ቅድመ ዳሰሳ | መቐለ 70 እንደርታ ከ ሀዋሳ ከተማ

ምዓም አናብስት ሀይቆቹን የሚያስተናግዱበት ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

በተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ ጥለው ከመሪነታቸው የተንሸራተቱት ቻምፒዮኖቹ ከመሪዎቹ ጋር ያላቸው ነጥብ ለማጥበብ እና ነጥቡን ለማስጠበቅ ይህን ጨዋታ ማሸነፍ የግድ ይላቸዋል።

የመቐለ 70 እንደርታ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
ተሸነፈ ተሸነፈ አሸነፈ ተሸነፈ አሸነፈ

ባለፉት ጨዋታዎች በርካታ ወሳኝ ተጫዋቾቻቸው በማጣታቸው በአቀራረባቸው ላይ ለውጥ ለማድረግ የተገደዱት አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ በነገው ጨዋታ ተጫዋቾቹን ከጉዳት መልስ ማግኘታቸው ተከትሎ በርካታ ለውጦች ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። አሰልጣኙ ባለፈው ጨዋታ ከረጅም ጊዜ በኋላ ከተለመደው 4-4-2 አደራደራቸው ወጣ ብለው ለመጫወት መሞከራቸው ሲታወስ በነገው ጨዋታ ግን የአማኑኤል እና የኦኪኪ የማጥቃት ጥምረት ላይ ትኩረት ወዳደረገው የ4-4-2 አደራደራቸው ይመለሳሉ ተብሎ ይጠበቃል። ከዚህ በተጨማሪ ባለፈው ሳምንት በተመሳሳይ የመከላከል ባህሪ ባላቸው የአማካይ ተጫዋቾች ወደ ሜዳ የገባው ቡድኑ ዮናስ ገረመው እና ያሬድ ከበደን ከጉዳት መልስ ማግኘቱ የፈጠራ አቅሙን ከፍ ያደርግለታል ተብሎ ይጠበቃል።

ባለፉት ጨዋታዎች ቀጥተኛ አጨዋወቱን ለመተግበር ተቸግሮ የነበረው የአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ቡድን በዚ ጨዋታ ወሳኝ ተጫዋቾቹን መልሶ ማግኝቱን ተከትሎ አጨዋወቱን በተሻለ መንገድ ለመተግበር ሁኔታዎች ተመቻችተውለታል።

መቐለዎች ያሬድ ከበደ፣ ዮናስ ገረመው እና ላውረንስ ኤድዋርድን ከጉዳት መልስ ሲያገኙ በረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ ያለው ሚካኤል ደስታ አሁንም ቡድኑን አያገለግልም። ዳንኤል ደምሴም በቅጣት ምክንያት አይኖርም።

የሀዋሳ ከተማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አሸነፈ ተሸነፈ አሸነፈ ተሸነፈ አሸነፈ

በሜዳቸው በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች እያሸነፉ ከሜዳቸው ውጭ እየተቸገሩ የሚገኙት ሀዋሳ ከተማዎች ደረጃቸው ለማሻሻል ይህን ጨዋታ ማሸነፍ ይጠበቅባቸዋል።

ከሜዳቸው ውጪ በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች በቀጥተኛ አጨዋወት የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት የሚያደርጉት ሀይቆቹ በነገው ጨዋታ በአጨዋወታቸው ላይ ወሳኝ ሚና ያለው መስፍን ታፈሰ በጉዳት ባያገኙም ተስፈኛው ብሩክ በየነ በጥሩ ወቅታዊ ብቃት መገኘቱ ለቡድኑ ጥሩ ዜና ነው። ቀዚህም ቡድኑ ፈጣን አጥቂው ላይ መሰረት ያደረገ አጨዋወት ይዞ ይቀርባል ተብሎ ሲጠበቅ በመከላከል ላይ ያለው ክፍተት ፈቶ መግባትም የጨዋታው ውጤት የመወሰን አቅም አለው።

የትኩረት ማጣት ችግር እና የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት የመመከት አቅም የሌለው የቡድኑ የተከላካይ መስመር በነገው ጨዋታ የመቐለ ፈጣን አጥቂዎች እንቅስቃሴ የመግታት ትልቅ ሀላፊነት ይዞ ይገባል።

ሀዋሳዎች በነገው ጨዋታ እስራኤል እሸቱ እና መስፍን ታፈሰን በጉዳት አያሰልፉም።

እርስ በርስ ግንኙነት 

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ አራት ጊዜ ተገናኝተው መቐለ ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ ሀዋሳ አንድ ጊዜ አሸንፏል። አንድ ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይቷል። መቐለ 2፤ ሀዋሳ 1 አሸንፏል።

ግምታዊ አሰላለፍ

መቐለ 70 እንደርታ (4-4-2)

ፊሊፕ ኦቮኖ

ሥዩም ተስፋዬ – ላውረንስ ኤድዋርድ – አሌክስ ተሰማ – አንተነህ ገብረክርስቶስ

ዮናስ ገረመው – አሚን ነስሩ – ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ – ያሬድ ከበደ

አማኑኤል ገብረሚካኤል – ኦኪኪ ኦፎላቢ

ሀዋሳ ከተማ (4-3-3)

ቤሊንጌ ኢኖህ

ተስፋዬ በቀለ – መሳይ ጳውሎስ – ላውረንስ ላርቴ – ያኦ ኦሊቨር

ዳንኤል ደርቤ – አለልኝ አዘነ – ሄኖክ ድልቢ- ብርሀኑ በቀለ

ብሩክ በየነ – የተሻ ግዛው

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ