በስድስተኛ ሳምንት የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሁለት ጨዋታዎች ተደርገው ጌዴኦ ዲላ መሪው አዳማን ሲያሸንፍ ሀዋሳ ከሜዳው ውጪ አርባምንጭን አሸንፏል።
[በፋሪስ ንጉሴ]
አርባምንጭ ላይ አርባምንጭ ከተማ ሀዋሳ ከነማን አስተናግዶ ሀዋሳ ከነማ በጎል ተንበሽቦሾ 4-0 አሸንፏል። ጨዋታው በሁለቱም ክለቦች በኩል የማሸነፍ መንፈስ እና ጥሩ እንቅስቃሴ ታክሎበት የተጀመረ ጨዋታ ግብ ለማየት የፈጀው 5ደቂቃ ብቻ ነበር። በፍጥነትና በመልሶ ማጥቃት ጥሩ እንቅስቃሴ እያሳዩ የነበሩት ሀዋሳ ከተማዎች 5ኛው ደቂቃ ላይ ግሩም እንቅስቃሴ እና የግል ችሎታዋን ተጠቅማ መሳይ ተመስገን ባስቆጠረችው ጎል ቀዳሚ ሆነዋል።
በተቆጠረባቸው ግብ ብዙም መደናገጥ ያልታየባቸው ባለሜዳዎቹ በተጋጣሚያቸው ላይ ጫና ፈጥረው ለመጫወት ሞክረዋል። ነገር ግን በማጥቃቱ ብዙም ኃይል ያልነበራቸው በመሆኑ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ለማድረግ ተቸግረዋል። እንግዳዎቹ በአንፃሩ በመልሶ ማጥቃት ጥቃት መሰንዘራቸውን ቀጥለው 18ኛ ደቂቃ ላይ ዙፋን ደፈርሻ ከርቀት አክርራ የመታችው ኳስ በግቡ ከግዳሚ የተመለሰባት አስደንጋጭ ሙከራ ነበር። 20ኛ ደቂቃ ላይም የመስመር ተጫዋጯ ነፃነት መና ላይ ተከላካይ ትዝታ ኃይለማርያም የሰራችውን ጥፋት ተከትሎ የፍፁም ቅጣት ምት ራሷ ነፃነት አስቆጥራ ልዩነቱን አስፍላለች።
ከጎሉ በኋላም በሙከራ የበላይ የሆኑት ሀዋሳዎች ጥሩ ጥሩ እድሎች መፍጠር ችለው ነበር። በተለይ በ36ኛው ደቂቃ ነፃነት መና ከመሐል የተሻገረላትን ኳስ ተከላካዮችን ቀድማ አገባች ሲባል የአርባምንጭ ግብ ጠባቂ ያዳነችባት እንዲሁም 40ኛ ደቂቃ ላይ በድጋሒ ነፃነት ያገኘችውን ጥሩ አጋጣሚ ተጥቅማ አገባች ተብሎ ሲጠበቅ በግቡ አግዳሚ የመለሰባት የሚጠቀሱ ነበሩ።
በሁለተኛው አጋማሽ ይበልጥ ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል በቀላሉ ሲደርሱ የነበሩት ሀዋሳ ከተማዎች በነፃነት መናና በመሳይ ተመስገን በተደጋጋሚ ጫና ሲፈጥሩ ቆይተው 62ኛ ደቂቃ ለይ በጨዋታው ጥሩ በነበረችው መሳይ ተመስገን አማካኝነት ሶስተኛውን ግብ ማስቆጠር ችለዋል።
በተቃራኒው የተቀዛቀዙት ባለሜዳዎቹ አርባምንጭ ከተማዎች በመከላከሉም በማጥቃቱም ተዳክመው ታይተዋል። በመልሶ ማጥቃቱ ተሽለው የታዩት ሀዋሳ ከተማዎችም 68ኛ ደቂቃ ላይ በመሳይ ተመስገን ያለቀለትን የግብ ዕድል አምክነዋል። ሀዋሳ ከተማዎች ሙሉ በሙሉ ብልጫ ወስደው ጨዋታውንም ተቆጣጥረው በመጫወታቸው ቀጥለው የጎል ቁጥራቸውን ወደ አራት አስፍተዋል። አራተኛውንም ጎል ከመሀል የተሻገረላትን ኳስ ምስር ኢብራሂም በግሩም አጨራረስ ማስቆጠር ችላለች። ጨዋታውም በሀዋሳ ከነማ 4ለ0 ተጠናቋል።
ዲላ ላይ የተደረገው የጌዴኦ ዲላ እና መሪው አዳማ ከተማ ጨዋታ በባለሜዳው 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። እፀገነት ግርማ ብቸኛውን የማሸነፍያ ጎል ያስቆጠረች ሲሆን አዳማም በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል።
© ሶከር ኢትዮጵያ