የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 9ኛ ሳምንት የሰኞ ውሎ

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ዘጠነኛ ሳምንት ዛሬም በአራት ጨዋታዎች ሲቀጥል ደደቢት፣ ገላን ከተማ፣ ኢኮሥኮ እና ጋሞ ጨንቻ ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል።
ምድብ ሀ


አቃቂ ቃሊቲ 2-3 ገላን ከተማ


(በዳንኤል መስፍን)

ትላንት መካሄድ የነበረበትና በአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ምክንያት ዛሬ በአዲስ አበባ ስታድየም የተካሂደው ይህ ጨዋታ 9:00 ላይ ጥሩ ፉክክር አስመልክቶን ገላን ከተማ በመጨረሻው ደቂቃ ባስቆጠራት ጎል 3-2 አሸንፎ ሊወጣ ችሏል።

አቃቂ ቃሊቲዎች ጎል እስከተቆጠረባቸው ጊዜ ድረስ ጥሩ መንቀሳቀስ ቢችሉም ፊሊሞን ገ/ፃድቅ በ27ኛው ደቂቃ ፍጥነቱን ተጠቀምሞ ከግራ መስመር ወደ ሳጥን አጥብቦ በመግባት የገላንን የመጀመርያ ጎል አስቆጥሯል። ጎል ካስቆጠሩ በኋላ ወደ ጨዋታው የገቡት ገላኖች 36ኛው ደቂቃ ዐቢይ ቡልቲ በጥሩ መንገድ አመቻችቶ ያቀበለውን ጅብሪል አህመድ ወደ ጎልነት በመቀየር የጎል መጠናቸውን ወደ ሁለት ከፍ አድርጎታል።

ብዙም ሳይቆይ በእንቅስቃሴ ብልጫ የነበራቸው አቃቂዎች ከማዕዘን ምት የተሻገረውን በ39ኛው ደቂቃ ቴዲ አጋ በግንባሩ በመግጭት ጎል አስቆጥሮ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሬ በ51ኛው ደቂቃ አቃቂዎች ያገኙትን ፍፁም ቅጣት ምት ጌትነት ታፈሰ ወደ ጎልነት በመቀየር ቡድኑን ሁለት አቻ ማድረግ ችሏል። ወድያውኑ አቃቂዎች መምራት የሚችሉበትን ዕድል ዘመን አበራ ፈጥሮ የነበረ ቢሆንም የግቡ ቋሚ መልሶበታል።

ያገኙትን አጋጣሚዎች ሳይጠቀሙ የቀሩት አቃቂዎች በመጨረሻም ዋጋ ከፍለውበታል። 89ኛው ደቂቃ ተቀይሮ በመግባት ጎል በማስቆጠር ገላን ከአንደኛ ሊግ አንስቶ እየታደገ የሚገኘው ወጣቱ የመስመር አጥቂ እሸቱ ጌታሁን ወሳኝ የማሸነፊያ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በገላን 3-2 በሆነ ውጤት አሸናፊነት ተጠናቋል።
ደደቢት 3-1 ደሴ ከተማ

(በማቲያስ ኃይለማርያም)

ብዙም ሳቢ እንቅስቃሴ ያልታየበት ይህ ጨዋታ ጥቂት የግብ ሙከራዎች የታየበት ነበር። በጨዋታው ከተጋጣምያቸው አንፃር የተሻለ የማጥቃት ፍላጎት የነበራቸው ባለ ሜዳዎቹ ደደቢቶች የተሻለ አጥቅተው የግብ ሙከራዎችም አድርገዋል። ከነዚህም መድሀኔ ታደሰ የተከላካዮች ትኩረት ማጣት ተጠቅሞ መቷት ለጥቂት የወጣችው ሙከራ እና ዳንኤል አድሐኖም ከመአዝን አሻምቷት መድሀኔ ታደሰ በግንባር ያደረጋት እጅግ ለግብ የቀረበች ሙከራ ይጠቀሳሉ። በሀያ ሰባተኛው ደቂቃም ዲሜጥሮስ ወልደሥላሴ በመሐል ሜዳ አከባቢ የተገኘችውን ቅጣት ምት በቀጥታ መቶ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። ኳሷ ተከላካዩ አክርሮ ከመታት በኃላ ከደሴው ግብ ጠባቂ ከፍያለው ኃይሉ እጅ ሾልካ ነበር የገባችው።

ደደቢቶች ከግቧ መቆጠር ከደቁቃዎች በኃላም በመድሀኔ ታደሰ አማካኝነት ተጨማሪ ግብ አክለዋል። አጥቂው በሳጥን ውስጥ ክብሮም አስመላሽ ያቀበለውን ኳስ ተረጋግቶ በማስቆጠር ነበር የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ የቻለው።

በአጋማሹ የተጋጣሚን አጨዋወት ከመከላከል አልፈው የግብ ዕድሎች ያልፈጠሩት ደሴዎች በአክዌር ቻም የግል ጥረት ሁለት ሙከራዎች አድርገዋል። በተለይም ረጅሙ አጥቂ ከርቀት አክርሮ መቷት ሙሴ ዮሐንስ ያዳናት ኳስ ቡድኑ ከሞከራቸው ጥቂት ሙከራዎች ለግብ የቀረበች ነበረች።

ጥቂት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች በታየበት ሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ጥቂት የግብ ሙከራዎች ቢያደርጉም በእንቅስቃሴ ረገድ የደሴ ከተማዎች ብልጫ የታየበት ነበር። በተለይም አሳዳጊ ክለቡን የገጠማው አክዌር ቻም ጥሩ እንቅስቃሴ አድርጎ በስልሳ ስምንተኛው ደቂቃ በረጅሙ የተላከለትን ኳስ ተጠቅሞ ከተከላካዮች ሾልኮ ግብ በማስቆጠር የግብ ልዩነቱን አጥቧል።

ደሴ ከተማዎች ከግቡ በኃላም የተጫዋቾች ቅያሪ አድርገው የግብ ሙከራዎች አድርገዋል ከነዚህም አክዌር ቻም በጭማሪ ደቂቃ ያደረጋት ሙከራ ትጠቀሳለች። ሆኖም ሰማያዊዎቹ መደበኛ የጨዋታ ግዜ ተጠናቆ በተሰጠው ጭማሪ ደቂቃ ግብ አስቆጥረዋል። አብዱልባሲጥ ከማል ከዮሐንስ ፀጋዬ የተመቻቸለትን ኳስ ወደ ግብነት ቀይሮ ጨዋታው በደደቢት 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በዚህም ደደቢቶች ደረጃቸው በማሻሻል ወደ መሪዎቹ ሲጠጉ ደሴ ከተማዎች ወልዲያን አሸንፈው ደረጃቸው ባሻሻሉ ማግስት ነጥብ ጥለዋል።

ምድብ ለ

(በዳንኤል መስፍን)

ከአቃቂ እና ገላን ጨዋታ በፊት አአ ስታዲየም ላይ በተደረገው በዚህ ጨዋታ ጥሩ ፍሰት ያለው እግርኳስ የተመለከትንበት ሲሆን በ4ኛው ደቂቃ አዲስ አበባዎች ኳሱን መስርተው ለመጀመር ባሰቡበት አጋጣሚ ብሩክ ተሾመ የሰራውን ስህተት በመጠቀም ተመስገን አመቻችቶ ያቀበለውን ያሬድ ደርዘ ጎል በማስቆጠር ኢኮሥኮን ቀዳሚ አድርጓል።

ገና በጊዜ ጎል በማስቆጠራቸው የተነቃቁት ኢኮሥኮዎች በፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ የአዲስ አበባ የግብ ክልል በመድረስ የመጀመርያውን የኢኮስኮን ጎል ያስቆጠረው ያሬድ ያቀበለውን ኳስ በሚገባ ተቆጣጥሮ ተመስገን በጅሮንድ በ7ኛው ደቂቃ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል።

አከታትለው ባስቆጠሩባቸው ሁለት ጎሎች የተደናገጡት አዲስ አበባዎች ተረጋግተው ወደሚፈልጉት እንቅስቃሴ ለመግባት ጊዜ ወስዶባቸዋል። ወሰኑ ማዜ ከመስመር አሻግሮት ሚካኤል በየነ በቀጥታ የመታው ኳስም ብቸኛው የመጀመርያ አጋማሽ ሙከራ ነበር።

ከእረፍት መልስ በተደጋጋሚ ወደ ጎል መድረስ እና የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የወሰዱት አዲስ አበባዎች ወደ ፊት የሚሄደውን ኳስ በሚገባ ተቀብሎ ወደ ውጤት የሚቀይር ሁነኛ አጥቂ በቡድኑ ውስጥ ያለመኖሩ ዛሬም ዋጋ እያስከፈላቸዋል። በዚህ ጥረታቸው ውስጥ በ76ኛው ደቂቃ ተከላካያቸው ብሩክ ተሾመ በሰራው ጥፋት ምክንያት በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ መወገዱ የቡድኑ እንቅስቃሴ መውረድ ላይ ተፅእኖ ፈጥሯል።

በቀሩት ደቂቃዎች የቁጥር ብልጫውን የወሰዱት ኢኮሥኮዎች እግራቸው ኳሱ ሲገባ ወደ ማጥቃት ሽግግር የሚያመሩበት ፍጥነት መልካም በመሆኑ ተጨማሪ ጎል ማስቆጠር የሚችሉበትን ዕድል በግል ጥረቱ ተጠቅሞ ተመስገን ሳይጠቀምበት የቀረው እና በሁለት አጋጣሚ የፈጠሩትን ተቀይሮ በገባው ሚካኤል ታመነ አማካኝነት የፈጠሩትን የጎል አጋጣሚ የአዲስ አበባ ግብጠባቂ ምናለ በቀለ አዳናቸው እንጂ ኢኮስኮ ተጨማሪ ጎሎች ማስቆጠር በቻሉ ነበር። ጨዋታውም በመጀመርያው አጋማሽ በተቆጠሩ ሁለት ጎሎች ኢኮስኮ 2–0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በዚህ ምድብ ዛሬ በተደረገ ሌላ ጨዋታ ጋሞ ጨንቻ በሜዳው ቤንች ማጂ ቡናን 4-0 አሸንፏል። በሜዳው አልቀመስ ላለው ቡድን ታደለ በቀለ ሁለት ጎሎችን ሲያስቆጥር ማቲዮስ ኤልያስ እና ለገሰ ዳዊት ቀሪዎቹን አስቆጥረዋል።

የምድቡ ቀሪ የ9ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገም ሲቀጥሉ መከላከያ ከ ወላይታ ሶዶ፣ ሀላባ ከተማ ከ ካፋ ቡና ይጫወታሉ።

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ