በዓመቱ መጀመርያ ወደ መቐለ ለማምራት ተስማምቶ ከቡድኑ ጋር የቅድመ ውድድር ዝግጅት ጀምሮ በጉዳት ምክንያት ሳይፈርም የቀረው ጋናዊው አልሀሰን ካሉሻ ዛሬ ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር ልምምድ ጀምሯል።
ዛሬ ከቡድኑ ጋር ልምምድ የጀመረው ይህ የቀድሞ የኤሌክትሪክ እና የኢትዮጵያ ቡና አማካይ በዚህ (የዓመቱ አጋማሽ) የዝውውር መስኮት የዓምናውን ቻምፒዮን የሚቀላቀል ከሆነ ቡድኑ በአማካይ ክፍል ያለውን የፈጠራ እና የአማራጭ ችግር ይፈታል ተብሎ ይጠበቃል።
የተጫዋቹ ቀጣይ ሁኔታ በመጪዎቹ ቀናት እንደሚታወቅ ሲጠበቅ ከክለቡ ጋር ያለውን የውል ሁኔታ እየተከታተልን የምናቀርብ ይሆናል።
በሌላ ከመቐለ ጋር የተያያዘ ዜና ያሬድ ብርሀኑ እና ሄኖክ ኢሳይያስ ከክለቡ ጋር ያላቸው ውል ሊያጠናቅቁ ተቃርበዋል። ሄኖክ ኢሳይያስ ባለፈው ዓመት አጋማሽ ወላይታ ድቻን ለቆ ቡድኑ የተቀላቀለ ሲሆን ያሬድ ብርሀኑ በ2010 በተመሳሳይ ጊዜ ወልዲያን ለቆ ወደ መቐለ መፈረሙ ይታወሳል። የዝውውር መስኮቱ ከሁለት ሳምንት በኋላ ሲከፈትም የቆይታቸው ጊዜ መራዘም አለመራዘም የሚጠበቅ ነው።
መቐለ በተጨማሪም የቡድኑን ጥልቀት ከፍ ለማድረግ እንቅስቃሴ ላይ የሚገኝ ሲሆን አምስት ታዳጊ ተጫዋቾችም ከዋናው ቡድን ጋር ልምምድ ጀምረዋል ተብሏል።
© ሶከር ኢትዮጵያ