ቅድመ ዳሰሳ | ጅማ አባጅፋር ከ ድሬዳዋ ከተማ

በጅማ ዩኒቨርሲቲ ሜዳ የሚደረገውን የጅማ አባጅፋር እና የድሬዳዋ ከተማን ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት በሃዋሳ ከተማ ሽንፈት ያስተናገዱት ጅማ አባጅፋሮች ዳግም ወደ አሸናፊነት ለመመለስ እና ከተደቀነባቸው የወራጅ ቀጠና ስጋት ለመላቀቅ ሦስት ነጥብን አልመው ወደ ሜዳ ይገባሉ።

የጅማ አባ ጅፋር ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
ተሸነፈ አሸነፈ አቻ አቻ ተሸነፈ

በአሰልጣኝ ጳውሎስ የሚመራው ቡድኑ ወጥ የሆነ ብቃት ማሳየት ተስኖት ጨዋታዎችን በተለያየ ስሜት ማድረግ ቀጥሏል። እርግጥ ቡድኑ ሁነኛ የዋንጫ ተፎካካሪ ቡድኖችን ሲገጥም በጠጣር የመከላከል አቀራረብ በመጫወት ፍሬያማ ቢሆንም ከወገብ በታች የሚገኙ እና ኳስን ለመቆጣጠር የማይፈልጉ ቡድኖችን ሲያገኝ ሲቸገር ይስተዋላል። ነገም ምናልባት ድሬዎች ለኳስ ቁጥጥር እምብዛም ፍላጎት ካላሳዩ ቡድኑ መፍትሄዎችን ለማምጣት እንደሚቸገር ይገመታል።

በመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ጥሩ የሆነው ቡድኑ በነገው ጨዋታ የአይደክሜውን አማካይ ኤሊያስ አህመድን ብቃት እጅግ ይሻል። ተጨዋቹ ሜዳውን እያካለለ ከመጫወቱ በተጨማሪ በግሉ የሚፈጥራቸው ግልፅ የግብ ማግባት አጋጣሚዎች ለተጋባዦቹ ፈተና ይሆናሉ ተብሎ ይታሰባል። ከዚህ በተጨማሪ ጅማዎች በነገው ጨዋታ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የቆሙ ኳሶችን እንደ ሁነኛ የግብ ማስቆጠሪያ ምንጭነት ሊጠቀሙ ይችላሉ። 

በባለሜዳዎቹ በኩል አምረላ ደልታታ ከጉዳት ሲመለስ አብርሃም ታምራት በቅጣት አይኖርም። ቡድኑ ከአብርሃም በተጨማሪ ግብ ጠባቂው ሰዒድ ሀብታሙን በግል ጉዳይ ምክንያት ከስብስቡ ውጪ አድርጓል።

የድሬዳዋ ከተማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አቻ ተሸነፈ አሸነፈ ተሸነፈ አሸነፈ

በጊዜያዊ አሰልጣኛቸው የሚመሩት ድሬዳዋ ከተማዎች ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት በአንድ ነጥብ ብቻ የሚበልጣቸው ጅማን ነገ ይገጥማሉ። 

የውጤት መጥፋት ያሳሰባቸው የድሬዳዋ የክለቡ አመራሮች አሰልጣኝ ፍሰሀ ጥዑመልሳንን በጊዜያዊነት በመሾም ጨዋታዎችን ማድረግ ጀምረዋል። በተለይ ቡድኑ ከሜዳ ውጪ የሚደረጉ ጨዋታዎችን በመሸነፍ ራሱን የወራጅ ቀጠናው ውስጥ ከትቷል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ቡድኑ ቀጥተኝነትን በማዘውተር ግቦችን ለማስቆጠር እና ከጨዋታ ነጥቦችን ይዞ ለመውጣት ይሞክራል። ነገም ቡድኑ ከተቻለ ሶስት ነጥብ ካልተቻለ ደግሞ አንድ ነጥብ ከጨዋታው ለማግኘት የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎች ላይ ብቻ ተንጠልጥሎ ጨዋታውን እንደሚያከናውን ይገመታል።

የቡድኑ ሁነኛ የማጥቂያ መንገድ የሆኑት ሁለቱ የፊት መስመር ተሰላፊዎች ሪችሞንድ እና ሙህዲን ነገም ለተጋባዦቹ ወሳኝ ናቸው። በተለይ ሪችሞንድ ጉልበቱን ሙህዲን ደግሞ ፍጥነቱን ተጠቅሞ የሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ለጅማዎች ፈታኝ ናቸው። ከዚህ መነሻነት ቡድኑ ከአማካዮቹ የሚነሱ ተከላካይ ሰንጣቂ እና በረጅሙ የሚጣሉ ኳሶችን በማብዛት ጎሎችን ለማስቆጠር እንደሚጥሩ ይገመታል።

በቡድኑ በኩል ያሬድ ታደሰ እና ረመዳን ናስር በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጪ መሆናቸው ተነግሯል።

እርስ በርስ ግንኙነት

– አራት ጊዜ በሊጉ ተገናኝተው ድሬዳዋ ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ጅማ አሸንፎ በአንዱ አቻ ተለያይተዋል። ድሬ 6፣ ጅማ 4 ጎሎችን አስቆጥረዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ጅማ አባጅፋር (4-2-3-1)

ዘሪሁን ታደለ

ጀሚል ያዕቆብ – አሌክስ አሙዙ – መላኩ ወልዴ – ኤልያስ አታሮ

ንጋቱ ገ/ሥላሴ – ሄኖክ ገምቴሳ

ሱራፌል ዐወል – ኤልያስ አህመድ – ብሩክ  ገብረአብ

ብዙዓየው እንዳሻው

ድሬዳዋ ከተማ (4-4-2)

ሳምሶን አሰፋ

ያሬድ ዘውድነህ – ዘሪሁን አንሼቦ – ያሲን ጀማል – ፍሬዘር ካሳ

ያሬድ ታደሰ – ፍሬድ ሙሸንዲ – አማኑኤል ተሾመ – ኤልያስ ማሞ

ሬችሞንድ አዶንጎ – ሙህዲን ሙሳ


© ሶከር ኢትዮጵያ