የፕሪምየር ሊግ 13ኛ ሳምንት – ዓበይት ጉዳዮች (፪) | ተጫዋች ትኩረት

👉 አስፈሪው የ”አ-ጌ-ጋ” ጥምረት ፈረሰኞቹን ወደፊት መግፋቱን ቀጥሏል

በተጫዋቾች ብቃት መውረድና ጉዳት የተነሳ ከዐምና ጀምሮ በሚጠበቀው ልክ ግልጋሎት እየሰጠ ያልነበረው የፈረሰኞቹ የፊት መስመር ላይ አሁን ላይ ግን አዲስ ተስፋን ይዞ ብቅ ብሏል።

በአቤል ያለው፣ ጌታነህ ከበደ እና ጋዲሳ መብራቴ “አ-ጌ-ጋ” ጥምረት ግን በተከታታይ ጨዋታዎች ፈረሰኞችን እየታደገ ቀጥሏል። በዚህኛው ሳምንትም አቤል ያለውና ጌታነህ እንደ 12ኛ ሳምንት ሁሉ ሁለት ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥሩ ጋዲሳ መብራቴ ደግሞ ምንም እንኳን ግብ ባያስቆጥርም በግቦች ላይ ተሳትፎ ማድረጉን ቀጥሏል።

ከሜዳ ውጭ ለማሸነፍ ተቸግሮ የከረመው የፈረሰኞቹ ስብስብ አሁን በስተመጨረሻም የመጀመሪያውና የሜዳ ውጭ ድሉን አስመዝግቧል። ወደ ቀደመ አስፈሪነቱ እየተመለሰ የሚመስለው ቅዱስ ጊዮርጊስ በቀጣይ ለዋንጫ በሚያደርጉት ጉዞ ላይ ከእነዚሁ ተጫዋቾች ጥምረት ከሳምንት ሳምንት ግሎጋሎትን የሚያገኝ ከሆነ ዋንጫውን ከሁለት ዓመታት በኃላ ወደ ሸገር የመመለሱ ነገር አይቀሬ ነው።

👉 ሀዋሳ ከተማ = ብሩክ በየነ

የዘንድሮውን የሀዋሳ ከተማ ስብስብ ያለ ወጣቱ አጥቂ ብሩክ በየነ ማሰብ እጅጉን ይከብዳል። ወጣቱ አጥቂ በጨዋታዎች ላይ ለቡድኑ ያለው አበርክቶ እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በ19 ነጥብ በ6ኛ ደረጃ ሀዋሳ ከተማ እንዲገኝ በወሳኝ ጨዋታዎች ላይ ወሳኝ ሦስት ነጥብ የሚያገኝባቸውን ግቦች ከዚሁ ወጣት የሚነሱ መሆናቸውን ቀጥለዋል።

ይህ አጥቂ የአዲሴ ካሳው ሀዋሳ ከተማ ሁለንተና ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። በዚህኛው ሳምንት የጨዋታ መርሃግብር ቡድኑ ጅማ አባጅፋርን ሲረታ ብቸኛዋን ግብ ለቡድኑ ማስገኘት ችሏል

👉 ሙጂብን የሚያቆም አልተገኘም

ዘንድሮ የሚያቆመው ያልተገኘው ሙጂብ በዚህኛው ሳምንት ደግሞ የፋሲል ከነማዎች ከሜዳ ውጭ የማሸነፍ ዓይነጥላ በተገፈፈበት ጨዋታ መቐለን 2-0 ሲረቱ ሙጂብ ቃሲም ሁለቱንም ግቦች ማስቆጠር ችሏል።

በ13 ግቦች በተናጥል የሊጉን ከፍተኛ አስቆጣሪነት ዝርዝር እየመራ የሚገኘው ሙጂብ በየጨዋታው በአማካይ አንድ ግብ እያስቆጠረ ቡድኑን ተሸክሞ መጓዙን ቀጥሏል። አምና ከተለያዩ አቅጣጫዎች በብዛት ግቦችን ያገኝ የነበረው ቡድኑ ዘንድሮ ላይ ግን ይህ ሂደት መቀዛቀዞችን ያሳየ ይመስላል። ላለፉት ተከታታይ ጨዋታዎች ቡድኑ ከአስቆጠራቸው ግቦች ውስጥ ከፍተኛ ድርሻን የሚይዙት የሙጂብ ቃሲም ግቦች ናቸው። ይህ አጥቂ ዘንድሮ ከሚገኝበት ድንቅ ወቅታዊ ብቃት አንፃር ጉዳት ካላስተናገደ የሊጉን የግብ ክብረወሰን የማሻሻሉ ነገር የሚቀር አይመስልም።

👉 የፍፁም ቅጣት ምቱ ፈርጥ ሀብታሙ ሸዋለም

በፕሪምየር ሊጉ ከሚጫወቱ ተጫዋቾች የፍፁም ቅጣት ምት ኳሶችን ወደ ግብ በመቀየር ረገድ በሀብታሙ ሸዋለም ደረጃ የሚስተካከል ተጫዋቾችን በሊጉ ፈልጎ ማግኘት የሚታሰብ አይመስልም ቢባል ማጋነን አይሆንም።

በወሳኝ የጨዋታ ቅፅበቶች የፍፁም ቅጣት ምቶችን በማስቆጠር ቡድኑን እየታደገ የሚገኘው ሀብታሙ በዚህኛው ሳምንት ደግሞ ገና በማለዳው ባስተናገዱት ግብ ከሜዳቸው ውጭ በድሬዳዋ ከተማ ሲመሩ ቢቆዩም በ75ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት የፍፁም ቅጣት ምት ኳስ ቡድኑ ከሜዳው ውጭ ወሳኝ አንድ ነጥብ ይዞ እንዲመለስ አስችሏል።

በዘንድሮው የ13ኛ ሳምንታት የሊጉ ጉዞ ውስጥ ስሑል ሽረዎች ያገኟቸውን አራት የፍፁም ቅጣት ምቶች በሙሉ ሀብታሙ ሸዋለም በተረጋጋ ሁኔታ መትቶ ማስቆጠር ችሏል። የስሑል ሽረዎች ተቀዳሚ የፍፁም ቅጣት ምት መቺ መሆኑን እያስመሰከረ የሚገኘው ተጫዋቹ በሊጉ ተወዳዳሪ የማይገኝለትም ስለመሆኑ መመስከር ይቻላል።

👉 የተረሳው ስንታየሁ መንግሥቱ አለሁ ብሏል

ዐምና በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 12 ግቦችን በማስቆጠር ከአርባምንጭ ከተማ ጋር የተሳካ ጊዜን ያሳለፈው ግዙፉ አጥቂ በክረምቱ ባህርዳር ከተማን መቀላቀል ቢችልም በማሊያዊው ማማዱ ሲዲቤ ጥላ ስር ሆኖ በአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ስብሰብ ውስጥ በቂ የመሰለፍ እድልን ማግኘት እየቻለ አይገኝም።

በጨዋታዎች ላይ በስተመጨረሻ ደቂቃዎች ተቀይሮ ከመግባት በዘለለ ማማዱ ሲዲቤ በደሞዝና ጉዳት ባልተሰለፈባቸው አራት ጨዋታዎች በቋሚነት የቡድኑን የፊት መስመር እየመራ በገባባቸው ጨዋታዎችም ጥሩ ከመንቀሳቀስ ባሻገር ግቦችን እያስቆጠረ ይገኛል። ከዚህ ቀደም በሲደማ ቡና 3-1 ሲረቱ የማስተዛዘኛዋን ግብ አስቆጥሮ የነበረው ስንታየሁ በዚህኛው ሳምንት ደግሞ ሰበታን ሲረቱ ሁለት ግቦችን በማስቆጠር ለቡድኑ ወሳኝ ሶስት ነጥብ ማስገኘት ችሏል። በአየር ላይ ኳሶችን አጠቃቀም ላይ የተሻለ የሆነው አጥቂው በዚህኛው ሳምንት ድል ላይ አንድ ኳስን በግንባር እንዲሁም የተቀረችውን በእግሩ ማስቆጠር ችሏል።

ዐምና በከፍተኛ ሊጉ ለከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ሲፎካከሩ የነበሩት ስንታየሁ መንግስቱና የወልቂጤ ከተማው አህመድ ሁሴን በሳምንት ልዮነት በፕሪምየር ሊጉ ሁለት ሁለት ግብ ማስቆጠራቸው አስገራሚ ግጥምጥሞሽ ሆኗል።

👉 የፍፁም ዓለሙ የደስታ አገላገፅ

በ13ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በባህር ዳር ዓለምአቀፍ ስታዲየም ሰበታ ከተማን ያስተናገዱት ባህርዳሮች 3-2 ማሸነፋቸው የሚታወስ ነው። በጨዋታውም የሶከር ኢትዮጵያ የፕሪምየር ሊጉ የህዳርና ታህሳስ ኮከብ ተጫዋች የነበረው ፍፁም ዓለሙ ለቡድኑ ሦስተኛዋን ግብ ካስቆጠረ በኃላ ያሳየው የደስታ አገላለጽ ሊደገም የማይገባውና የጨዋታ መንፈስን ሊረብሽ የሚችል አስነዋሪ ነግባር ነበር።

ተጫዋቹ ግቡን ካስቆጠረ በኃላ በቀጥታ ወደ ሰበታ ተጠባባቂ ተጫዋቾች መቀመጫ በማምራት ያሳየው “የአንገት ማረድ” አካላዊ እንቅስቃሴ በበርካቶች የተወገዘ ነበር። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ በጉዳዩ ላይ ሀሳባቸውን የሰጡት የሰበታው አለቃ ውበቱ አባተም የተጫዋቹን ድርጊት ኮንነዋል።

👉 የያሬድ ባየ ሚና

በገጠመው ጉዳት ለሳምንታት ከሜዳ ርቆ የቆየው የዐፄዎቹ አምበል ያሬድ ባየ ከጉዳት መልስ የቡድኑን የመከላከል አደረጃጀት ላይ ካመጣው ለውጥ በላይ በሜዳ ላይ የነበረው የመሪነት ሚና የተጫዋቹ ሚና የማይተካ መሆኑ አስመስክሯል።

ቡድኑ መቐለ 70 እንደርታን በገጠመበት ጨዋታ ላይ በጨዋታው መሀል ለተፈጠሩት ንትርኮች የፈታበት መንገድ እና የቡድኑ ተጫዋቾች የመራበት መንገድ በእጅጉ የሚያስደንቅ ነው። በተለይም በመጀመርያው አጋማሽ በሜዳ ላይ ለተፈጠሩት ነገሮች መረጋጋት አምበሉ የነበረው ሚና ለሌሎች አምበሎችም ጥሩ ምሳሌ ነው።

👉 የአህመድ ሁሴን ተመዝግዛጊ ፍጥነት

ዐምና በከፍተኛ ሊግ ለወልቂጤ ከተማ ከፍተኛ ግልጋሎት ሲሰጥ የነበረው አህመድ ባሳለፍነው ሳምንት ተቀይሮ በመግባት ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር በዚህኛው ሳምንትም በቋሚነት በጀመረበት የኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ ላይ አንድ ግብ ማስቆጠር ችሏል።

የመጀመሪያውን ግብ ሲያስቆጥር ከወንድሜነህ ደረጀ የተሳሳተ ማቀበል መነሻነት ከአዳነ በላይ የደረሰውን ተከላካይ ሰንጣቂ ኳስ ላይ ደርሶ ግቧን ባስቆጠረበት ሒደት የተጠቀመው ፍጥነትና አጨራረስ አስገራሚ ነበር። በመጀመሪያው አጋማሽ በሌላ አጋጣሚ በመልሶ ማጥቃት ከጥልቀት ተነስቶ ፈቱዲንን በአስደናቂ ፍጥነቱ አልፎ በረኛ የያዘበት እንዲሁም በሁለተኛው አጋማሽ እንዲሁ በሦስት አጋጣሚዎች ከመሀል ሜዳ በመነሳት በአስደናቂ ፍጥነት የኢትዮጵያ ቡናን ተከላካዮችን ያልፍበት የነበረው መንገድ እጅግ በጣም አስገራሚ ነበር።

በከፍተኛ ደረጃ በመጫወት ገና ሁለተኛ የውድድር ዘመኑ ላይ የሚገኘው ወጣቱ አጥቂ ፍጥነቱ እና አካላዊ ቁመናው የተሟላ ቢሆንም አጨራረስ ላይ ማሻሻል የሚገቡትን ነገሮችን በሒደት እያረመ ከመጣ መጪ ጊዜው ብሩህ ይመስላል።

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ