የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ስድስተኛ ሳምንት ዛሬ በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ሲቀጥል መከላከያ አሸንፏል። አዲስ አበባ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
08:00 ስድስት ኪሎ በሚገኘው ሜዳው አቃቂ ቃሊቲን ያስተናገደው መከላከያ በመጨረሻው ደቂቃ አረጋሽ ካልሳ ባስቆጠረችው የቅጣት ምት ብቸኛ ጎል ሦስት ነጥብ ማግኘት ችለዋል።
የውድድሩ ክስተት በመሆን ጠንካራ ተፎካካሪ ቡድን እንደሆነ እያሳየ የሚገኘው አቃቂ ቃሊቲ በመጀመርያው አጋማሽ ከመከላከያ በተሻለ መንቀሳቀስ ቢችሉም የጎል ዕድል ለመፍጠር ሲቸገሩ ተመልክተናል። በአንፃሩ መከላከያ በተደጋጋሚ ነጥብ በመጣላቸው ጫና ውስጥ የገቡት እንስቶች መረጋጋት ተስኗቸው ወደ ፊት የሚሄደው ኳሶቻቸው በአመዛኙ ከጨዋታ ውጭ አቋቋም እየሆነባቸው ተቸግረዋል።
በዚህ ሂደት ውስጥ ግን በመከላከያ በኩል አይዳ ኡስማን ከመስመር ወደ ሳጥን አጥብባ በመግባት በጥሩ ሁኔታ ወደ ጎል የመታችው ለጥቂት በግቡ ቋሚ ታኮ የወጣባት፣ በአቃቂዎች በኩል ደግሞ ከማዕዘን ምት የተሻገረውን በመከላከያዎች ተከላካይ እርስ በእርስ ተደርቦ የቀረውን ኳስ መሀሪ በቀለ በቀጥታ ወደ ጎል ብትመታውም ግብጠባቂዋ ታሪኳ በርገና ያዳነችው በመጀመርያው አጋማሽ በሁለቱም በኩል የተፈጠረ ግልፅ የጎል አጋጣሚ ነበር።
ከእረፍት መልስ አቃቂ ቃሊቲዎች በራሳቸው ሜዳ አድልተው በጥሩ መከላከል ውስጥ በሚያገኙት አጋጣሚ የጎል ዕድል ለመፍጠር ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም። ይልቁኑም ወደ ጨዋታው መጠናቀቂያ አካባቢ እየተዳከሙ ሊመጡ ችለዋል። መከላከያዎች በተሻለ መጫወት በቻሉበት በዚህ እንቅስቃሴ 52ኛው ደቂቃ አይዳ ኡስማን የግል ጥረቷን ተጠቅማ ወደ ፊት በመሄድ ወደ ጎል የመታችው እና ግብጠባቂዋ ሽብሬ ያዳነችባት ኳስ እጅግ ለጎል የቀረበች ሙከራ ነበር።
የአቃቂዎች ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀትን ሰብረው ለመግባት የተቸገሩት መከላከያዎች በበክፍት ሜዳ ጎል ለመስቆጠር ባይችሉም በ80ኛው ደቂቃ ከሳጥን ውጭ የተሰጠውን ቅጣት ምት አረጋሽ ካልሳ በግሩም ሁኔታ ባስቆጠረችው ጎል ጨዋታው በመከላከያ 1-0 በሆነ ውጤት አሸናፊነት ተጠናቋል።
በአዲስ አበባ ስታዲየም 9:00 ላይ የተደረገው የአአ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል። የተቀዛቀዘ እና በሙከራዎች ያልታጀበው የመጀመርያው አጋማሽ በመሐል ሜዳ ኳስ ከማንሸራሸር እና ብልጭ ብለው ከሚጠፉ የማጥቃት አጋጣሚዎች ውጪ የሚጠቀስ ሙከራ ያስመለከተን ወደ እረፍት ሊያመሩ በተቃረቡበት ወቅት ነው። አንፃራዊ ብልጫ የነበራቸው ድሬዳዋዎች ባደረጉት የማጥቃት እንቅስቃሴ በሳጥን ውስጥ የተፈጠረውን የጎል ዕድል ቁምነገር ካሳ አግኝታ ሳትጠቀምበት ቀርታለች።
የተሻለ እንቅስቃሴ በታየበት ሁለተኛው አጋማሽ የተጫዋቾች ለውጥ ያደረጉት ድሬዳዋዎች የተሻለ መንቀሳቀስ ሲችሉ አጋማሹ እንደተጀመረም ታደለች አብርሀም ግልፅ የጎል እድል አግኝታ የመታችውን ኳስ ግብ ጠባቂዋ አውጥታባታለች። አዲስ አበባዎችም በምላሹ ከቆመ ኳስ አደጋ የፈጠሩ ሲሆን በ56ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት የተሻማውን ኳስ ግብ ጠባቂዋ ሳትቆጣጠረው ቢያመልጣትም ተከላካዮች ከመስመር ያወጡት ኳስ የሚጠቀስ ነው።
ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ድሬዳዋዎች ቀዳሚ የሚያደርጋቸውን ጎል አሰቆጥረዋል። በ59ኛው ደቂቃ ተቀይራ የገባችው ሥራ ይርዳው ነበረች ጎሉን ማስቆጠር የቻለችው። የድሬ መሪነት ብዙም ሳይቆይ በግብ ክልላቸው ኳስ በእጅ በመነካቱ በ65ኛው ደቂቃ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት አአ ከተማዎች ተቀይራ የገባችው ፍቅርተ አስማማው በአግባቡ ተጠቅማ አዲስ አበበ ከተማን አቻ አድርጋለች።
ከጎሎቹ መቆጠር በኋላ ጨዋታው የተሻለ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ቢጠበቅም በተቃራኒው የረባ ሙከራ ሳይታይበት በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ