ቅድመ ዳሰሳ | ወላይታ ድቻ ከ ባህር ዳር ከተማ

በ14ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ ግብር የሚደረገውን የወላይታ ድቻ እና የባህር ዳር ከተማን ጨዋታ እንደሚከተለው ተመልክተነዋል።

በተከታታይ ጨዋታዎች ባስመዘገቡት በጎ ውጤት ከወራጅ ቀጠናው ተስፈንጥረው የወጡት ወላይታ ድቻዎች ያገኙትን የማሸነፍ መንገድ ላለመልቀቅ እና በትክክል መሻሻል ላይ እንደሆኑ ለማስመስከር የነገውን ጨዋታ ማሸነፍ የግድ ይላቸዋል።

የወላይታ ድቻ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አሸነፈ አሸነፈ ተሸነፈ አሸነፈ አሸነፈ

አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራን አሰናብተው ደለለኝ ደቻሳን በጊዜያዊ ዋና አሰልጣኝነት የሾሙት ባለሜዳዎቹ ከፍተኛ የመነቃቃት ስሜት ላይ ሆነው ጨዋታዎችን እያደረጉ ይገኛሉ። እኚህ አሰልጣኝ ቡድኑን ከያዙ በኋላ ከተደረጉ 5 ጨዋታዎች አራቱን በድል ያጠናቀቁት ድቻዎች የነገውንም ጨዋታ በማሸነፍ ከደረጃ ሰንጠረዡ አጋማሽ በላይ ለመቀመጥ ይጥራሉ ተብሎ ይጠበቃል። ለዚህ ደግሞ ቡድኑ በ13 የሊጉ ጨዋታዎች ካስቆጠራቸው 14 ጎሎች ስድስቱን ያስቆጠረው ባዬ ገዛኸኝ ወሳኝ እንደሚሆን ይጠበቃል። ተጨዋቹ ፍጥነቱን ተጠቅሞ የሚያደርጋቸው የተከላካይ ጀርባ ሩጫዎች ተጋጣሚን እጅግ ይፈትናሉ። ይህንን ተከትሎ ነገ ባለሜዳዎቹ ይህንን አጥቂ የሚያስሮጡ ተከላካይ ሰንጣቂ ኳሶችን ከአማካይ መስመር ተጨዋቾቻቸው በመላክ ግብ ለማስቆጠር እንደሚሞክሩ ይገመታል።

ከባዬ በተጨማሪ ቡድኑ እዮብ እና ቸርነትን ዓላማ ያደረጉ የአግድሞሽ ኳሶችን በማዘውተር የመስመር ላይ ጥቃቶችን ለመሰንዘር ይሞክራሉ ተብሎ ይገመታል። በተለይ ደግሞ ተጋጣሚያቸው ባህር ዳሮች አማካይ መስመር ላይ አጥብበው ስለሚጫወቱ መስመሩን በምቾት ሊጠቀሙበት ይችላሉ። 

የጦና ንቦቹ ያሬድ ዳዊት ከጉዳቱ ሲመለስላቸው የውብሸት ዓለማየሁ እና ባዬ ገዛኸኝ የመሰለፍ ጉዳይ አጠራጣሪ ነው ተብሏል።

የባህር ዳር ከተማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አሸነፈ ተሸነፈ አሸነፈ ተሸነፈ አሸነፈ

ከሜዳቸው ውጪ የሚደረግ ጨዋታን የማሸነፍ ከፍተኛ አይናፋርነት ያለባቸው ባህር ዳር ከተማዎች የመጀመሪያ ድላቸውን ለማጣጣም እና ከደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላለመራቅ የነገውን ጨዋታ ጅማሮ ይጠባበቃሉ።

በጉዳት እየታመሰ የሚገኘው ቡድኑ በሜዳው እና ከሜዳው ውጪ ሲጫወት የሚከተለው የጨዋታ አቀራረብ እየተለያየ መጥቷል። በተለይ ቡድኑ ከሜዳው ውጪ ሲጫወት ቀጥተኝነትን ከፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎች ጋር በመደባለቅ ግብ ለማስቆጠር ይሞክራል። ለዚህ አጨዋወት ደግሞ የሚሆኑ የመስመር ተጨዋቾችን ቡድኑ በመያዙ በነገውም ጨዋታ ይህንኑ ሰሞነኛ አቀራረቡ ይጠቀማል ተብሎ ይታሰባል። ከሁለቱ አጨዋወቶች ግን በዋነኝነት ወጣቱ አጥቂ ስንታየሁን ያነጣጠሩ ረጃጅም ኳሶችን ከመሃል እና ከመስመር በመላክ ቡድኑ ግብ ለማስቆጠር እንደሚሞክር ይገመታል።

የኋላ መስመሩ የላላበት ቡድኑ በነገውም ጨዋታ ይህ የመከላከል አደረጃጀቱ እንደ ከዚህ ቀደሞቹ የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች ዋጋ እንዳያስከፍለው አስግቷል። ከዚህ መነሻነት ቡድኑ በነገው ጨዋታ ወደ ራሱ የግብ ክልል በመጠጋት ግቡን ላለማስደፈር እንደሚሞክር ይታሰባል። ከዚህ ውጪ ድቻዎች በአማካይ መስመራቸው ላይ ከፍተኛ መሻሻልን ስላሳዩ የመሃል ሜዳው ብልጫ ሊወሰድበት ይችላል።

አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ 7 ቋሚ ተሰላፊ ተጨዋቾቹን በጉዳት ምክንያት ሳይዝ ሀዋሳ ገብቷል። በዚህም አዳማ ሲሶኮ፣ ወሰኑ ዓሊ፣ ማማዱ ሲዲቤ፣ ዜናው ፈረደ፣ ፍቅረሚካኤል ዓለሙ፣ ሳላምላክ ተገኝ እና ፍፁም ዓለሙ (ከጉዳቱ በተጨማሪ 5 ቢጫ በማየቱ መሰለፍ አይችልም) በነገው ጨዋታ አይኖሩም። በተቃራኒው በቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ ቀይ ካርድ ያየው ሃሪስተን ሄሱ ቅጣቱን በመጨረሱ ለጨዋታው ዝግጁ ነው ተብሏል።

እርስ በርስ ግንኙነት 

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ሁለት ጊዜ (ዐምና) ተገናኝተው ሁለቱንም በተመሳሳይ 1-1 አቻ ውጤት ተለያይተዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወላይታ ድቻ (4-3-3)

መክብብ ደገፉ 

ፀጋዬ አበራ – ውብሸት ዓለማየሁ – ደጉ ደበበ – አንተነህ ጉግሳ 

በረከት ወልዴ – ተስፋዬ አለባቸው – እድሪስ ሰዒድ

ቸርነት ጉግሳ – ባዬ ገዛኸኝ – እዮብ ዓለማየሁ

ባህር ዳር ከተማ (4-3-3)

ሃሪስተን ሄሱ

ሚኪያስ ግርማ – ሰለሞን ወዴሳ – አቤል ውዱ – ሳሙኤል ተስፋዬ

ሳምሶን ጥላሁን – ደረጄ መንግስቱ – ዳንኤል ኃይሉ

ፍቃዱ ወርቁ – ስንታየሁ መንግሥቱ – ግርማ ዲሳሳ

©ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ