የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 13ኛ ሳምንት ከቅዳሜ እስከ ሐሙስ መደረጋቸው የሚታወስ ሲሆን እኛም እንደተለመደው በሳምንቱ አንፃራዊ ብቃታቸው ከፍ ያሉትን መርጠን እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።
* ምርጫው የሚከናወነው የሶከር ኢትዮጵያ ሪፖርተሮች እንዲሁም ጨዋታዎችን የሚከታተሉ ባሙያዎች ለተጫዋቾች በሚሰጡት የተናጠል ነጥብ መነሻነት ነው።
አሰላለፍ፡ 3-5-2
ግብ ጠባቂ
ሚኬል ሳማኬ (ፋሲል ከነማ)
ሳማኬ በዚህ ሳምንት ድንቅ ብቃት በማሳየት ቡድናቸውን ተሸክመው ከወጡ ተጫዋቾች መካከል በግንባር ቀደምትነት ሥሙ ይጠቀሳል። ዐፄዎቹ መቐለን በረቱበት ጨዋታ ላይ በርካታ ያለቀላቸው ኳሶች ግብ ከመሆን ያዳነው ማሊያዊው ግብ ጠባቂ ፋሲል ከሜዳ ውጪ የመጀመርያ ሙሉ ሦስት ነጥቡን እንዲያሳካ ጉልህ ሚና ተጫውቷል።
ተከላካዮች
መሳይ ጳውሎስ (ሀዋሳ ከተማ)
ሀዋሳ ከተማ ጅማ አባ ጅፋርን 1-0 ባሸነፈበት በዚህ ሳምንት ጨዋታ በጎዶሎ የተጫዋቾች ቁጥር እየተጫወቱ በመልሶ ማጥቃት ፈታኝ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩት የጅማ ተጫዋቾችን በመቆጣጠር ረገድ መሳይ ጳውሎስ ትልቅ ድርሻ ነበረው። የአንድ ለአንድ የኳስ ግንኙነት ወቅት አጥቂዎች ቦታ እንዳያገኙ ሲያደርግ የነበረው እንቅስቃሴ በተጨማሪ ተሻጋሪ ኳሶችን ወደ ፊት በመላኩም የተሻለ ቀን አሳልፏል።
ውብሸት ዓለማየሁ (ወላይታ ድቻ)
ወላይታ ድቻ በዚህ ሳምንት ሜዳው በመቀጣቱ ሀዋሳ ላይ ለማድረግ የተገደደው ሀዲያ ሆሳዕናን 1-0 ሲረታ ለረጅም ደቂቃዎች መሪነቱን ለማስጠበቅ ባደረገው ትግል የውብሸት አበርክቶ የሚጠቀስ ነበር። በተደጋጋሚ የሆሳዕና የማጥቂያ መንገድን በመዝጋት ጥሩ እንቅስቃሴን ያሳየ ሲሆን በተለይ ቢስማርክ ኦፖንግ ቡድኑን አቻ የምታደርግ ግልፅ አጋጣሚን አግኝቶ ወደ ግብ ሲመታት ከግቡ ጠርዝ ላይ ተንሸራቶ ወደ ውጪ ያወጣበት መንገድ ድቻዎችን አቻ ከመሆን አትርፋ ውድ ሦስት ነጥብ ይዘው እንዲወጡ ያደረገች ነበረች፡፡
ኤድዊን ፍሪምፖንግ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)
ከውድድር ዓመቱ መጀመር አንስቶ በጥሩ ብቃት ላይ የሚገኘው ፍሪምፖንግ በዚህ ሳምንትም ቡድኑ ወደ መቐለ ተጉዞ ባደረገው ጨዋታ ጥሩ እንቅስቃሴ በማድረግ በሳምንቱ ምርጡ መካተት ችሏል። በጨዋታው ምንም እንኳ ቡድኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ በሰፊ ውጤት ቢያሸንፍም ተጋጣሚው የወሰደውን ብልጫ ተጠቅሞ በክፍት የጨዋታ እንቅስቃሴ ግብ ሳያስቆጥር እንዲወጣ የዚህ ጋናዊ ሚና ትልቅ ነበር።
አማካዮች
ጫላ ተሺታ (ወልቂጤ ከተማ)
ፈጣኑ የመስመር ተጫዋች ከኢትዮጵያ ቡና ጋር አንድ አቻ ሲለያዩ በተሰለፈበት የቀኝ መስመር በማጥቃቱ እንዲሁም ወደ መስመር ለጥጠው ጥቃት ለመንሰዘር የሚሞክሩት የኢትዮጵያ ቡናዎችን እንቅስቃሴን ወደ ኃላ እየተሳበ የሚያጨናግፍበት መንገድ ልዩ ነበር። በጣም ታታሪ ስለመሆኑ ዳግም ያስመሰከረው ጫላ መላ ኮሪደሩን እያካለለ የተጫወተበት መንገድ በታታሪነት ጥያቄ ለሚነሳባቸው የሀገራችን የመስመር ተጫዋቾች ማስተማሪያ የሚሆን ነው። በግል ጥረቱ ጥሩ ጥሩ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን የፈጠረው ጫላ የትላንትናው ጨዋታ ምንም እንኳን ግብ ባያስቆጥርም ምን መስራት እንደሚችል ያሳየበት ነበር።
ኤፍሬም ዘካርያስ (ወልቂጤ ከተማ)
የኢትዮጵያ ቡናዎች አጨዋወት ለማበላሸት ሁነኛ ዘዴን ይዘው በገቡት ወልቂጤ ከተማዎች እንቅስቃሴ ውስጥ ኤፍሬም ዘካርያስ ለኢትዮጵያ ቡና አጨዋወት ወሳኙ ሰው የነበረው አማኑኤል ዮሐንስን ከጨዋታው እንዲነጠል ያደረገበት መንገድ እና በሁለተኛው አጋማሽ በተሻለ ጫና ፈጥረው ለመጫወት በሞከሩት ወልቂጤ ከተማዎች እንቅስቃሴ ውስጥ ቁልፍ ሚናን ተወጥቷል። ከዚህም በዘለለ በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎች ላይ የነበረው ተሳትፎም ጥሩ የሚባል ነበር።
ሳምሶን ጥላሁን (ባህር ዳር ከተማ)
በሦስት የአማካይ መስመር ተጨዋቾች ለሚጫወተው የፋሲል ተካልኝ ቡድን የሳምሶን ሚና ጎላ ያለ ነው። በተለይ ቡድኑ ሰበታን አስተናግዶ በረታበት ጨዋታ ሳምሶን ያሳየው እንቅስቃሴ ቡድኑን እጅግ ጠቅሟል። ከተከላካይ እየተቀበለ የሚያሰራጫቸው ኳሶች፣ ቡድኑ በመከላከሉ ረገድ ሚዛኑን እንዳይስት የሚያደርገው ጥረት እና የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎችን የሚያስጀምረበት ሂደት ተጨዋቹን የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ ለመጀመርያ ጊዜ እንዲካተት አድርጎታል።
ፍፁም ዓለሙ (ባህር ዳር ከተማ)
በጉዳት እና በተለያዩ ምክንያቶች ድንቅ አቋሙን ማስቀጠል ያልቻለው ፍፁም ዳግም ወደ ምርጥ ብቃቱ እየተመለሰ ይመስላል። ከሦስቱ የቡድኑ አጥቂዎች ኋላ፣ መሐል አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ፊት በመገኘት የተጋጣሚን የተከላካይ መስመር የሚፈታተነው ተጨዋቹ በእሁዱ ጨዋታ አንድ ጎል ሲያስቆጥር አንድ ለጎል የሚሆን ኳስ ደግሞ አመቻችቶ አቀብሏል። በዚህም ለአራተኛ ጊዜ የሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ ተካቷል።
አቤል ያለው (ቅዱስ ጊዮርጊስ)
ፈረሰኞቹ ወደ መቐለ አምርተው ሦስት ወሳኝ ነጥቦች አሳክተው በተመለሱበት ጨዋታ ጥሩ እንቅስቃሴ ካሳዩት ተጫዋቾች አንዱ አቤል ያለው ነው። በጨዋታው ሁለት ግቦች አስቆጥሮ ለአንዱ የፍፁም ቅጣት ምት መገኘት ምክንያት የነበረው ይህ ፈጣን አጥቂ ቡድኑ በርካታ የግብ ዕድሎች ባልፈጠረበት ጨዋታ በግሉ ያሳየው ብቃት እና ታታሪነት የሚደነቅ ነበር። በሁለት ጨዋታዎች አራት ግቦች ያስቆጠረው ይህ ተጫዋች በተከታታይ ሁለት ሳምንታት በሳምንቱ ምርጥ ቡድን መካተት ችሏል።
አጥቂዎች
ሙጂብ ቃሲም (ፋሲል ከነማ)
በዚህ ሳምንት ዐፄዎቹ በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ግዜ ከሜዳቸው ውጭ አሸንፈው ሲመለሱ በጨዋታው ዋና ተዋናይ የነበረው ሙጂብ ቃሲም ሁለት ግሩም ግቦች በማስቆጠር ቡድኑን ሦስት ነጥቦች አስጨብጧል። ከጊዜ ወደ ጊዜ የአስፈሪ አጥቂዎችን ባህሪ እየተላባሰ የመጣው ይህ አጥቂ በተለይም ሁለተኛዋን ግብ ያስቆጠረበት መንገድ የሚያስደንቅ ነበር።
ስንታየሁ መንግሥቱ (ባህር ዳር ከተማ)
ይህ ወጣት አጥቂ የባህር ዳር ከተማ የችግር ጊዜ ፈጥኖ ደራሽ ሆኗል። በተለይ የቡድኑ ዋና አጥቂዎች በጉዳት እና በተለያዩ ምክንያቶች በማይሰለፉበት ጊዜ የፊት መስመሩን በድፍረት በመምራት ጎሎችን ለማስቆጠር ይታትራል። ተጨዋቹም በእሁዱ ጨዋታ ሁለት ጎሎችን ከማስቆጠሩ በተጨማሪ ወደ ኋላ እየተመለሰ የቡድኑን የአማካይ መስመር ይረዳበት የነበረው መንገድ ጥሩ ነበር። ይህንን ተከትሎ ቁመተ መለሎ ስንታየሁ ለመጀመሪያ ጊዜ የሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ ተካቷል።
ተጠባባቂዎች
ፓትሪክ ማታሲ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)
መሐመድ ዐወል (ወልቂጤ ከተማ)
ዳዊት ተፈራ (ሲዳማ ቡና)
ያሬድ ታደሰ (ድሬዳዋ ከተማ)
እዮብ ዓለማየሁ (ወላይታ ድቻ)
ቡልቻ ሹራ (አዳማ ከተማ)
ጌታነህ ከበደ (ቅዱስ ጊዮርጊስ
© ሶከር ኢትዮጵያ