የፕሪምየር ሊግ 13ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፩) – ክለብ ትኩረት

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 13ኛ ሳምንት ከቅዳሜ አንስቶ እስከ ሐሙስ በተደረጉ ጨዋታዎች ፍፃሜውን አግኝቷል። በዚህም ቅዱስ ጊዮርጊስና ፋሲል ከተማ የመጀመሪያ የሜዳ ውጭ ድላቸውን በማሳካት መሪነታቸውን ሲያስቀጥሉ፤ አሰልጣኝ የቀየረው ሀዲያ ሆሳዕና፣ ኢትዮጵያ ቡና እና ወልዋሎ አሁንም ማሸነፍ ሳይችሉ ቀርተዋል። እኛም በዚህኛው ሳምንት በነበሩ 8 ጨዋታዎች ላይ የነበሩ ዓበይት ክለብ ነክ ክንውኖችን በተከታዩ መልክ ለመዳሰስ ሞክረናል።

👉 ጥገናን የሚሻው የመቐለ ስብስብና በጫና ውስጥ የሚገኙት ተጫዋቾች

በተጫዋቾች ጉዳት እና መሰል ችግሮች እየታመሰ የሚገኘው መቐለ 70 እንደርታ ለዋንጫ የሚያደርገውን ፉክክር ለማስቀጠል ከቀናት በኃላ በሚከፈተው የውድድር አጋማሹ የዝውውር መስኮት በሁሉም የሜዳ ክፍሎች አማራጩ የጠበበውን ስብስባቸውን ለማጠናከር በንቃት ወደ ገበያ መውጣት እንደሚጠበቅባቸው የቅዳሜው ሽንፈት በደንብ የጠቆመ ይመስላል።

በፋሲል ከተማ በሜዳቸው በተረቱበት ጨዋታ ላይ አሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌ በጣም የሳሳውን ቡድናቸው እንደነገሩ ጠጋግነው ወደ ጨዋታ ገብተዋል። በዚህም በስፋት ከሚጠቀሙባቸው የመጀመሪያ ተሰላፊዎች ተጫዋቾች ውስጥ 5 ተጫዋቾችን ለመቀየር በተገደዱበት ጨዋታ በሜዳቸው በአምናው ብርቱ ተፎካካሪያቸው ፋሲል ከነማ ተሸንፈው አንገታቸውን ለመድፋት ተገደዋል።

መቐለዎች የሊጉን ክብራቸውን ለማስጠበቅ ከፍተኛ ጥረት ያደርጉበታል ተብሎ በሚጠበቀው የዘንድሮው የውድድር ዘመን ቡድናቸው ዐምና ከነበረው ስብስብ ውስጥ ወሳኝ ተጫዋቾችን ድንገት ሳይጠበቅ ከቀጥተኛ ተፎካካሪዎች የለቀቀበት ሒደት በጉልህ ሲጎዳው እየተመለከትን እንገኛለን። በተከላካይ መስመር አምና ጠንካራ የነበረው የአሌክስ እና የአሚኑ የመሀል ተከላካይ ጥምረት ዘንድሮ ከብቃት መዋዠቅና ላውረንስ ኤድዋርድ መፈረም ጋር ተያይዞ እንደቀደሙት ወቅቶች የቡድኑ ደጀንነታቸው አብሯቸው የለም። አማካይ ስፍራ ላይ የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾች የነበሩትን የተከላካይ አማካዮቹ ጋብርኤል አህመድ እና ሀይደር ሸረፋ መልቀቃቸው ቡድኑ በመከላከሉ ሆነ በማጥቃቱ ረገድ በሚታይ መልኩ ሁለቱንም ስለማጣቱ ማስተዋል ይቻላል። በተጨማሪም የሚካኤል ደስታና የዮናስ ገረመው ጉዳት አማካይ ክፍሉ ዳግም እንዲያዋቅር ያስገደደ ሆኗል።

በተጨማሪም በተደጋጋሚ አሰልጣኙ በድህረ ጨዋታ ቃለ ምልልሳቸው ሲነገሩ እንደሚመጡት ተጫዋቾቻቸው በከፍተኛ ጫና ውስጥ እንደሚገኙና ከዚህ በተነሳ ሜዳ ላይ የሚሰጣቸውን ታክቲካዊ ተልዕኮ ለመውጣት እየተቸገሩ ስለመሆናቸው ሲናገሩ ይደመጣል። ለአብነት ያክል ቡድኑ በዘንድሮ የውድድር ዘመን 4 ያክል ፍፁም ቅጣት ምቶችን በሜዳው ቢያገኝም እስካሁን 1 ብቻ አስቆጥሮ በሶስቱ አጋጣሚዎች መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል። ይህም ተጫዋቾች ላይ ያለው የበረታ ጫናን በማሳያነት ማቅረብ ይቻላል።

ስለዚህ አሰልጣኙ በሁለተኛው ዙር የተሻሻለ ቡድን ይዘው ለመቅረብ የተጫዋቾች አማራጫቸውን በግዥዎች ማስፋትና ተጫዋቾች ከጫና ማላቀቅ የግድ ይላቸዋል።

👉 ከሜዳ ውጭ የነበረባቸውን ዓይነ ጥላ የገፈፉት ፋሲል እና ቅዱስ ጊዮርጊስ

በ13ኛ ሳምንት ለዋንጫ ፉክክር የተሻለ ቅድመ ግምት ያላቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ ፋሲል ከነማ በሊጉ ጉዟቸው ላይ ወሳኝ ተልዕኮዎችን ያሳኩበት ሳምንት ነበር። በ12 ሳምንታት የሊጉ ጉዞ ውስጥ ማሳካት ያልቻሉትን የሜዳ ውጭ ድል በዚህኛው ሳምንት ማሳካት ችለዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ መቐለ አምርቶ ፋሲልን በአቤል ያለው እና ጌታነህ ከበደ ሁለት ሁለት ግቦች ወልዋሎን ሲረታ ፋሲል ከተማዎች ደግሞ በተመሳሳይ ሜዳ የዐምናው የሊጉ ባለክብር መቐለ 70 እንደርታን በሙጂብ ቃሲም ሁለት ግቦች እጅ ያሰጡበትን የ2-0 ውጤት ያስመዘገቡበት ሳምንት ነው።

ለወትሮው ኃያልነታቸው በሜዳቸው ብቻ የተገደበ ነው በሚል ወቀሳ ይሰነዘርባቸው የነበሩት ሁለቱ ቡድኖች እውነተኛ የዋንጫ ተፎካካሪ ለመሆን ከሚያበቃቸው አንደኛ ቅድመ ሁኔታን ለሟሟላት የመጀመሪያውን ምዕራፍ ጉዞ የጀመሩበት ሳምንት ሆኖ አልፏል።

👉 የመከላከል ክፍተት በባህር ዳር እና ሰበታ ጨዋታ

በዘመናዊ እግርኳስ ውስጥ መከላከል ከተከላካይ መስመር ተጫዋቾች በዘለለ በጥቅሉ እንደቡድን የሚከወን ተግባር እንደሆነ ይታመናል። ታድያ በዚህ እውነታ መነሾ የዘንድሮው የፋሲል ተካልኙ ባህርዳር ከተማ ከዐምናው የጳውሎስ ጌታቸው ቡድን በግብ ማስቆጠሩ ረገድ በጣም የተሻሻለ የነበረ ቢመስልም የዐምናው ቡድን ዋነኛ ጥንካሬ የነበረውን የመከላከል አደረጃጀት ወደ ዘንድሮ ማሻገር ግን ሳይችሉ ቀርተዋል።

ቡድኑ በአንፃራዊነተ ጥራት ያላቸው የተከላካይ መስመር ተጨዋቾችን ቢይዝም በአጠቃላይ እንደ ቡድን ያለው የመከላከል መዋቅር ግን በየጨዋታዎቹ ግቦችን እንዲያስተናግድ አድርጎታል። በተለይ አጥብበው የሚጫወቱት የቡድኑ የአማካይ መስመር ተጨዋቾች ሽግግር (ከማጥቃት ወደ መከላከል) መንቀራፈፍ ተከላካዮቹን በደንብ አጋልጧል። ከዚህ በተጨማሪ የመስመር አጥቂዎቹ በአብዛኛው ወደፊት ተስቦ መጫወት ክፍተቶችን እያመጣ ይስተዋላል። ከዚህም መነሻነት ቡድኑ ጎሎችን በየጨዋታዎቹ እያስተናገደ ይገኛል።

በተመሳሳይ የባህር ዳር ከተማ ተጋጣሚ የነበረው የሰበታ የተከላካይ መስመር ራሱን ለአደጋ አጋልጦ ሲንቀሳቀስ ተስተውሏል። በተለይ ቡድኑ ከኋላ ጀምሮ ኳሶችን ለመቀባበል የሚያደርገው ጥረት ለተጋጣሚ ምቹ ሁነቶችን ሲፈጥር ታይቷል። ቡድኑ ወደ ባህር ዳር አምርቶ ካስተናገዳቸው ሶስት ጎሎች ሁለቱ በራሱ የኳስ ቅብብል ስህተት የመነጩ ናቸው። ከእነዚህ ጎሎች በተጨማሪ ቡድኑ ወደ ግብነት ያልተቀየሩ ጥቃቶችንም በራሱ የቅብብል ስህተት መነሻነት ሲያስተናግድ ታይቷል። ከምንም በላይ ደግሞ በሁለቱ የመሃል ተከላካዮች መካከል ያለው የጎንዮች ስፋት መርዘሙ ቡድኑ በቶሎ ጥፋቱን እንዳያርም ለአደጋ ዳርጎታል። ከዚህ በተጨማሪ ተከላካዮቹ ኳስ ለመመስረት በሚያደርጉት ጥረት የቅብብል አማራጮችን ከአማካይ መስመር ተጨዋቾች እንደ ልብ አያገኙም። ይህ ደግሞ ተጨዋቾቹ በሚገመት መስመር ብቻ ኳሶችን እንዲቀባበሉ ያደርጋቸዋል።

👉 ከፍ ብሎ መጀመሩ መዘዝ ይዞበት የመጣው ወልዋሎ

በመጀመሪያዎቹ 7 ሳምንታት አልቀመስ ብለው የነበሩት ወልዋሎዎች በሂደት መፈረካከስ ጀምረዋል። አሁን ለወራጅ ቀጠናው እጅግ ተጠግተው በ13ኛ ደረጃ ላይ በ15 ነጥብ ለመቀመጥ ተገደዋል። ላለፉት ስድስት ጨዋታዎች ድል ማድረግ የተሳናቸው ቢጫ ለባሾቹ በዚህኛው ሳምንት ምንም እንኳን የተሻለ መንቀሳቀስ ቢችሉም በአይምሬዎቹ የፈረሰኞቹ አጥቂዎች ተቀጥተው ለመሸነፍ በቅተዋል።

በነበራቸው አስደናቂ አጀማመር የተነሳ እሩቅ ሲያልሙ የከረሙት የወልዋሎ ደጋፊዎች ከሰሞኑ ቡድኑ እየሄደበት ያለውን የእውነታ ፈተና /reality check/ በሆደ ሰፊነት ለመቀበል ተቸግረው ከጊዮርጊሱ ጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ ደጋፊዎች ከፍተኛ ተቃውሞ ሲያሰሙ ተደምጠዋል።

በእርግጥ ቡድኑ ገና በከፍተኛ ደረጃ መጫወትን እየጀማመሩ በሚገኙ ተጫዋቾች እንደመገንባቱና ጨዋታዎችን በተለዋጭ ሜዳ እንደማድረጉ ከደጋፊዎች የሚጠበቀው ትዕግሥት በመጀመሪያዎቹ ሳምንታት የከፍታ ጉዞ ጋር በተያያዘ በተፈጠረው መነቃቃት ሰለባ የሆኑ ይመስላል።

👉 የተጫዋች መጉደል ያልበገራቸው ሽረ እና ጅማ

በዚህ ሳምንት ሁለቱ ቡድኖች ባደረጓቸው ጨዋታዎች ቀደም ብለው ተጫዋቾቻቸውን በቀይ ካርድ በማጣታቸው አመዛኙን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በጎዶሎ የተጫዋቾች ቁጥር ለመጫወት ቢገደዱም በቀላሉ ለተጋጣሚያቸው እጅ አልሰጡም።

ሽረቸች ወደ ድሬዳዋ አምርተው 1-1 በተለያዩበት ጨዋታ 1-0 እየተመራ ገና በ30ኛው ደቂቃ ግብ ጠባቂውን በቀይ ካርድ ቢያጡም በቀሪው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በጥሩ ተነሳሽነት ተጫውተው በሁለተኛው አጋማሽ ባስቆጠሩት ግብ ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል። በተመሳሳይ ገና በ26ኛው ደቂቃ አማካዩ አብርሀም ታምራትን ያጡት ጅማ አባ ጅፋሮች ከሜዳቸው ውጪ በሀዋሳ 1-0 ቢሸነፉም ባለሜዳውን በእጅጉ ፈትነው ተስተውለዋል።

👉 ቢሸነፍም የመሻሻል ፍንጭን ያሳየው የፀጋዬው ሆሳዕና

ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ሀዲያ ሆሳዕና አሰልጣኝነት መንበር የመጡት አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ክለቡን በይፋ ከተረከቡ ከአራት ቀናት ልዩነት በገለልተኛው የሀዋሳ ስታዲየም ገጥመው በጠባብ ውጤት ሽንፈትን አስተናግደዋል።

ቡድኑ በጨዋታ ምንም እንኳን ሽንፈት ያስተናግድ እንጂ ከቀድሞው አሰልጣኙ ጋር ዳግም ከተገናኘው አፈወርቅ ኃይሉ እግር በሚነሱ ተደጋጋሚ ረጃጅም ኳሶች በርካታ እድሎችን መፍጠር ቢችሉም ብኩኖቹ ቢስማርክ አፒያና አፖንግ በሚያስቆጭ መልኩ መጠቀም ሳይችሉ ኳሶቹ ባክነው ቀሩ እንጂ ቢያንስ አንድ ነጥብ ይዘው ሊወጡበት የሚችሉትን አንድ ግብ ማግኘት በተገባቸው ነበር።

አሰልጣኙ ከተጫዋቾቹ ጋር በልምምድ ወቅት በነበራቸው አጭር ቆይታ የተነሳ ከቀደመው አሰልጣኝ ይጠቀምበት ከነበረው የመጀመሪያ ተመራጭ ተጫዋቾች ላይ ከጉዳት የተመለሰው ይሁን እንደሻውን ከመለሱበት ለውጥ ውጭ ይህ ነው የሚባል ለውጥ ሳያደርጉ ወደ ጨዋታው ገብተዋል። በቀጣይም ዝውውር መስኮቱ ከመከፈቱ በፊት ባሉት ቀሪ ሁለት ጨዋታዎች በዚሁ መንገድ እንደሚቀጥሉና በሁለተኛው ዙር መጠነኛ ማሻሻያዎችን አድርገው እንደሚቀርቡ ይጠበቃል።

👉 የሲዳማ የማጥቃት እንቅስቃሴ ያለ አዲስ ግደይ

ከአስፈሪው የሦስትዮሹ የሲዳማ ቡና የአጥቂ መስመር ተሰላፊዎች ውስጥ ዋነኛው ተዋናይ እና የቡድኑ አምበል አዲስ ግደይ በአዳማው ጨዋታ ላይ በነበረበት ጉዳት በተጠባባቂነት ጨዋታውን ቢጀምርም ቡድኑ ግቦችን ከማስቆጠር አላገደውም። ቡድኑ አብዛኞቹ የሀገራችን ክለቦች ግቦችን ለማስቆጠር በተወሰኑ ተፅዕኖ ፈጣሪ ተጫዋቾቻቸው ላይ የመንጠልጠል ሁኔታ ቢያሳዩም ሲዳማ ቡናዎች ግን ያለሁነኛው የፊት መስመር ተሰላፊያቸው አዲስ ግደይ ባደረጉት በዚሁ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ሶስት ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል።

ይህም የአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ስብስብ በማጥቃቱ ረገድ እንደ ቡድን በመንቀሳቀስ ከግለሰብ ጥገኝነት ይልቅ በወጥነት የግብ አጋጣሚዎችን መፍጠር የሚችል ቡድን ለመገንባት ያደረጉት ጥረት ፍሬያማ ስለመሆኑ ማሳያ ነው።

👉 ኢትዮጵያ ቡና ስለምን ተቸገረ?

በሊጉ ከሚገኙና የራሳቸው የሆነ የጠራ የጨዋታ ሀሳብን ሜዳ ላይ ለመተግበር ከሚሞክሩ ቡድኖች አንዱ የሆነው ኢትዮጵያ ቡና ከሰሞኑ ጨዋታዎችን ለማሸነፍ ተቸግሮ ተስተውሏል።

በዚህ ሰሞነኛ የውጤት እጦት ጉዞ ውስጥ ደጋፊዎች በቡድናቸው እንቅስቃሴ ደስተኛ ስላለመሆናቸው በተደጋጋሚ እየተመለከትን እንገኛለን ፤ ነገርግን ቡድኑ “እንደ እሴት” እቆጥረዋለሁ በሚለው የአጨዋወት መንገድን በቁርጠኝነት ለመተግበር የአቅማቸውን ጥረት እያደረጉ የሚገኙት ተጫዋቾች በስህተቶች ውስጥ ሆነው ኳስን ለመቀባበል በሚሞክሩበት ወቅት ኳስን በረጅሙ እንዲያወጡ በደጋፊዎች ይደርስባቸው የነበረ ጫና አንድ ልክ ያልሆነ ነገር ስለመኖሩ ፍንጭ ይሰጣል።

በኳስ ምስረታ ሒደታቸው ላይ መሠረታዊ መሻሻል የሚሹ ነገሮች ስለመኖራቸው ግልፅ ነው። ኳስን ለመመስረት ከሁለቱ የመሀል ተከላካዮችና በ6 ቁጥራቸው ብቻ ለመጠቀም የሚሞክረው የካሳዬው ቡና በተለይ እንደ ትላንቱ 6 ቁጥራቸው በተጋጣሚ ተጫዋች ቢያዝ (man mark ሲደረግ) ቡድኑ ኳስ ወደ መሀለኛው የሜዳ ክፍል ለማሸጋገር እጅጉን ሲቸገሩ ይስተዋላል። በአማራጭነት በመጠኑም ቢሆን በተገፋ አቋቋም ላይ የሚገኙት የመስመር ተከላካዮች በኩል የሚደረገው ጥረትም ከበረኞች የስርጭት አቅም ጋር በተያያዘ በትላንቱ ጨዋታ በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ እስከ 60ኛው ደቂቃ በ6 አጋጣሚዎች በቀጥታ ከበረኛው ወደ መስመር ተከላካይ የተላኩት ኳሶች ሲባክኑ ተስተውሏል።

አሰልጣኙ ምንም እንኳን በዚህ የምስረታ አማራጭ ላይ የፀና እምነት እንዳለው በድህረ ጨዋታ ቃለምልልሶቹ ከሚሰጠው ሀሳብ መረዳት ቢቻልም እንደ ወልቂጤ ከተማ ሁሉ ተጋጣሚዎች ለዚህ ሂደት መላ የሚዘይዱ ከሆነ ቡድን ይህን የምስረታ ሂደት ላይ አማራጭ መንገዶችን መፈለግ በአጠቃላይ የቡድኑ አጨዋወት ላይ የሚኖረው አዎንታዊ ተፅዕኖ የጎላ ነውና ይህን አጢኖ ሌሎች ተለዋዋጭ መንገዶችን መፈለግ በአጠቃላይ ለቡድኑ ሰሞነኛ ችግሮች ቁልፉ እዚህ ላይ የሚወድቅ ይሆናል።

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ