የሞገስ ታደሰ የቀብር ሥነ ሥርዓት ነገ ይፈፀማል

ከታዳጊ ቡድን እስከ ዋናው ብሔራዊ ቡድን እና በተለያዩ ክለቦች የእግርኳስ ህይወቱን የመራውና በዛሬው ዕለት ህይወቱ ያለፈው ሞገስ ታደሰ ግብዓተ መሬት ነገ ይፈፀማል።

ከቅዱስ ጊዮርጊስ ተስፋ ቡድን አንስቶ በዋናው ቡድን መጫወት የቻለው ሞገስ ታደሰ በመቀጠል በሲዳማ ቡና፣ በአዳማ ከተማ፣ በወልዲያ እና የመጨረሻ ክለቡ በሆነው ኢትዮ ኤሌክትሪክ መጫወት ችሏል። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ከታዳጊ እስከ ዋናው ቡድን መጫወት ችሏል።

አዳማ ከተማ ተጫዋች በነበረበት ዘመን በደረሰበት የመኪና አደጋ እጁ ላይ ጉዳት ቢገጥመውም ለጊዜው ጉዳቱ የከፋ ያልመሰለው ሞገስ ቀላል አድርጎት ወደ መደበኛ የእግርኳስ ህይወቱ ተመልሶ ነበር። ሆኖም የጉዳቱ መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመምጣቱ ህክምናውን መከታተል ሲጀምር የእጁ ነርቭ ላይ ጉዳት እንደደረሰ ከሀኪሞች ተነግሮታል። በዚህም ምክንያት ህመሙ በቶሎ ይድናል ብሎ ተስፋ ቢያርግም በተለይ በወልዲያ እና በኢትዮ ኤሌክትሪክ የነበረውን ቆይታ የጉዳቱ ሁኔታ የእግርኳስ ህይወቱን ፈታኝ አድርጎበታል። እግርኳስን እስከ ማቆም ያደረሰው ይህ ጉዳት ግማሽ ሰውነቱን ፓላራይዝድ አድርጎት ከህመሙም እንዲያገግም ከፍተኛ ርብርብ ቢደረግም ለረጅም ጊዜያት አልጋ ላይ ቆይቶ ዛሬ ረፋድ በ29 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።

የሞገስ ታደሰ የቀብር ሥነ ሥርዓት ነገ (ዓርብ) የካቲት 6 ቀን 2012 በቀጨኔ መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን የሚፈፀም ይሆናል።

ሶከር ኢትዮጵያ በድጋሚ በሞገስ ታደሰ ህልፈት የተሰማትን ሀዘን እየገለፀች ለቤተሰቦቹ ወዳጅ ዘመዶቹ እንዲሁም ለስፖርት ቤተሰቡ መፅናናትን ትመኛለች።

©ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ