ሲዳማ ቡና አዳማ ከተማን አሸንፎ ደረጃውን ካሻሻለበት ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል።
” ጥሩ የኳስ ፍሰት የታየበት ጨዋታ ነው ብዬ አስባለው” ዘርዓይ ሙሉ (ሲዳማ ቡና)
ጨዋታው ጥሩ ነበር። ቡድናችን በማጥቃት ላይ ያለው እንቅስቃሴ ማራኪ ነው። ቡድናችን በመከላከል ላይ ብዙ መስተካከል አለበት። የቆመ ኳስ እና የተሻገረ ኳስ ነው የገባብን። ያሉትን ቀሪ ሁለት ተጫዋቾች ከጨረስን በኃላ እዛጋ ተጫዋች በማምጣት ቡድናችን ለማጠናከር እንሞክራለን። አዳማ ጥሩ ቡድን ነው ፤ ኳስ የሚጫወት ቡድን ነው። ጥሩ የኳስ ፍሰት የታየበት ጨዋታ ነው ብዬ አስባለው። እነሱም ጋር እና እኛ ጋር ያለው ችግር ተመሳሳይ የመከላከል ችግር ነው። እኛ የቆሙ ኳስ ላይ ችግር ነበረብን። እነሱ ደሞ ከኃላ ፍጥነትም ስለሌላቸው ሰንጣቂ ኳስ ላይ ነበር ያተኮሩት። በመከላከል ላይ ያለንን ችግር በሁለተኛው ዙር ፈተን እንመጣለን።
ስለተሻረው ጎል
እሱ ለዳኛው ትቼዋለው። ህዝብም የሚያየው ችግር ስለሆነ ህዝቡ ይመልሰው። ዳኛውም ይፍረድ።
“ትክክለኛ ዳኝነት እንፈልጋለን” የአዳማ ረዳት አሰልጣኝ አስቻለው ኃይለሚካኤል
ስለ ጨዋታው
በሁለታችንም በኩል ጥሩ ጨዋታ ነበር። አስምሬ ምናገረው ነገር ግን ባለፈውም ገልጬዋለው። ዳኞች በባለሜዳ ተፅዕኖ አላቸው። ፌደሬሽኑ ይሄንን ላይ መስራት አለበት ፤ ባለፈውም ተናግሬዋለው። ዳኛ ዳኛ እስከሆነ ድረስ ሚዛናዊ አድርጎ ማጫወት አለበት። በህዝብ አይደለም። ጥሩ ዳኞች አሉ፤ ኢንተርናሽናል ሆነው ውጭም የሚዳኙት፤ ከነሱ ትምህርት መውሰድ አለባቸው። ሁለቱም የመስመር ዳኞች ልክ አልነበሩም። የመስመር ዳኛው ጥሩ ነበር፤ ግን አልረዱትም። ትክክለኛ ዳኝነት እንፈልጋለን። የትም ሜዳ እውነተኛ ዳኝነት ያስፈልጋል። በሁለታችንም በኩል ጥሩ ነበር ኳሱን ነው የተጫወትነው። ያገኘናቸው ዕድሎች ባለመጠቀም ዋጋ አስከፍሎናል። ተጫዋቾቹን ስሜታዊ እንዲሆኑ ያደረጉት ዳኞች ናቸው። ዳኞች ላይ ትልቅ ስራ መሰራት አለበት።
ስለ ቡድናቸው እንቅስቃሴ
ያገኘናቸውን ኳሶች አልተጠቀምንም። ሆኖም የዳኞች ጉዳይ ይታሰብበት።
ስለ ቡድኑ የፋይናንስ ችግር
የፋይናንስ ችግሩ ብአጭር ግዜ ይቀረፋል። የክለባችን አስተዳደር ትኩረት ሰጥቶ እየሰራበት ነው። በአጭር ግዜም ይቀረፋል።
ስለ ተሻረው ጎል
አዲስን አናግሬዋለው፤ ካለቀ በኃላ በእጅ ተነክቷል ብሎኛል። ግብ ጠባቂ አይደለም ኳስ በእጅ መጠቀም የለበትም። ኳሱ ከምኞት ነው በእጁ የወሰደው። ህዝቡም ስሜታዊ መሆን የለበትም። ምክንያቱም ሁላችንም ለሀገር ነው የምንሰራው። ረዳት ዳኞች ዋና ዳኛው መርዳት አለባቸው፤ ይሄ ነገር እናንተም ዘግቡ። ችግር ያለበት ሜዳ መቀጣት ካለበት መቅጣት ነው።
ስለ ምኞት ደበበ ቅያሪ
በወቅታዊ ብቃት ነው ፤ የአሰልጣኝ ውሳኔ ነው።
ግን ምኞት ምርጥ ተከላካያችን ነው።
© ሶከር ኢትዮጵያ