሰነ መልኩ ጫናዎች ነበሩብን። በተለይ እነሱ ረጃጅም የሚለቋቸው ኳሶች አስቸጋሪዎች ነበሩ፡፡ 

ሁለተኛው አርባ አምስት ላይ ሌላ የተለየ አቀራረብ ሳይሆን ዕርማት አድርገን ገብተን የተሻለም የጎል ሙከራ አድርገን በተጨማሪም ያገኘነውን ፍፁም ቅጣት ምት ተጠቅመን አቻ ወጥተናል፡፡ ጫና ግን ነበረብን፤ እኛ አስር ልጅ ነው የነበርነው። ስለዚህ ቢያንስ አቻ የምንወጣበትን ነገር ነበር ለመፍጠር የጣርነው። ያላቸውን አሟጠው ሶስት ነጥባቸውን ለማስጠበቅ ሞክረው ነበር፡፡ ቀይ ካርዱም ሆነ ፔናሊቲው ከዳኝነት ጋር የሚያያዝ ነው፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ