13ኛ ሳምንት የማሳረጊያ መርሐግብር የሆነውና ተከታታይ ሽንፈቶችን ያስተናገደው ኢትዮጵያ ቡና ከሰሞኑ ተከታታይ ድል እያስመዘገበ የሚገኘውን ወልቂጤ ከተማን የሚያስተናግድበት ጨዋታን በተከታዩ መልኩ ዳሰነዋል።
ኢትዮጵያ ቡና በተከታታይ ሽንፈቶች ከገባበት የወራጅ ቀጠና ለመውጣት ነገ በደጋፊው ፊት የሚያደርገውን ጨዋታ ለማሸነፍ አልሞ ወደ ሜዳ ይገባል።
የኢትዮጵያ ቡና ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ) | ||||
ተሸነፈ | ተሸነፈ | አቻ | አሸነፈ | ተሸነፈ |
በአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ የሚመሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች በተከታታይ ባደረጓቸው የሊጉ ጨዋታዎች በቅዱስ ጊዮርጊስ እና አዳማ ከተማ ሽንፈትን አስተናግደዋል፤ በተለይም በአዳማ ከተማ 3-0 በተሸነፉበት ጨዋታ በተጋጣሚያቸው የተወሰደባቸው ብልጫ በቡድኑ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ተስፋን ሰንቆ የነበረውን ደጋፊ ያስቆጣ ነበር።
በሁለቱም በተሸነፈባቸው ጨዋታዎች በተጋጣሚዎቹ በሜዳው የላይኛው ክፍል ለሚደረግ ጫናን በቂ መላ ስለመዘየዳቸው በሚያጠያይቅ መልኩ ኳሶች በምስረታ የመጀመሪያ ሒደቶች ላይ ሲቋረጥ ማስተዋል ችለናል። በነገው ጨዋታ ታታሪዎቹ የወልቂጤ የፊት መስመር ተሰላፊዎች ይህን እንቅስቃሴ የሚደግሙ ከሆነ ቡናዎች ሊቸገሩ እንደሚችል ይገመታል።
በርከት ያሉ የጎንዮሽ ቅብብሎች በሚያደርገው ቡድኑ በተለይ ወደ ተጋጣሚ የሜዳ ክፍል ኳሶችን በቀጥተኛ ቅብብል በተሻለ የማጥቃት አቋቋም ላይ ለሚገኙ ተጫዋቾች ለማድረስ ታፈሰ ሰለሞን የሚያደርጋቸው የኳስ ንኪኪዎች ወሳኝ ሚና ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።
ጀርባቸውን በስፋት ለተጋጣሚ ግብ ሰጥተው የሚጫወቱት የኢትዮጵያ ቡና የአጥቂ ተሰላፊዎች በተለይ እንደ ወልቂጤ አይነት በመከላከል ጠንካራ የሆነ ቡድኖች ለማስከፈት ከኳስ ጋርና ያለ ኳስ ሳጥን ውስጥ የሚኖሩ የተጫዋቾች እንቅስቃሴ የማይታገዙ ከሆነ ለማስከፈት በጣም ሊቸገሩ እንደሚችል ይገመታል።
የወልቂጤ ከተማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ) | ||||
አሸነፈ | አሸነፈ | አሸነፈ | ተሸነፈ | ተሸነፈ |
ወልቂጤ ከተማ በተከታታይ ሦስት ጨዋታ ያስመዘገበውን ድል ለማስቀጠል የነገውን ጨዋታ ይጠባበቃል።
ከሰሞኑ ከፍተኛ መነቃቃት ላይ የሚገኙት አዲስ አዳጊዎቹ ወልቂጤዎች ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አሰልጣኙ ከሚታወቁበት የኳስ ቁጥጥርን መሰረት ካደረገ እንቅስቃሴ በመውጣት በቀጥተኛ አጨዋወት ጥቃቶችን ሲሰነዝሩ እንዲሁም ግብ ካስቆጠሩ በኃላ ለማስከፈት እጅግ አዳጋች የሆነ የመከላከልን አደረጃጀት ፈጥረው ሲጫወቱ ይስተዋላል።
በግብ ማስቆጠር ረገድ ክፍተቶች የነበሩበት ቡድኑ አሁን ውድድሩን ሲጀምሩ የቡድኑ ሁለተኛ አማራጭ በመሆን የውድድር ዘመኑን የጀመሩት ሳዲቅ ሴቾና አህመድ ሁሴን በተስፈኛው ጫላ ተሺታ ላይ ብቻ ተንጠልጥሎ የነበረውን የግብ ማግባት ጣጣ የተጋሩ ይመስላል። ሁለት ሁለት ግቦችን ያስቆጠሩት አጥቂዎቹ ነገም ለቡድናቸው አንዳች ነገር ይፈይዳሉ ተብለው ይጠበቃሉ። በነገው ጨዋታ ላይ ባለሜዳዎቹ በማጥቃቱ ሂደት የሚተዋቸውን ክፍት ሜዳዎች እነዚሁ አጥቂዎች በቀጥተኛ አጨዋወት ለመጠቀም ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ኢትዮጵያ ቡናዎች በነገው ጨዋታ ወሳኙን አጥቂያቸውን አቡበከር ናስርን የማግኘት ነገራቸው አጠራጣሪ ሲሆን ወልቂጤ ከተማዎች ደግሞ የአንጋፋው ተጫዋቻቸውን አዳነ ግርማን ግልጋሎት ዳግም ከጉዳት መልስ ሲያገኙ ይበልጣል ሽባባው እና አባይነህ ፋኖ ግን አሁንም ከጨዋታ ውጭ መሆናቸው ተረጋግጧል።
እርስ በርስ ግንኙነት
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለመጀመርያ ጊዜ ይገናኛሉ።
ግምታዊ አሰላለፍ
ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)
በረከት አማረ
አህመድ ረሺድ – ፈቱዲን ጀማል – ወንድሜነህ ደረጀ – አሥራት ቱንጆ
ታፈሰ ሰለሞን – አማኑኤል ዮሐንስ – ፍቅረየሱስ ተ/ብርሃን
አቤል ከበደ – እንዳለ ደባልቄ – ሚኪያስ መኮንን
ወልቂጤ ከተማ (3-5-2)
ይድነቃቸው ኪዳኔ
ቶማስ ስምረቱ – ዐወል መሐመድ – ዳግም ንጉሴ
ጫላ ተሺታ – ፍፁም ተፈሪ – አሳሪ አልመሐዲ – በረከት ጥጋቡ – ሙሐጅር መኪ
አህመድ ሁሴን – ሳዲቅ ሼቾ
© ሶከር ኢትዮጵያ