ቅድመ ዳሰሳ | ሰበታ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና

በ14ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ የጨዋታ ቀን ነገ በአዲስ አበባ ስታዲየም ሰበታ ከተማን ከኢትዮጵያ ቡና የሚያገናኘውን ጨዋታ በተከታዩ መልክ ዳሰነዋል።

ወጣ ገባ የሆነ የውድድር ዓመትን እያሳለፉ የሚገኙት ሰበታ ከተማዎች በከፍተኛ ጫና ውስጥ የሚገኙትን ኢትዮጵያ ቡናዎች ነገ በ10 ሰዓት ይጋብዛሉ፤ ጨዋታው ለሁለቱ ቡድኖች ከሚኖረው ትርጉም የተነሳ በጉጉት ይጠበቃል።

የሰበታ ከተማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
ተሸነፈ አሸነፈ ተሸነፈ አሸነፈ ተሸነፈ

ከሜዳቸው ውጭ ነጥብ ማስመዝግብ የከበዳቸው ሰበታ ከተማዎች በሜዳቸው በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች በእስካሁኑ ጉዟቸው የተሻለ ነጥብ የሚሰበስቡባቸው ጨዋታዎች ሰለመሆናቸው የእስካሁኑ ውጤታቸው ይመሰክራል። በሂደት ቡድናቸውን እየለዩ የመጡት አሰልጣኝ ውበቱ በተለይ መሀል ሜዳ ላይ ወሳኝ ተጫዋቾቻቸውን በጉዳት ማጣታቸው ለአሰልጣኙ ከባድ የቤት ስራ መፍጠሩን ቀጥሏል።

ቡድኑ ከቅርብ ጨዋታዎች ወዲህ በመከላከል መስመራቸው ላይ በአስገዳጅ ሁኔታ በርካታ ለውጦች ማድረጋቸው ቡድኑን ዋጋ ሲያስከፍለው ተመልክተናል። በተጨማሪም ኳስን ከኃላ መስርተው ለመውጣት የሚያደርጉት ጥረት ላይ በሚሰሯቸው ቀላል የቅብብሎሽ ስህተቶች (የባህር ዳር ከተማው ጨዋታ እንደምሳሌ ይጠቀሳል) አደጋ ሲጋብዙባቸው ይስተዋላል።

መሀል ሜዳ ላይ በርከት ያሉ በቴክኒኩ ረገድ ጥሩ የሆኑ ተጫዋቾችን የያዘው ቡድኑ ለአጥቂዎች የተሻሉ የግብ አጋጣሚዎችን በመፍጠር ረገድ ክፍተቶች የሚስተዋሉበት ቢሆንም የሚፈጠሩ ጥቂት አጋጣሚዎችን በመጠቀም ከኳስ ውጪ እንቅስቃሴ ረገድ ጥሩ የሆኑት የሰበታ የፊት መስመር ተሰላፊዎች ከሰሞኑ እየተፈተነ ለሚገኘው የቡና የኋላ መስመር ስጋት መሆናቸው አይቀሬ ነው።

ሰበታ ዳዊት እስጢፋኖስ እና በኃይሉ አሰፋን ከጉዳት ሲያገኝ አስቻለው ግርማ ግን አሁንም አላገገመም፡፡

የኢትዮጵያ ቡና ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አቻ ተሸነፈ ተሸነፈ አቻ አሸነፈ

ከሰሞኑ ውጤት እየራቀቸው የመጡትና በወራጅ ቀጠና ውስጥ ለመቀመጥ የተገደዱት ኢትዮጵያ ቡናዎች በነገው ጨዋታ አንዳች መልካም ውጤትን ከጨዋታው ይዘው የመውጣት ግዴታ ውስጥ ሆነው የነገውን ጨዋታ የሚያደርጉ ይሆናል።

በመጨረሻው የሊግ ጨዋታ ለኳስ ምስረታ በዋነኝነት የሚጠቀሙት የተከላካይ አማካያቸው በተቃራኒ ቡድን ተጫዋች በመያዙ ከፍተኛ ውጥንቅጥ ውስጥ ገብተው የነበሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች በነገው ጨዋታ ተጋጣሚያቸው ተመሳሳይ መንገድ ሊከተል ስለሚችል አሰልጣኙ አማራጭ እቅድ ይዘው ወደ ጨዋታው መግባት ይኖርባቸዋል ተብሎ ይታሰባል። ከመከላከል ወደ ማጥቃት የሚደረጉ ሽግግሮች ላይ የሚኖራቸው ፍነጥትም ለነገው ጨዋታ ወሳኝ ነው።

ጨዋታው በአዲስ አበባ ስታዲየም በመደረጉ በደጋፊዎቻቸው በመታገዝ የተሻለ ተጠቃሚነት ይኖራቸዋል ተብለው የሚጠበቁት ኢትዮጵያ ቡናዎች የተከፋውን ደጋፊያቸውን ለመካስ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በቡና በኩል የቡድን ዜና ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

እርስበርስ ግንኙነት 

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ስድስት ጊዜ ተገናኝተው ሰበታ ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ ቡና አንድ አሸንፏል። በሦስቱ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ሰበታ 5፣ ቡና 4 ጎሎች አስቆጥረዋል።

ሰበታ ከተማ (4-3-3)

ዳንኤል አጃይ

ኢብራሂም ከድር – አንተነህ ተስፋዬ – አዲስ ተስፋዬ – ኃይለሚካኤል አደፍርስ

ታደለ መንገሻ – ደሳለኝ ደበሽ – መስዑድ መሐመድ

ባኑ ዲያዋራ  – ፍፁም ገ/ማርያም – ሲይላ ዓሊ

ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)

በረከት አማረ

አህመድ ረሺድ – ፈቱዲን ጀማል – ወንድሜነህ ደረጀ – አሥራት ቱንጆ

ፍቅረየሱስ ተ/ብርሃን – አማኑኤል ዮሐንስ – ታፈሰ ሰለሞን

አቤል ከበደ – እንደለ ደባልቄ – አቡበከር ናስር

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ