የአሰልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ ቡና 1-1 ወልቂጤ ከተማ

በ13ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ መርሐግብር ኢትዮጵያ ቡና ከወልቂጤ አቻ ከተለያዩበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።

“ተጫዋቾቹ በነፃነት እንዲጫወቱ ነፃነት መስጠት ያስፈልጋል ብዬ አስባለሁ” ካሳዬ አራጌ (ኢትዮጵያ ቡና)

ስለጨዋታው

አጠቃላይ የነበረው ነገር ጥሩ ነው፤ እኔ በአጠቃላይ ማለት የምፈልገው ሒደቱን መታገስ ያስፈልጋል። በየሰከንዱ የተጋጣሚ ጎል ጋር መድረስ አይቻልም፤ ይደረስም ቢባል
አስተማማኝ ባልሆነ መንገድ መድረስ ይቻላል። ተጫዋቾቹ በነፃነት እንዲጫወቱ ነፃነት መስጠት ያስፈልጋል ብዬ አስባለሁ፤ ከውጤቱ መራራቅ ከነጥቡ አንፃር ልጆቹ በሁለተኛው አጋማሽ ላይ መጣደፍ ውስጥ ገብተው ነበር።

ተጋጣሚያችን ከመጀመሪያው አጋማሽ ከቀረቡበት በሁለተኛው አጋማሽ ለወጥ ብለው ሜዳችን ላይ ቁጥር ጨምረው ለመቅረብ ነው የሞከሩት። በዚህ ሒደት ውስጥ ለመውጣት የምናደርገውን መንገድ መታገስ ይፈልጋል፤ ያለበለዚያ ልጆች ጫና ውስጥ ስለሚገቡ የምንፈልገውን ለማድረግ በጣም እንቸገራለን። በጨዋታው አጠቃላይ የነበረው መልክ ተጋጣሚ በመጀመሪያው አጋማሽ በራሳቸው ሜዳ በቁጥር በዝተው ይጫወቱ ነበር። በሁለተኛው ደግሞ በተወሰነ መልኩ ቁጥር ጨምረው እኛ ሜዳ ላይ ለመጫን ጥረት አድርገው ነበር፤ በጫና ውስጥ በምንሆንበት ወቅት የሚበላሹ ኳሶች ይኖራሉ።

“ያሰብነውን የጨዋታ እቅድ ለመተግበር ተጫዋቾቼ የሚችሉትን ጥረት አድርገዋል” ደግአረግ ይግዛው (ወልቂጤ ከተማ)

ስለጨዋታው

ለፕሪምየር ሊጉ እንግዳ ብንሆንም የገጠምነው ጠንካራውን ኢትዮጵያ ቡና ነበር። በጨዋታው ለመተግበር ያሰብነውን የጨዋታ እቅድ ተጫዋቾቼ ለመተግበር የሚችሉትን ጥረት አድርገዋል። በእርግጥ በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ እንደምንፈልገው መንቀሳቀስ አልቻልንም ፤ በሁለተኛው አጋማሽ ችግሮቻችንን ቀርፈን በተሻለ ተጭነን ለመጫወት ያደረግነው ጥረትም በጎል ማጀብ አልቻልንም። እንደአጠቃላይ ግን ከጠንካራው ኢትዮጵያ ቡና ባደረግነው ጨዋታ ልጆቻችን ያደረጉት እንቅስቃሴ ለወደፊቱ ተስፋ የሚጣልበትና በሒደት ክፍተቶችቻን አርመን ጠንካራ ተፎካካሪ ለመሆን የምንጥርበት ነው።

©ሶከር ኢትዮጵያ